የሜዳ አህያን ነጻ ያወጣ ማን ነው?
ጥያቄው የሰው አስተዳደር በማያስፈልጋቸው የዱር ፍጥረታት ይቀጥላል፤ ብቻቸውን የሚወልዱ የተራራ ፍየሎች፣ ከተማን የሚንቅ የዱር አህያ፣ እንቁላሎቿን የምትረሳ ሰጎን፣ በፍርሃት የሚስቅ ፈረስ፣ በገደሉ ላይ ያለ ንስር። ከእነዚህ አንዳቸውም ለኢዮብ ምቾት የሚኖሩ አይደሉም።
39 1"የተራራ ፍየሎች መቼ እንደሚወልዱ ታውቃለህ? ዋላዎች ሲወልዱ ትጠብቃቸዋለህን? 2ፅንሳቸውን የሚሸከሙባቸውን ወራት መቍጠር ትችላለህን? የሚወልዱበትንስ ጊዜ ታውቃለህን? 3ተንበርክከው ይወልዳሉ፤ የምጥ ሥቃያቸውም ያልፋል። 4ልጆቻቸው በሜዳ ላይ ይጠነክራሉ፤ ይሄዳሉ፣ ተመልሰውም አይመጡም።
5"የሜዳ አህያን ነጻ ያወጣ ማን ነው? የፈጣኑን አህያ ገመድ የፈታስ ማን ነው? 6ለመኖሪያው ምድረ በዳውን፣ ለማደሪያውም የጨው ሜዳውን የሰጠሁት ለማን ነው? 7የከተማውን ጫጫታ ይንቃል፤ የነጂንም ጩኸት ከቶ አይሰማም። 8ለግጦሹ ተራሮችን ይዞራል፤ አረንጓዴውን ሁሉ ይፈልጋል።
9"የሜዳ በሬ ሊያገለግልህ ይፈቅዳልን? በግርግምህ አጠገብ ያድራልን? 10የሜዳውን በሬ በገመድ ከትልም ጋራ ማሰር ትችላለህን? ሸለቆዎችንስ ተከትሎህ ያርሳልን? 11ኀይሉ ታላቅ ስለ ሆነ በእርሱ ትመካለህን? ድካምህንስ ለእርሱ አደራ ትሰጣለህን? 12እህልህን መልሶ እንዲያመጣ፣ ወደ አውድማህም እንዲሰበስብልህ ታምነዋለህን?
13"የሰጎን ክንፎች በደስታ ይማታሉ፤ ነገር ግን የሽመላ ላባና ክንፍ ናቸውን? 14እንቍላሎቿን በመሬት ላይ ትተዋለች፤ በትቢያ ውስጥም እንዲሞቁ ታደርጋለች፤ 15እግር ሊጨፈልቃቸው እንደሚችል፣ የዱር አውሬም ሊረግጣቸው እንደሚችል ረስታ። 16ልጆቿ የራሷ እንዳልሆኑ፣ በጭካኔ ትይዛቸዋለች፤ ድካሟ ከንቱ ስለ መሆኑ ፍርሃት የላትም፤ 17ጥበብን እንድትረሳ ስላደረግኋት፣ ማስተዋልንም ስላላካፈልኋት ነው። 18ነገር ግን ለመሮጥ ስትነሣ፣ ፈረሱንና ጋላቢውን ትሥቃለች።
19"ለፈረስ ኀይልን የምትሰጠው አንተ ነህን? አንገቱንስ በተንዠረገገ ጋማ ታለብሰዋለህን? 20እንደ አንበጣ ዘልሎ እንዲሄድ ታደርገዋለህን? ኵራት የተሞላበት ማናፈሱ ያስደነግጣል። 21መሬቱን በኰቴው እየጫረ በኀይሉ ይደሰታል፤ ወደ ውጊያም ይገሠግሣል። 22ፍርሃትን ይሥቃል፣ አይደነግጥምም፤ ከሰይፍም ፊት ወደ ኋላ አያፈገፍግም። 23አፎቱ በጐኑ ያንቃጭላል፤ የሚያብለጨልጨው ጦርና ዠምቢያም እንዲሁ። 24በጽኑና በሚንቀለቀል ስሜት መሬቱን ይውጣል፤ መለከት በተነፋ ጊዜ ጸጥ ብሎ መቆም አይችልም። 25መለከት በተነፋ ጊዜ፣ ‘እሰይ!’ ይላል፤ የውጊያውንም ሽታ ከሩቅ ያሸታል፤ የአዛዦችን ነጐድጓድና የጦር ጩኸት።
26"ጭልፊት የሚበረው፣ ክንፎቹንም ወደ ደቡብ የሚዘረጋው በአንተ ማስተዋል ነውን? 27ንስር ከፍ ብሎ የሚበረው፣ ጎጆውንም በከፍታ ላይ የሚሠራው በአንተ ትእዛዝ ነውን? 28በገደል ላይ ይኖራል፤ ማደሪያውንም እዚያ ያደርጋል፤ በዓለት አቀበት ላይ፣ በጽኑ መጠጊያው። 29ከዚያ ሆኖ ምግቡን ይፈልጋል፤ ዐይኖቹም ከሩቅ ያዩታል። 30ጫጩቶቹ ደምን ይጎነጫሉ፤ የተገደሉትም ባሉበት ስፍራ ሁሉ፣ እርሱ በዚያ ይገኛል።"