ከእነዚህ ሁሉ የሚበልጠው
የሚፎካከሩበት ስጦታ ሁሉ፣ ልሳኖች፣ ትንቢት፣ እውቀት፣ ተራራን የሚያፈልስ እምነት፣ ያለውን ሁሉ መስጠት እንኳ ቢሆን፣ ፍቅር ከሌለ ምንም አይጠቅምም። ፍቅር ይታገሣል፣ በደልን አይቈጥርም፤ ፊት ለፊት ስናይ ከሚያልፉት ስጦታዎችም ይዘልቃል።
13 1በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ፣ የሚያስተጋባ ናስ ወይም ዠንዠን የሚል ጸናጽል ሆኜአለሁ። 2ትንቢት ብናገር፣ ምስጢርን ሁሉና ዕውቀትን ሁሉ ብረዳ፣ ተራሮችን እስከ ማፍለስ የሚያደርስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። 3ያለኝን ሁሉ ባካፍል፣ ለመመካትም ሰውነቴን አሳልፌ ብሰጥ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አልጠቀምም።
4ፍቅር ይታገሣል፣ ፍቅር ቸር ነው። አይቀናም፣ አይመካም፣ አይታበይም። 5የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱን አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቈጥርም። 6ፍቅር በዐመፅ ደስ አይለውም፣ ከእውነት ጋራ ግን ደስ ይለዋል። 7ሁሉን ይከልላል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ይታገሣል።
8ፍቅር ከቶ አያልፍም። ትንቢት ግን ያልፋል፣ ልሳኖች ይቀራሉ፣ ዕውቀትም ያልፋል። 9ዕውቀታችን ከፊል ነውና፣ ትንቢታችንም ከፊል ነውና፣ 10ፍጹም የሆነው ሲመጣ ግን፣ ከፊል የሆነው ይጠፋል። 11ሕፃን ሳለሁ እንደ ሕፃን እናገር ነበር፣ እንደ ሕፃን አስብ ነበር፣ እንደ ሕፃንም እመራመር ነበር። ጐልማሳ በሆንሁ ጊዜ ግን የሕፃንነትን ነገር ተውሁ። 12አሁን በመስተዋት የደበዘዘ ምስል እናያለንና፣ በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን። አሁን ከፊሉን አውቃለሁ፣ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ፍጹም እንደ ታወቅሁ ሁሉ ፍጹም አውቃለሁ። 13አሁንም እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር። ከእነዚህ ግን የሚበልጠው ፍቅር ነው።