ለሁሉም ነገር ወቅት አለው
ለሁሉ ጊዜ አለው፤ ለመወለድና ለመሞት፣ ለጦርነትና ለሰላም። እግዚአብሔር ዘላለምን በሰው ልብ ቢያኖርም፣ ማንም የሠራውን ሁሉ ሊረዳ አይችልም። ፍትሕ ሊኖር በሚገባው ስፍራ ብልሹነት ተቀምጧል። ሰዎችና እንስሶች አንድ እስትንፋስ ይተነፍሳሉ፤ አንድ መቃብርም ይጋራሉ።
3 1ለሁሉም ነገር ወቅት አለው፤ ከሰማይ በታችም ላለ ለማንኛውም ነገር ጊዜ አለው፦ 2የመወለጃ ጊዜ፣ የመሞቻም ጊዜ፤ የመትከያ ጊዜ፣ የተተከለውንም የመንቀያ ጊዜ፤ 3የመግደያ ጊዜ፣ የመፈወሻም ጊዜ፤ የማፍረሻ ጊዜ፣ የመሥሪያም ጊዜ፤ 4የማልቀሻ ጊዜ፣ የመሳቂያም ጊዜ፤ የማዘኛ ጊዜ፣ የመደነሻም ጊዜ፤ 5ድንጋይ የመበተኛ ጊዜ፣ ድንጋይ የመሰብሰቢያም ጊዜ፤ የመተቃቀፊያ ጊዜ፣ ከመተቃቀፍም የመከልከያ ጊዜ፤ 6የመፈለጊያ ጊዜ፣ የማጣትም ጊዜ፤ የመጠበቂያ ጊዜ፣ የመጣያም ጊዜ፤ 7የመቅደጃ ጊዜ፣ የመስፊያም ጊዜ፤ ዝም የመሰኛ ጊዜ፣ የመናገሪያም ጊዜ፤ 8የመውደጃ ጊዜ፣ የመጥላትም ጊዜ፤ የጦርነት ጊዜ፣ የሰላምም ጊዜ።
9ሠራተኛው ከድካሙ ምን ትርፍ ያገኛል? 10እግዚአብሔር ሰዎች እንዲደክሙበት የሰጣቸውን ሥራ አየሁ። 11ሁሉን ነገር በየጊዜው ያማረ አድርጎ ሠራ፤ ዘላለምነትንም በሰው ልብ ውስጥ አኖረ፤ ሆኖም ማንም እግዚአብሔር ከጥንት እስከ መጨረሻ ያደረገውን ሊያስተውል አይችልም። 12ሰዎች በሕይወታቸው ዘመን ደስ ከመሰኘትና መልካም ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐውቃለሁ። 13ደግሞም ሰው ሁሉ እንዲበላ፣ እንዲጠጣና በድካሙ ሁሉ እንዲረካ፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 14እግዚአብሔር የሚያደርገው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር ዐውቃለሁ፤ በእርሱ ላይ ምንም ሊጨመር፣ ከእርሱም ምንም ሊቀነስ አይችልም። ሰዎችም በፊቱ እንዲፈሩ እርሱ ይህን አደረገ። 15አሁን ያለው አስቀድሞ የነበረ ነው፤ የሚመጣውም አስቀድሞ የነበረ ነው፤ እግዚአብሔርም የተባረረውን ይሻል።
ክፋት በፍትሕ ስፍራ
16ደግሞም ከፀሓይ በታች ይህን አየሁ፤ በፍርድ ስፍራ ክፋት፣ በጽድቅም ስፍራ ክፋት ነበረ። 17በልቤ እንዲህ አልሁ፤ “እግዚአብሔር ጻድቁንም ክፉውንም ይፈርዳል፤ ለማንኛውም ነገርና ለማንኛውም ሥራ በዚያ ጊዜ አለውና።” 18በልቤ እንዲህ አልሁ፤ “እግዚአብሔር ሰዎችን ይፈትናል፤ ራሳቸውም እንስሳት ብቻ መሆናቸውን እንዲያዩ ያደርጋል።” 19ሰዎችና እንስሳት አንድ ዕጣ ይጋራሉ፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም ይሞታል፤ ሁለቱም አንድ ዐይነት እስትንፋስ አላቸው። ሰው ከእንስሳ የሚበልጥ ጥቅም የለውም፤ ሁሉ እንፋሎት ነው። 20ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ ይሄዳል፤ ሁሉ ከዐፈር ተገኘ፤ ሁሉም ወደ ዐፈር ይመለሳል። 21የሰው መንፈስ ወደ ላይ ይወጣ እንደሆነ፣ የእንስሳም መንፈስ ወደ ታች ወደ ምድር ይወርድ እንደሆነ ማን ያውቃል? 22ስለዚህ ሰው ዕጣው ይህ ስለ ሆነ፣ በሥራው ደስ ከመሰኘት የተሻለ ነገር እንደሌለ አየሁ። ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ሊያሳየው የሚችል ማን ነውና?