የበደል መሥዋዕት ሕግ
የበደልና የኅብረት መሥዋዕቶች በዝርዝር ይቀርባሉ፤ የምስጋና ሥጋ በዚያው ቀን ይበላል፤ የስእለት ቍርባን በሁለት ቀን ውስጥ፤ እስከ ሦስተኛው ቀን የቀረ ሁሉ ይቃጠላል። ስብ ወይም ደም የበላ፣ ወይም ርኩስ ሆኖ የበላ ሰው ይወገዳል፤ ፍርምባውና ቀኙ ወርች ለካህናት ይሰጣሉ።
7 1“የበደል መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ እጅግ ቅዱስ ነው። 2የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት ስፍራ የበደል መሥዋዕቱን ያርዱ፤ ደሙንም በመሠዊያው ዙሪያ ሁሉ ይርጩ። 3ስቡ ሁሉ ይቀርባል፤ የሰባው ጭራና የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነው ስብ፣ 4ሁለቱ ኵላሊቶችና በወገብ አካባቢ ያለባቸው ስብ፣ ከኵላሊቶቹ ጋራ የሚወጣው የጒበት ድርብ። 5ካህኑም ለአባታችን በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥላቸዋል፤ የበደል መሥዋዕት ነው። 6ከካህናት ወንድ የሆነ ሁሉ ሊበላው ይችላል፤ በተቀደሰ ስፍራ ብቻ ይበላል፤ እጅግ ቅዱስ ነው።
7“የኀጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት አንድ ሕግ አላቸው፤ በእርሱ ማስተስረያ ለሚያደርገው ካህን ይሆናል። 8የማንም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ካህን የመሥዋዕቱን ቍርበት ለራሱ ይወስዳል። 9በምድጃ የተጋገረ የእህል ቍርባን ሁሉ፣ በምጣድ ወይም በሳሕን የተዘጋጀም ሁሉ ለሚያቀርበው ካህን ይሆናል። 10በዘይት የተለወሰ ወይም ደረቅ የእህል ቍርባን ሁሉ ለአሮን ልጆች ሁሉ በእኩል ይሆናል።
የኅብረት መሥዋዕት ሕግ
11“ማንም ሰው ለአባታችን የሚያቀርበው የኅብረት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። 12ለምስጋና መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው ከሆነ፣ ከእርሱ ጋራ እርሾ የሌለበት በዘይት የተለወሰ ቂጣ፣ እርሾ የሌለበት በዘይት የተቀባ ስስ እንጀራ፣ በዘይት ተለውሶ በደንብ የተቦካ መልካም ዱቄት ቂጣ ያቅርብ። 13ከምስጋና የኅብረት መሥዋዕቱ ጋራ እርሾ ያለበት ዳቦ ያቅርብ። 14ከእያንዳንዱም አንዳንድ ለአባታችን መባ አድርጎ ያቅርብ፤ የኅብረት መሥዋዕቱን ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል። 15የምስጋናው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ በተቀረበበት ቀን ይበላል፤ ከእርሱ ምንም እስከ ጥዋት ድረስ አይቈይ።
16“መሥዋዕቱ የስእለት ወይም በፈቃደኝነት የሚቀርብ መሥዋዕት ቢሆን ግን፣ ባቀረበበት ቀን ይበላል፤ የተረፈውም በማግስቱ ሊበላ ይችላል። 17ከመሥዋዕቱ ሥጋ በሦስተኛው ቀን የተረፈው ግን በእሳት ይቃጠል። 18ከኅብረት መሥዋዕቱ ሥጋ በሦስተኛው ቀን ቢበላ፣ ተቀባይነት አያገኝም፤ ላቀረበውም አይቈጠርለትም፤ የረከሰ ነው፤ የበላውም ኀጢአቱን ይሸከማል።
19“ርኩስ የሆነ ማናቸውንም ነገር የነካ ሥጋ አይበላም፤ ያ ሥጋ በእሳት ይቃጠል። ሌላውን ሥጋ ግን ንጹሕ የሆነ ሁሉ ሊበላው ይችላል። 20ርኩስ ሆኖ ሳለ የአባታችንን የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ የሚበላ ሁሉ ከወገኖቹ ተለይቶ ይጠፋል። a a v20 ‘ከወገኖቹ ተለይቶ ይጠፋል’ ማለት ከእስራኤል የኪዳን ማኅበር መለየት ማለት ሲሆን፣ ይህም ምናልባት በመለኮታዊ ፍርድ ወይም በማኅበሩ ርምጃ ይፈጸማል። 21ርኩስ የሆነ ማናቸውንም ነገር፣ የሰውን ርኩሰት ወይም ርኩስ እንስሳ ወይም ማናቸውንም ርኩስና አስጸያፊ ነገር የነካ፣ ከዚያም የአባታችንን የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ የሚበላ ሰው ከወገኖቹ ተለይቶ ይጠፋል።”
አባታችን ስብንና ደምን ይከለክላል
22አባታችን ሙሴን እንዲህ አለው፤
23“ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ከበሬ፣ ከበግ ወይም ከፍየል ምንም ስብ አትብሉ። 24ከሬሳ ወይም በአውሬ ከተገደለ እንስሳ የተገኘ ስብ ለማናቸውም ነገር ሊያገለግል ይችላል፤ ነገር ግን ከቶ አትብሉት። 25ለእኔ በእሳት ከሚቀርብ እንስሳ ስብ የሚበላ ሁሉ ከወገኖቹ ተለይቶ ይጠፋል። 26በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ከወፍ ወይም ከእንስሳ ምንም ደም ከቶ አትብሉ። 27ማናቸውንም ደም የሚበላ ሁሉ ከወገኖቹ ተለይቶ ይጠፋል።”
የካህናቱ ድርሻ
28አባታችን ሙሴን እንዲህ አለው፤
29“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ የኅብረት መሥዋዕቱን ለእኔ የሚያቀርብ ሁሉ ከዚያ መሥዋዕት ቍርባኑን ለእኔ ያምጣ። 30በእሳት የሚቀርብልኝን መሥዋዕት በእጆቹ ያምጣ፤ ስቡን ከደረቱ ጋራ ያምጣ፤ ደረቱንም በፊቴ የሚወዘወዝ ቍርባን አድርጎ ይወዝውዘው። 31ካህኑም ስቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል፤ ደረቱ ግን ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል። 32ከኅብረት መሥዋዕታችሁም የቀኙን ታፋ መባ አድርጋችሁ ለካህኑ ስጡ። 33ከአሮን ልጆች የኅብረት መሥዋዕቱን ደምና ስብ የሚያቀርበው የቀኙን ታፋ እንደ ድርሻው ያገኛል። 34ከእስራኤል ልጆች የኅብረት መሥዋዕት የሚወዘወዘውን ደረትና የመባውን ታፋ ወስጄ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹ ከእስራኤል ዘንድ የዘላለም ድርሻ አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁና።”
35ይህ ለአባታችን ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ከቀረቡበት ቀን ጀምሮ፣ ከአባታችን በእሳት ከሚቀርቡ መሥዋዕቶች ለአሮንና ለልጆቹ የተወሰነ ድርሻ ነው። 36አባታችን በቀባቸው ቀን ይህ ከእስራኤል ልጆች እንዲሰጣቸው አዘዘ፤ ለትውልዳቸውም ሁሉ የዘላለም ድርሻ ነው። 37ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ ለእህል ቍርባን፣ ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ለበደል መሥዋዕት፣ ለሹመት መሥዋዕትና ለኅብረት መሥዋዕት ሕጉ ይህ ነው፤ 38ይህም አባታችን በሲና ተራራ ላይ ሙሴን ያዘዘው፣ በሲና ምድረ በዳ የእስራኤል ልጆች ቍርባናቸውን ለአባታችን እንዲያቀርቡ ባዘዘበት ቀን ነው።