የአባታችን ብርሃን ሊገታ አይችልም
በሁለት የወይራ ዛፎች የሚመገብ የወርቅ መቅረዝ፣ ትንሽና ያልተጠናቀቀ መቅደስ ተስፋ ላስቈረጠው ለዘሩባቤል መልስ ይሆናል። የአብ ቃል ለእርሱ፦ በኃይል አይደለም፣ በብርታትም አይደለም፣ በመንፈሴ ነው እንጂ። መሠረቱን የጣሉት እጆች ይፈጽሙታል፤ ማንም ትንሹን ነገር አይናቅ።
4 1ከዚያም ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረው መልአክ ተመልሶ፣ ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው ቀሰቀሰኝ። 2እርሱም፣ “ምን ታያለህ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም እንዲህ አልሁ፤ “የወርቅ መቅረዝ ዐየሁ፤ በላዩ ላይ ጽዋ፣ ሰባት መብራቶችም፣ በላዩ ላይ ላለው ለእያንዳንዱ መብራት ሰባት ቱቦዎች አሉት።
3ሁለት የወይራ ዛፎች በአጠገቡ ይቆማሉ፤ አንዱ ከጽዋው ቀኝ፣ ሌላው ከግራው።”
4ከእኔም ጋራ ይነጋገር የነበረውን መልአክ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት።
5ከእኔም ጋራ ይነጋገር የነበረው መልአክ፣ “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን?” አለኝ። እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አላውቅም” አልሁ።
6እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ይህ የአባታችን ቃል ለዘሩባቤል ነው፤ ‘በጦር ኀይል አይደለም፣ በብርታትም አይደለም፣ ነገር ግን በመንፈሴ ነው’ ይላል የሰማይ ሰራዊት አባት። 7ታላቅ ተራራ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ መሬት ትሆናለህ። እርሱም፣ ‘ጸጋ፣ ጸጋ ይሁንለት!’ እያለ እየጮኸ የማዕዘን ድንጋዩን ያወጣል።”
8ከዚያም የአባታችን ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
9“የዘሩባቤል እጆች የዚህን ቤት መሠረት ጣሉ፤ እጆቹም ይፈጽሙታል። ያን ጊዜ የሰማይ ሰራዊት አባት ወደ አንተ እንደ ላከኝ ታውቃለህ። 10ቀኑን የናቀ ማን ነው? ታናናሽ ነገሮችን የናቀ ማን ነው? በዘሩባቤል እጅ ያለውን የቱንቢ ገመድ አይተው ደስ ይላቸዋል። እነዚህ ሰባቱ በመላው ምድር የሚመለከቱ የአባታችን ዐይኖች ናቸው።”
11ከዚያም፣ “ከመቅረዙ ቀኝና ግራ ያሉት እነዚህ ሁለቱ የወይራ ዛፎች ምንድን ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት። 12ዳግመኛም፣ “የወርቅ ዘይት በሚያፈሱ በሁለቱ የወርቅ ቱቦዎች አጠገብ ያሉት እነዚህ ሁለቱ የወይራ ቅርንጫፎች ምንድን ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት።
13እርሱም፣ “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን?” አለኝ። እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አላውቅም” አልሁ።
14እርሱም፣ “እነዚህ በመላው ምድር ጌታ አጠገብ የሚቆሙ ሁለቱ የተቀቡ ናቸው” አለ።