ትውፊት በአብ ቃል ላይ
ኢየሱስ ለፈሪሳውያን ወጋቸው የአብን የገዛ ትእዛዝ እንደ ሻረ፣ የሚያረክሰውም ወደ አፍ የሚገባ ሳይሆን ከልብ የሚወጣ እንደ ሆነ ይነግራቸዋል። አንዲት ከነዓናዊት ሴት ለመመለስ እምቢ ትላለች፣ መልስም ትሰጠዋለች፤ የምትሠቃየው ልጇም ትፈወሳለች።
15 1ከዚያም ፈሪሳውያንና ጻፎች ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ አሉ፤ 2“ደቀ መዛሙርትህ የሽማግሌዎችን ትውፊት ለምን ይተላለፋሉ? በሚበሉበት ጊዜ እጃቸውን አይታጠቡም።”
3እርሱም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እናንተስ ስለ ትውፊታችሁ የአባታችንን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? 4አባታችን፣ ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ አለ፤ ደግሞም፣ ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ሁሉ በእርግጥ ይገደል’ ብሏል። 5እናንተ ግን፣ ‘ማንም ሰው አባቱን ወይም እናቱን፣ “ከእኔ የምታገኘው ሁሉ ለአባታችን የተሰጠ መባ ነው” ቢል፣ 6በዚያ አባቱን ማክበር አያስፈልገውም’ ትላላችሁ። ስለ ትውፊታችሁም የአባታችንን ቃል ሽራችኋል። 7እናንተ ግብዞች! ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ሲል በትክክል ትንቢት ተናግሯል፤ 8‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ ዘንድ የራቀ ነው፤ 9በከንቱ ያመልኩኛል፤ የሰውን ትእዛዛት እንደ ትምህርት እያስተማሩ።’”
10ከዚያም ሕዝቡን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ስሙ፤ አስተውሉም፤ 11ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባው አይደለም፤ ሰውን የሚያረክሰው ግን ከአፍ የሚወጣው ነው።”
12ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ፈሪሳውያን ይህን ቃል በሰሙ ጊዜ እንደ ተሰናከሉ ታውቃለህ?” አሉት።
13እርሱም መልሶ እንዲህ አለ፤ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። 14ተዋቸው፤ እነርሱ ዕውር መሪዎች ናቸው። ዕውር ዕውርን ቢመራ፣ ሁለቱም ጕድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ።”
15ጴጥሮስም፣ “ይህን ምሳሌ ፍታልን” አለው።
16ኢየሱስም፣ “እናንተም ገና እንደ ሌሎቹ የማታስተውሉ ናችሁን?” አለ። 17“ወደ አፍ የሚገባው ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ከዚያም ወደ ውጭ እንደሚጣል አታስተውሉምን? 18ከአፍ የሚወጣው ግን ከልብ ይመጣል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው። 19ከልብ ክፉ አሳቦች፣ ነፍስ መግደል፣ ምንዝር፣ ዝሙት፣ ስርቆት፣ ሐሰተኛ ምስክርነትና ስም ማጥፋት ይወጣሉና። 20ሰውን የሚያረክሱት እነዚህ ናቸው፤ ባልታጠበ እጅ መብላት ግን ማንንም አያረክስም።”
የአንዲት ሴት የጸና እምነት
21ኢየሱስም ከዚያ ስፍራ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ሲዶና አውራጃ ፈቀቅ አለ። 22ከዚያ አካባቢ የመጣች አንዲት ከነዓናዊት ሴትም እየጮኸች፣ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ማረኝ! ልጄ በጋኔን ክፉኛ ትሠቃያለች” አለች።
23እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፣ “ከኋላችን ስትጮኽ ናትና አሰናብታት” ብለው ለመኑት።
24እርሱም መልሶ፣ “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች ብቻ ተልኬአለሁ” አለ።
25እርሷ ግን መጥታ በፊቱ ተንበርክካ፣ “ጌታ ሆይ፣ እርዳኝ!” አለች።
26እርሱም መልሶ፣ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል ተገቢ አይደለም” አለ።
27እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ ነገር ግን ውሾች እንኳ ከጌቶቻቸው ማዕድ ላይ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች።
28ኢየሱስም መልሶ፣ “አንቺ ሴት፣ እምነትሽ ታላቅ ነው። እንደ ፈለግሽ ይሁንልሽ” አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች።
አባታችን አራት ሺሑን መገበ
29ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ በገሊላ ባሕር አጠገብ አለፈ፤ ወደ ተራራውም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። 30ብዙ ሕዝብም ዐንካሶችን፣ ዕውሮችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ዲዳዎችንና ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ መጡ፤ በእግሩም ፊት አኖሯቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። 31ሕዝቡም ዲዳዎች ሲናገሩ፣ አካለ ስንኩሎች ሲድኑ፣ ዐንካሶች ሲሄዱ፣ ዕውሮችም ሲያዩ አይቶ ተደነቀ፤ የእስራኤልንም አባት አከበሩ።
32ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ይህ ሕዝብ ያሳዝነኛል፤ ከእኔ ጋራ ሦስት ቀን ቈይተዋል፤ የሚበሉትም የላቸውም። ተርበው ላሰናብታቸው አልወድድም፤ በመንገድ ሊዝሉ ይችላሉና።”
33ደቀ መዛሙርቱም፣ “ይህን የመሰለውን ሕዝብ ለማጥገብ የሚበቃ እንጀራ በዚህ ምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን?” አሉት።
34ኢየሱስም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሰባት፣ ጥቂት ታናናሽ ዓሣዎችም አሉን” አሉ።
35እርሱም ሕዝቡ በመሬት ላይ እንዲቀመጥ አዘዘ። 36ሰባቱንም እንጀራና ዓሣዎቹን ወስዶ አመስግኖ ቈረሰ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሰጠ፤ እነርሱም ለሕዝቡ አደሉ። 37ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ሙሉ ቅርጫት ሰበሰቡ። 38የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች ሌላ አራት ሺሕ ወንዶች ነበሩ። 39ሕዝቡንም አሰናብቶ ወደ ታንኳ ገባ፤ ወደ መጋዳን አካባቢም መጣ።