የተጻፈውና የተነበበው ጥቅልል
ባሮክ ኤርምያስ እያስጻፈው የአባታችንን ቃላት ይጽፋል፤ በቤተ መቅደሱ የጾም ቀንም ያነብባቸዋል፤ ሹማምቱ ነገሩን በቁም ነገር ይዘው ሁለቱንም ሰዎች ይሸሽጓቸዋል። ኢዮአቄም ከፍም ምድጃው አጠገብ ተቀምጦ ያዳምጣል፤ ዓምዶቹን እየቈረጠ ያቃጥላቸዋል። ጥቅልሉ ከቀድሞው ረዝሞ እንደገና ይጻፋል፤ ዘሩም ዙፋኑን ያጣል።
36 1በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት፣ ይህ ቃል ከአባታችን ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፦
2“ጥቅልል ውሰድ፤ በኢዮስያስ ዘመን መጀመሪያ ከተናገርሁህ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በእስራኤል፣ በይሁዳና በሕዝቦች ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ በእርሱ ላይ ጻፍ። 3ምናልባት ይሁዳ ላመጣባቸው ያሰብሁትን መዓት ሁሉ ሰምተው እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም በደላቸውንና ኀጢአታቸውን ይቅር እላለሁ።”
4ኤርምያስም የኔርያን ልጅ ባሮክን ጠራው፤ ባሮክም፣ ኤርምያስ ከአፉ እየነገረው፣ አባታችን ለኤርምያስ የተናገረውን ቃል ሁሉ በጥቅልል ላይ ጻፈ። 5ከዚያም ኤርምያስ ባሮክን እንዲህ ብሎ አዘዘው፤ “እኔ ተከልክዬአለሁ፤ ወደ አባታችን ቤት መሄድ አልችልም። 6እኔ ከአፌ እየነገርሁህ የጻፍሃቸውን የአባታችንን ቃል ከጥቅልሉ ሄደህ አንብብ፤ በጦም ቀን በአባታችን ቤት ለሚሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ፣ ከከተሞቻቸው ለሚመጡት የይሁዳ ሰዎችም ሁሉ አንብብላቸው። 7ምናልባት ምሕረት ለማግኘት የሚያቀርቡት ልመና ወደ አባታችን ይደርስ ይሆናል፤ እያንዳንዱም ከክፉ መንገዱ ይመለስ ይሆናል፤ አባታችን በዚህ ሕዝብ ላይ ታላቅ ቍጣ ተናግሮአልና።”
8የኔርያ ልጅ ባሮክም ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፤ የአባታችንን ቃል ከመጽሐፉ በአባታችን ቤት አነበበ። 9በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአምስተኛው ዓመት፣ በዘጠነኛው ወር፣ በኢየሩሳሌም የነበሩ ሁሉና ከይሁዳ ከተሞች የመጡ ሁሉ በአባታችን ፊት ጦም አወጁ። 10ባሮክም የኤርምያስን ቃል ከጥቅልሉ ሕዝቡ ሁሉ እንዲሰማ፣ በአባታችን ቤት፣ በጸሐፊው በሳፋን ልጅ በጎማርያ ክፍል፣ በላይኛው ግቢ፣ በአባታችን ቤት በአዲሱ በር መግቢያ አነበበ።
11የሳፋን ልጅ የጎማርያ ልጅ ሚክያስ የአባታችንን ቃል ሁሉ ከጥቅልሉ በሰማ ጊዜ፣ 12ወደ ንጉሡ ቤት፣ ወደ ጸሐፊው ክፍል ወረደ፤ በዚያም መኳንንቱ ሁሉ ተቀምጠው ነበር፦ ጸሐፊው ኤሊሳማ፣ የሸማያ ልጅ ደላያ፣ የዐክቦር ልጅ ኤልናታን፣ የሳፋን ልጅ ጎማርያ፣ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ፣ መኳንንቱም ሁሉ ነበሩ። 13ሚክያስም ባሮክ ለሕዝቡ ከመጽሐፉ ባነበበ ጊዜ የሰማውን ቃል ሁሉ ነገራቸው። 14ስለዚህ መኳንንቱ ሁሉ የኩሲ ልጅ የሰለምያ ልጅ የናታንያ ልጅ ይሁዲን ወደ ባሮክ ላኩ፤ “ለሕዝቡ ያነበብኸውን ጥቅልል ይዘህ ና” አሉት። የኔርያ ልጅ ባሮክም ጥቅልሉን ይዞ ወደ እነርሱ መጣ።
15እነርሱም፣ “ተቀምጠህ አንብብልን” አሉት። ባሮክም አነበበላቸው።
16ቃሉን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ እያንዳንዳቸው እየፈሩ እርስ በርሳቸው ተያዩ፤ ባሮክንም፣ “ይህን ቃል ሁሉ ለንጉሡ ልንነግረው ይገባናል” አሉት። 17ባሮክንም፣ “ይህን ቃል ሁሉ እንዴት እንደ ጻፍኸው ንገረን፤ እርሱ ከአፉ እየነገረህ ነውን?” ብለው ጠየቁት።
18ባሮክም መልሶ፣ “ይህን ቃል ሁሉ ከአፉ ነገረኝ፤ እኔም በቀለም በመጽሐፉ ጻፍሁት” አላቸው።
19ከዚያም መኳንንቱ ባሮክን፣ “አንተና ኤርምያስ ሄዳችሁ ተሰወሩ፤ ያላችሁበትን ማንም አያውቅ” አሉት።
20ጥቅልሉንም በጸሐፊው በኤሊሳማ ክፍል ትተው ወደ ንጉሡ ወደ ግቢው ገቡ፤ ነገሩንም ሁሉ ነገሩት። 21ንጉሡም ጥቅልሉን ያመጣ ዘንድ ይሁዲን ላከ፤ እርሱም ከጸሐፊው ከኤሊሳማ ክፍል አመጣው። ይሁዲም ለንጉሡና በአጠገቡ ቆመው ለነበሩት መኳንንት ሁሉ ጮኾ አነበበው። 22ንጉሡም በዘጠነኛው ወር በክረምት ቤት ተቀምጦ ነበር፤ በፊቱም በምድጃ ውስጥ እሳት ይነድ ነበር። 23ይሁዲም ሦስት ወይም አራት አምዶች ባነበበ ጊዜ፣ ንጉሡ በጸሐፊ ቢላዋ እየቈረጠ ጥቅልሉ ሁሉ እስኪቃጠል ድረስ ወደ ምድጃው ውስጥ ጣለው። 24ነገር ግን ይህን ቃል የሰሙት ንጉሡና ባሪያዎቹ ሁሉ አልፈሩም፤ ልብሳቸውንም አልቀደዱም። a a v24 ልብስ መቅደድ በእግዚአብሔር ፊት የሐዘን፣ የለቅሶ ወይም የንስሓ ባህላዊ ምልክት ነበር። 25ኤልናታን፣ ደላያና ጎማርያ ንጉሡ ጥቅልሉን እንዳያቃጥል ለመኑት፤ እርሱ ግን ሊሰማቸው እምቢ አለ። 26ንጉሡም የንጉሡን ልጅ ይራሕምኤልን፣ የዐዝርኤልን ልጅ ሠራያንና የዐብድኤልን ልጅ ሰለምያን ጸሐፊው ባሮክንና ነቢዩ ኤርምያስን እንዲይዟቸው አዘዘ፤ አባታችን ግን ሰወራቸው።
27ንጉሡም ባሮክ ኤርምያስ ከአፉ እየነገረው የጻፈውን ቃል የያዘውን ጥቅልል ካቃጠለ በኋላ፣ የአባታችን ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦
28“ሌላ ጥቅልል ውሰድ፤ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው በመጀመሪያው ጥቅልል የነበረውን ቃል ሁሉ በእርሱ ላይ ጻፍ። 29ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ በል፤ አባታችን እንዲህ ይላል፦ አንተ ይህን ጥቅልል አቃጠልህ፤ ‘የባቢሎን ንጉሥ በርግጥ መጥቶ ይህችን ምድር ያጠፋል፤ ሰውንም እንስሳንም ከእርስዋ ያስወግዳል ብለህ ለምን ጻፍህ?’ ብለህም ጠየቅህ። 30ስለዚህ አባታችን ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፦ ከእርሱ ወገን በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ አይኖርም፤ በድኑም ለቀን ትኵሳትና ለሌሊት ቍር ወደ ውጭ ይጣላል። 31እርሱንም፣ ዘሩንም፣ ባሪያዎቹንም ስለ ኀጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ፤ በእነርሱ ላይ፣ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና በይሁዳ ሰዎች ላይ የተናገርሁትን መዓት ሁሉ አመጣባቸዋለሁ፤ እነርሱ ግን አልሰሙም።”
32ኤርምያስም ሌላ ጥቅልል ወስዶ ለጸሐፊው ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠው፤ እርሱም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ያቃጠለውን የጥቅልሉን ቃል ሁሉ ኤርምያስ ከአፉ እየነገረው ጻፈ፤ ከእነዚያም ጋር የሚመሳሰል ብዙ ቃል ተጨመረባቸው።