ያንብቡ። ይቀበሉ። ይጠቁሙ።

♥ አስተያየቶች

1 ቆሮንቶስ 14

መጽሐፍ

ቤተ ሰብን የሚያንጹ ስጦታዎች

ያልተተረጎመ ልሳን የሚያንጸው ተናጋሪውን ብቻ ነው፤ ስለዚህ ትንቢት ይሻላል። ከውጭ የገባ ሰው የልቡ ሐሳብ ተገልጦ ወድቆ ሊሰግድ ይገባዋል። በጉባኤ ያለው ሁሉ የሚመዘነው ያንጻል ወይ በሚለው ነው፤ በሥርዓትም ይደረግ፤ አብ ሥርዓተ አልበኛ አይደለምና።

ምዕራፍ 14።

ፍቅርን ተከታተሉ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችንም በብርቱ ፈልጉ፤ ይልቁንም ትንቢት መናገርን። በልሳን የሚናገር ለሰዎች ሳይሆን ለአባታችን ይናገራል፤ ማንም አይረዳውም፤ በመንፈስ ምሥጢርን ይናገራል። ትንቢት የሚናገር ግን ለሰዎች ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት ይናገራል። በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢት የሚናገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል። ሁላችሁም በልሳን እንድትናገሩ እወዳለሁ፤ ነገር ግን ይልቁን ትንቢት እንድትናገሩ እወዳለሁ። ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ ትርጓሜውን ካልተረጐመ በቀር፣ ትንቢት የሚናገር በልሳን ከሚናገር ይበልጣል።

አሁንም፣ ወንድሞችና እኅቶች ሆይ፣ በልሳን እየተናገርሁ ወደ እናንተ ብመጣ፣ መገለጥን ወይም ዕውቀትን ወይም ትንቢትን ወይም ትምህርትን ካልተናገርሁ በቀር፣ ምን እጠቅማችኋለሁ? ድምፅ የሚያሰሙ ሕይወት የሌላቸው ነገሮች እንኳ፣ ዋሽንት ቢሆኑ ወይም በገና፣ ድምፆቻቸው ተለይተው ባይታወቁ፣ የሚደረደረው ምን እንደ ሆነ እንዴት ይታወቃል? መለከቱም ግልጽ ያልሆነ ድምፅ ቢያሰማ፣ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? እናንተም እንዲሁ፣ ምላሳችሁ ግልጽ ቃል ካልተናገረ በቀር፣ የተነገረው ነገር እንዴት ይታወቃል? ለአየር ብቻ የምትናገሩ ትሆናላችሁና። በዓለም ውስጥ ብዙ ዐይነት ቋንቋዎች እንዳሉ ጥርጥር የለውም፤ ከእነርሱም አንዱ እንኳ ትርጒም የሌለው የለም። እንግዲህ የድምፁን ትርጒም ባላውቅ፣ ለተናጋሪው ባዕድ እሆናለሁ፤ ተናጋሪውም ለእኔ ባዕድ ይሆናል። እናንተም እንዲሁ፣ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለማግኘት ስለምትቃጠሉ፣ ቤተ ክርስቲያንን በማነጽ ልቃችሁ ለመገኘት ፈልጉ። ስለዚህ በልሳን የሚናገር ሊተረጕመው እንዲችል ይጸልይ። በልሳን ብጸልይ፣ መንፈሴ ይጸልያል፤ አእምሮዬ ግን ፍሬ አልባ ነው።

እንግዲህ ምን ላድርግ? በመንፈሴ እጸልያለሁ፤ በአእምሮዬም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈሴ እዘምራለሁ፤ በአእምሮዬም ደግሞ እዘምራለሁ። ያለዚያ በመንፈስ ብትባርክ፣ የምትናገረውን ስለማያውቅ፣ በዚያ የተቀመጠው ባዕድ ሰው ለምስጋናህ እንዴት “አሜን” ይላል? አንተ መልካም ምስጋና ታቀርብ ይሆናል፤ ሌላው ሰው ግን አይታነጽም። ከሁላችሁ ይልቅ በልሳን ስለምናገር አባታችንን አመሰግናለሁ። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በልሳን ዐሥር ሺሕ ቃላት ከመናገር ይልቅ፣ ሌሎችን ደግሞ ለማስተማር በአእምሮዬ አምስት ቃላት መናገር ይሻለኛል።

ወንድሞችና እኅቶች ሆይ፣ እንደ ሕፃናት አታስቡ። በክፋት ሕፃናት ሁኑ፤ በአስተሳሰብ ግን የበሰላችሁ ሁኑ።

ሕጉ እንዲህ ይላል፦ “በእንግዳ ልሳኖችና በባዕድ ከንፈሮች ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ ያን ጊዜም እንኳ አያዳምጡኝም” ይላል አባታችን።

እንግዲህ ልሳኖች ለማያምኑ እንጂ ለሚያምኑ ምልክት አይደሉም፤ ትንቢት ግን ለማያምኑ ሳይሆን ለሚያምኑ ምልክት ነው። እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ በአንድ ላይ ተሰብስቦ ሁሉም በልሳን ቢናገሩ፣ ባዕዳንም ወይም የማያምኑ ቢገቡ፣ ዐብዳችኋል አይሉምን? ሁሉም ትንቢት ቢናገሩ ግን፣ የማያምን ወይም ባዕድ ሰው ቢገባ፣ በሁሉ ይወቀሳል፤ በሁሉም ይመረመራል፤ የልቡ ምሥጢር ይገለጣል፤ ስለዚህ በፊቱ ተደፍቶ ለአባታችን ይሰግዳል፤ አባታችን በእውነት በመካከላችሁ እንዳለ ይመሰክራል።

በተገቢ ሥርዐት የሚደረግ አምልኮ

እንግዲህ ወንድሞችና እኅቶች ሆይ፣ ምን ይደረግ? በምትሰበሰቡ ጊዜ፣ እያንዳንዱ መዝሙር ወይም ትምህርት ወይም መገለጥ ወይም ልሳን ወይም ትርጓሜ አለው። ሁሉም ነገር ለማነጽ ይሁን። ማንም በልሳን ቢናገር፣ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት፣ በተራ ይናገሩ፤ አንዱም ይተርጕም። ተርጓሚ ከሌለ ግን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዝም ይበል፤ ለራሱና ለአባታችን ብቻ ይናገር። ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ይናገሩ፤ ሌሎቹም የተነገረውን አስተውለው ይመርምሩ። በዚያ ተቀምጦ ለነበረ ለሌላ ሰው መገለጥ ቢመጣለት፣ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። ሁሉም እንዲማርና ሁሉም እንዲበረታታ፣ አንድ በአንድ ሁላችሁም ትንቢት መናገር ትችላላችሁና፤ የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ። አባታችን የሁከት ሳይሆን የሰላም አምላክ ነውና፤ በቅዱሳን ቤተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደ ሆነ። ሴቶች በቤተ ክርስቲያናት ውስጥ ዝም ይበሉ፤ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም፤ ነገር ግን ሕጉ ደግሞ እንደሚል፣ ሊገዙ ይገባቸዋል። a a v34 አንዳንዶቹ ቅጂዎች ቍጥር 34-35ን ከቍጥር 40 በኋላ ያስቀምጣሉ። አንዳች ነገር መማር ቢፈልጉ፣ በቤታቸው የራሳቸውን ባሎች ይጠይቁ፤ ሴት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መናገር ነውር ነውና። ወይስ የአባታችን ቃል የተጀመረው ከእናንተ ነውን? ወይስ ለእናንተ ብቻ ደረሰን? ራሱን ነቢይ ወይም መንፈሳዊ አድርጎ የሚቈጥር ማንም ሰው፣ የምጽፍላችሁ የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ። ማንም ይህን ቸል ቢል ግን፣ እርሱ ራሱ ቸል ይባላል።

እንግዲህ ወንድሞቼና እኅቶቼ ሆይ፣ ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ፤ በልሳን መናገርንም አትከልክሉ። ነገር ግን ሁሉም ነገር በተገቢና በሥርዐት ይሁን።

A young man reading the Father's Heart Bible (FHB) print edition in a coffee shop አሁን በኅትመት ይገኛል

አስተያየቶች

ሐሳብ፣ ጥያቄ፣ ወይም ይህ ምዕራፍ በልብዎ ያነሣሣው ቃል — እዚህ ያካፍሉ። እያንዳንዱ አስተያየት ስምዎን በአስተዋጽኦ አበርካቾች ግድግዳ ላይ ያሰፍራል።

ማንበብ፣ ማዳመጥ፣ መቅዳትና ማጋራት ለሁሉም ክፍት ነው — መለያ አያስፈልግም። አስተያየት መስጠት፣ ቁጥሮችን ማድመቅና የደረሱበትን ቦታ ምልክት ማድረግ ከነጻ መለያ ጋራ ይመጣሉ፤ እያንዳንዱ አስተያየትም ስምዎን በአስተዋጽኦ አበርካቾች ግድግዳ ላይ ያሰፍራል።

ቤተሰቡን ይቀላቀሉ — በነጻ ነው →
  • እስካሁን ምንም አስተያየት የለም። ድምፅዎን በማሰማት የመጀመሪያው ይሁኑ።