የመጥምቁ ዮሐንስ ሞት
ሄሮድስ በግብዣ ላይ በማለው መሐላ ተይዞ የዮሐንስን ራስ ያስቈርጣል። ኢየሱስ ለማዘን ገለል ይላል፤ ሕዝቡ ግን ይከተሉታል፤ እርሱም በአምስት እንጀራ ይመግባቸዋል። በኋላም ጴጥሮስ በውኃው ላይ ወደ እርሱ ይራመዳል፤ ነፋሱን አይቶ መስጠም ይጀምራል።
14 1በዚያን ጊዜ የአውራጃው ገዥ ሄሮድስ ስለ ኢየሱስ የተነገረውን ወሬ ሰማ። 2አገልጋዮቹንም፣ “ይህ ከሙታን የተነሣው መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ ስለዚህ እነዚህ ኀይላት በእርሱ ይሠራሉ” አላቸው። 3ሄሮድስ የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት ስለ ነበረችው ስለ ሄሮድያዳ ዮሐንስን አስይዞ አስሮ በወኅኒ ዘግቶት ነበርና፤ 4ዮሐንስ፣ “እርሷን ለአንተ ማግባት አይገባህም” ይለው ነበርና። 5ሄሮድስም ሊገድለው ፈልጎ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ይቈጥሩት ስለ ነበር ፈራቸው። 6ነገር ግን የሄሮድስ የልደት በዓል በደረሰ ጊዜ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች፤ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው። 7ስለዚህ የለመነችውን ሁሉ ሊሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። 8በእናቷ ተመክራ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በዚህ፣ በወጭት አምጥተህ ስጠኝ” አለች።
9ንጉሡም አዘነ፤ ነገር ግን ስለ መሐላውና በማእድ አብረውት ስለ ተቀመጡት እንዲሰጣት አዘዘ፤ 10ልኮም ዮሐንስን በወኅኒ ውስጥ አንገቱን አስቈረጠ። 11ራሱም በወጭት መጥቶ ለብላቴናዪቱ ተሰጠ፤ እርሷም ወደ እናቷ ወሰደችው። 12ከዚያም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት መጥተው ሬሳውን ወስደው ቀበሩት፤ ሄደውም ለኢየሱስ ነገሩት።
ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መገበ
13ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ ለብቻው በታንኳ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ፈቀቅ አለ። ሕዝቡ ግን ሰምተው ከከተሞች በእግራቸው ተከተሉት። 14ከታንኳውም በወጣ ጊዜ ብዙ ሕዝብ አየ፤ አዘነላቸውም፤ ድውዮቻቸውንም ፈወሰ። 15በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ይህ ገለልተኛ ስፍራ ነው፤ ጊዜውም አሁን አልፏል። ሕዝቡ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ አሰናብታቸው” አሉት።
16ኢየሱስ ግን፣ “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ ስጧቸው” አላቸው።
17እነርሱም፣ “በዚህ ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር ምንም የለንም” አሉት።
18እርሱም፣ “ወደዚህ ወደ እኔ አምጡልኝ” አለ።
19ሕዝቡም በሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ። አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየ፤ አመስግኖም እንጀራውን ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ሰጡ። 20ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከተረፈውም ቍርስራሽ ዐሥራ ሁለት ሙሉ መሶብ አነሡ። 21የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አምስት ሺህ ያህል ወንዶች ነበሩ።
ኢየሱስ በውሃ ላይ ተራመደ
22ወዲያውም ሕዝቡን እስኪያሰናብት ድረስ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ ገብተው ቀድመውት ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አደረጋቸው። 23ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ሊጸልይ ለብቻው ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ በዚያ ብቻውን ነበር። 24ታንኳዪቱም ያን ጊዜ ከየብስ ርቃ ነበር፤ ነፋሱ ከፊት ለፊታቸው ስለ ነበር በማዕበል ትናወጥ ነበር። 25ከሌሊቱም ዘጠኝ ሰዓት ገደማ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ። a a v25 የሌሊቱ አራተኛው ክፍለ ጊዜ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት እስከ ንጋቱ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ገደማ ነበር፤ ከጎሕ በፊት እጅግ የጨለመውና የቀዘቀዘው ጊዜ ነው። 26ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲራመድ ባዩት ጊዜ፣ “ምትሀት ነው!” ብለው እጅግ ደንግጠው ከፍርሃታቸው የተነሣ ጮኹ።
27ኢየሱስ ግን ወዲያው፣ “አይዟችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” ብሎ ተናገራቸው።
28ጴጥሮስም መልሶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ከሆንህ በውሃ ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው።
29እርሱም፣ “ና” አለው። ጴጥሮስም ከታንኳው ወርዶ በውሃ ላይ ተራምዶ ወደ ኢየሱስ ሄደ።
30ነገር ግን ኀይለኛውን ነፋስ ባየ ጊዜ ፈራ፤ መስጠምም በጀመረ ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፤ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ።
31ኢየሱስም ወዲያው እጁን ዘርግቶ ያዘው፤ “አንተ እምነት የጐደለህ፤ ለምን ተጠራጠርህ?” አለው።
32ወደ ታንኳውም በገቡ ጊዜ ነፋሱ ጸጥ አለ። 33በታንኳው የነበሩትም፣ “በእውነት አንተ የአባታችን ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት።
34ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር ደረሱ። 35የዚያ ስፍራ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ ወደ አካባቢው ሁሉ ልከው ድውዮችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ። 36የልብሱንም ጫፍ ብቻ እንዲዳስሱ ለመኑት፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።