የበደል መሥዋዕት
ባልንጀራን በአደራ ዕቃ ወይም በወደቀ ዕቃ ማታለል ለአባታችሁ እንደ አለመታመን ይቈጠራል፤ ሙሉውን መልሱ፣ አንድ አምስተኛ ጨምሩ፣ ከዚያም አውራውን በግ አምጡ። የመሠዊያው እሳት ፈጽሞ መጥፋት የለበትም፤ ከእህልና ከኃጢአት መሥዋዕቶችም የካህናት ድርሻ ይወሰናል።
6 1አባታችን ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦
2“ማንም ሰው ቢበድል፣ ለአባታችሁ ታማኝ ሳይሆን፣ ባልንጀራውን በአደራ ነገር፣ በመያዣ ወይም በተሰረቀ ዕቃ ቢያታልል ወይም ቢያጭበረብረው፣ 3ወይም የጠፋ ነገር አግኝቶ ስለ እርሱ ቢዋሽ፣ በሐሰት ቢምል፦ ሰው በእነዚህ በመሰሉ በማናቸውም ተግባር ኀጢአት ይሠራል። 4በድሎ በደለኛ በሆነ ጊዜ፣ የሰረቀውን ወይም በግፍ የወሰደውን ወይም የተሰጠውን አደራ ወይም ያገኘውን የጠፋ ነገር ይመልስ፤ 5ወይም በሐሰት የማለበትን ማናቸውንም ነገር፣ ሙሉ በሙሉ ይክፈል፤ አንድ አምስተኛውንም በላዩ ይጨምር፤ በደሉን በሚያምንበት ቀን ለባለቤቱ ይስጠው። 6የበደል መሥዋዕቱን ለአባታችሁ ያቅርብ፤ ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ፣ አንተ በገመትኸው ዋጋ፣ ለበደል መሥዋዕት አድርጎ ለካህኑ ይስጥ። 7ካህኑም በአባታችሁ ፊት ያስተሰርይለታል፤ ያደረገውም በደለኛ ያደረገው ማናቸውም ነገር ይቅር ይባልለታል።”
የሚቃጠለው መሥዋዕት
8ከዚያም አባታችን ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦
9“አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ የሚቃጠለው መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ ሌሊቱን ሙሉ እስከ ማለዳ ድረስ በመሠዊያው ምድጃ ላይ ይቈይ፤ የመሠዊያውም እሳት በላዩ ነድዶ ይቈይ። 10ካህኑም የተልባ እግር ልብሱን ይልበስ፤ የተልባ እግር ሰናፊልም በገላው ላይ ያድርግ፤ ከዚያም እሳቱ በመሠዊያው ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ከበላ በኋላ የቀረውን ዐመድ አንሥቶ በመሠዊያው አጠገብ ያኑረው። 11ከዚያም ልብሱን አውልቆ ሌላ ለብሶ ዐመዱን ከሰፈሩ ውጭ ወዳለ ንጹሕ ስፍራ ያውጣው። 12የመሠዊያው እሳት ነድዶ ይቈይ፤ አይጥፋም። ካህኑም በየማለዳው በላዩ ዕንጨት ይጨምር፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በላዩ ያስተካክል፤ የደኅንነትንም መሥዋዕት ስብ በላዩ ያቃጥል። 13እሳቱ ዘወትር በመሠዊያው ላይ ነድዶ ይቈይ፤ አይጥፋም።
የእህል መሥዋዕት
14“የእህል መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የአሮን ልጆች በአባታችሁ ፊት፣ በመሠዊያው ፊት ለፊት ያቅርቡት። 15ካህኑም ከእህል መሥዋዕቱ ከላመ ዱቄትና ከዘይት እፍኝ ሙሉ፣ ከነሙሉ ዕጣኑ ይውሰድ፤ ይህን መታሰቢያ ፈንታ ለአባታችሁ ደስ የሚያሰኝ መዓዛ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል። 16የቀረውንም አሮንና ልጆቹ ይብሉት፤ ያለ እርሾ በተቀደሰ ስፍራ ይበላ፤ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ይበላ። 17በእርሾ አይጋገር። ከምግብ መሥዋዕቴ እንደ ኀጢአትና እንደ በደል መሥዋዕት ድርሻቸው አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እጅግ የተቀደሰ ነው። 18ከአሮን ዘር ወንድ የሆነ ሁሉ ይብላው፤ ይህ ከአባታችሁ ምግብ መሥዋዕት በትውልዳችሁ ሁሉ የሚኖር የዘላለም ድርሻ ነው። የሚነካቸውም ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል።”
19አባታችን ሙሴን እንዲህ አለው፦
20“አሮንና ልጆቹ በሚቀቡበት ቀን ለአባታችሁ የሚያቀርቡት መሥዋዕት ይህ ነው፦ መደበኛ የእህል መሥዋዕት የሚሆን ሁለት ሊትር ያህል ላመ ዱቄት፤ እኩሌታው በማለዳ፣ እኩሌታው በማታ ይቅረብ። 21በዘይት በምጣድ ላይ ይዘጋጅ፤ መልካም አድርገህ አብኩተህ አምጣው፤ የእህሉን መሥዋዕት ቈራርሰህ አቅርብ፤ ለአባታችሁ ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ነው። 22ከልጆቹም መካከል በእርሱ ፋንታ የሚቀባው ካህን ያዘጋጀው፤ ይህ በአባታችሁ ፊት የዘላለም ሥርዐት ነው፤ ፈጽሞ ይቃጠል። 23የካህኑ የእህል መሥዋዕት ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠል፤ አይበላም።”
የኀጢአት መሥዋዕት
24ደግሞም አባታችን ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦
25“አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የኀጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በአባታችሁ ፊት ይታረድ፤ እጅግ የተቀደሰ ነው። 26ስለ ኀጢአት የሚያቀርበው ካህን ይብላው፤ በተቀደሰ ስፍራ፣ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ይበላ። 27ሥጋውን የሚነካ ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል። ደሙም በልብስ ላይ ቢረጭ፣ የተረጨበትን ስፍራ በተቀደሰ ስፍራ እጠበው። 28የተቀቀለበት የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ በናስ ዕቃ ቢቀቀል ግን ይፈቅ፤ በውሃም ይታጠብ። 29ከካህናቱ ወንድ የሆነ ሁሉ ይብላው፤ እጅግ የተቀደሰ ነው። 30ደሙ በተቀደሰው ስፍራ ለማስተስረይ ወደ መገናኛው ድንኳን የሚገባ የኀጢአት መሥዋዕት ግን አይበላም፤ በእሳት ይቃጠል።”