አርኤል፣ የዳዊት ከተማ
ኢየሩሳሌም ድምፅዋ ከአፈር እስኪያንሾካሹክ ድረስ ትከበባለች፤ ከዚያም አጥቂዎቿ ሰውን ተርቦ እንደሚተው የምግብ ሕልም ይጠፋሉ። ልባቸው ሩቅ ሆኖ ሳለ አብን በከንፈሮቻቸው ያከብራሉ፤ ስለዚህ ጥበባቸው ትጠፋለች። ሆኖም ደንቆሮች ይሰማሉ።
29 1ወዮ ለአርኤል፣ አርኤል፣ ዳዊት ሰፍሮባት የነበረ ከተማ! ዓመትን በዓመት ላይ ጨምሩ፤ በዓላትም እየተመላለሱ ይምጡ። 2ነገር ግን አርኤልን አስጨንቃታለሁ፣ ልቅሶና ዋይታም ይሆናል፤ ለእኔም እንደ መሠዊያ እቶን ትሆናለች። 3በዙሪያሽ ሁሉ እሰፍርብሻለሁ፤ በቅጥር እከብሻለሁ፣ በአንቺም ላይ የመክበቢያ ዕርከን አነሣለሁ። 4ትዋረጃለሽ፤ ከምድር ትናገራለሽ፣ ቃልሽም ከትቢያ ውስጥ ይደበዝዛል። ድምፅሽ እንደ መናፍስት ከምድር ይወጣል፣ ንግግርሽም ከትቢያ ውስጥ ያሾካሹካል። 5ነገር ግን የጠላቶችሽ ብዛት እንደ ረቂቅ ትቢያ፣ የጨካኞችም ብዛት እንደሚበን ገለባ ይሆናል። ይህም በቅጽበት፣ በድንገት ይሆናል። 6የሰማይ ሠራዊት አባት በነጎድጓድ፣ በመሬት መንቀጥቀጥና በታላቅ ጩኸት፣ በዐውሎ ነፋስ፣ በማዕበልና በሚባላ እሳት ነበልባል ይጐበኝሻል። 7በአርኤል ላይ የሚዋጉ፣ በእርሷና በምሽጓ ላይ የሚፋለሙ፣ የሚያስጨንቋትም ሁሉ፣ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደ ሕልም፣ እንደ ሌሊት ራእይ ይሆናሉ። 8የተራበ ሰው የሚበላ መስሎት እንደሚያልም፣ ሲነቃ ግን ርቦት እንደሚገኝ ነው፤ ወይም የተጠማ ሰው የሚጠጣ መስሎት እንደሚያልም፣ ሲነቃም ደክሞ ጥሙ ሳይረካ እንደሚቀር ነው። በጽዮን ተራራ ላይ የሚዋጉ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንዲሁ ይሆናል። 9ተገረሙ፣ ተደነቁም፤ ራሳችሁን አሳውሩ፣ ዕውሮችም ሁኑ! ሰክረዋል፣ ነገር ግን ከወይን ጠጅ አይደለም፤ ይንገዳገዳሉ፣ ነገር ግን ከብርቱ መጠጥ አይደለም። 10አባታችን የከባድ እንቅልፍ መንፈስን በእናንተ ላይ አፍስሶባችኋልና፤ ዓይኖቻችሁን፣ ነቢያቱን፣ ጨፍኗል፤ ራሶቻችሁንም፣ ባለ ራእዮቹን፣ ሸፍኗል። 11ራእዩ ሁሉ ለእናንተ የታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል። ማንበብ ለሚችል ሰው ሰጥተው፣ “ይህን እባክህ አንብብ” ባሉት ጊዜ፣ “አልችልም፣ ታትሟልና” ይላል። 12መጽሐፉም ማንበብ ለማይችል ሰው ተሰጥቶ፣ “ይህን አንብብ” ባሉት ጊዜ፣ “ማንበብ አልችልም” ይላል።
13ጌታ አባት እንዲህ አለ፤ “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፣ በከንፈሩም ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፤ ለእኔ የሚያሳዩት ፍርሃት በሰዎች የታዘዘ ሥርዐት ነው፤ 14ስለዚህ እነሆ፣ በዚህ ሕዝብ ላይ እንደ ገና ድንቅ ነገር አደርጋለሁ፣ ድንቅ በድንቅ ላይ፤ የጥበበኞቻቸው ጥበብ ይጠፋል፣ የአስተዋዮቻቸውም ማስተዋል ይከስማል።” 15ዕቅዳቸውን ከአባታችን ለመሰወር ጠልቀው ለሚሄዱ፣ ሥራቸውንም በጨለማ ለሚያደርጉ፣ “ማን ያየናል? ማንስ ያውቀናል?” ለሚሉ ወዮላቸው።
16ነገሩን ሁሉ እንዴት ትገለብጣላችሁ! ሸክላ ሠሪ እንደ ጭቃው ይቈጠር ይሆን? የተሠራው ነገር ሠሪውን፣ “አልሠራኝም” ይለው ይሆን? ወይስ የተቀረጸው ነገር ቀራጩን፣ “ምንም አያውቅም” ይለው ይሆን?
17ሊባኖስ ለም መሬት የሚሆንበት፣ ለም መሬቱም እንደ ጫካ የሚቈጠርበት፣ ገና ጥቂት ጊዜ ብቻ አይደለምን? 18በዚያ ቀን ደንቆሮዎች የመጽሐፉን ቃል ይሰማሉ፤ ከጭጋግና ከጨለማ ውስጥ የዕውሮች ዓይኖች ያያሉ። 19ትሑታን በአባታችን እንደ ገና ደስ ይላቸዋል፤ ከሰዎችም መካከል ድኆች በእስራኤል ቅዱስ፣ በአባታችን ሐሤት ያደርጋሉ። 20ጨካኝ ይጠፋልና፣ ፌዘኛም ይደመሰሳል፤ ክፋትን ለማድረግ የሚተጉ ሁሉ ይቈረጣሉ፤ 21እነርሱም በቃል ሰውን ኀጢአተኛ የሚያስመስሉ፣ በበር ላይ ፍትሕን ለሚያስከብር ወጥመድ የሚዘረጉ፣ ጻድቁንም በከንቱ ክርክር የሚያርቁ ናቸው። a a v21 የከተማዪቱ በር የፍርድ ክርክር የሚሰማበትና ፍርድ የሚሰጥበት የጥንቱ ፍርድ ቤት ነበር።
22ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠው አባታችን ስለ ያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፤ “ያዕቆብ ከእንግዲህ አያፍርም፣ ከእንግዲህም ፊቱ አይገረጣም። 23ልጆቹን፣ በመካከላቸው ያለውን የእጆቼን ሥራ ባየ ጊዜ፣ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብንም ቅዱስ ይቀድሳሉ፣ አባታችንንም ይፈራሉ። b b v23 አባታችን ልጆቹን — በገዛ እጆቹ የተሠሩትን — ባየ ጊዜ፣ ስሙ ይከብራል። የሠራቸው ልጆች ወደ እርሱ ሲመለሱ፣ ዳግም መቋቋም ይጀምራል። 24በመንፈስ የሚስቱ ማስተዋልን ያገኛሉ፤ የሚያጕረመርሙም ተግሣጽን ይቀበላሉ።”