በፈሪሳዊው ማዕድ ላይ የተፈወሰ
በአንድ ፈሪሳዊ ማዕድ ላይ ሁሉም ዝም ብለው ሳሉ በሽታ ያሳበጠውን ሰው ይፈውሳል፤ ከዚያም እንግዶችን የመጨረሻውን ስፍራ እንዲይዙ፣ ጋባዦችንም ብድር መመለስ የማይችሉትን እንዲጠሩ ይነግራቸዋል። በአብ ግብዣ የተጠሩት ምክንያት ያቀርባሉ፤ ከመንገድ ያሉትም ይገባሉ። እርሱን መከተል ሁሉን ያስከፍላል።
14 1በአንድ ሰንበት ቀን ከፈሪሳውያን መሪዎች ወደ አንዱ ቤት ምግብ ሊበላ በገባ ጊዜ፣ አጥብቀው ይከታተሉት ነበር። 2በፊቱም ሰውነቱ በፈሳሽ ያበጠ አንድ ሰው ነበረ።
3ኢየሱስም ሕግ አዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን፣ “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?” ሲል ጠየቃቸው።
4እነርሱ ግን ዝም አሉ። እርሱም ሰውዬውን ይዞ ፈወሰውና አሰናበተው።
5ከዚያም እንዲህ አላቸው፤ “ከእናንተ አንዱ ልጁ ወይም በሬው በሰንበት ቀን ጕድጓድ ውስጥ ቢወድቅ፣ ወዲያውኑ አያወጣውም?”
6ለዚህም የሚመልሱት መልስ አጡ።
7የተጋበዙትም የክብር ስፍራዎችን እንዴት እንደሚመርጡ ባስተዋለ ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤
8“አንድ ሰው ወደ ሰርግ ግብዣ በጠራህ ጊዜ፣ የክብር ስፍራ አትያዝ፤ ምናልባት ካንተ የተከበረ እንግዳ ተጠርቶ ይሆናልና። 9ያን ጊዜ ሁለታችሁንም የጠራው መጥቶ፣ ‘ስፍራህን ለዚህ ሰው ልቀቅ’ ይልሃል፤ አንተም በኀፍረት ዝቅተኛውን ስፍራ ትይዛለህ። 10አንተ ግን በተጠራህ ጊዜ፣ ሄደህ ዝቅተኛውን ስፍራ ያዝ፤ የጠራህ ሰው በመጣ ጊዜ፣ ‘ወዳጄ፣ ወደ ላይ ውጣ’ እንዲልህ። ከዚያም ከአንተ ጋራ በማዕድ ተቀምጠው ባሉት ሁሉ ፊት ክብርን ታገኛለህ። 11ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋልና፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይደረጋል።”
12ከዚያም የጠራውን ሰው እንዲህ አለው፤ “ምሳ ወይም እራት ባዘጋጀህ ጊዜ፣ ወዳጆችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ባለጠጎች ጎረቤቶችህን አትጥራ፤ ይህን ብታደርግ ምናልባት እነርሱ ደግመው ይጠሩሃል፤ ብድራትም ይመለስልሃል። 13አንተ ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ፣ ድኾችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ አንካሶችን፣ ዕውሮችን ጥራ፤ 14ትባረካለህም። ብድራት የሚመልሱልህ ስለሌላቸው፣ በጻድቃን ትንሣኤ ብድራትህ ይከፈልሃል።”
የአብ ግብዣ
15ከእርሱ ጋራ በማዕድ ተቀምጠው ከነበሩት አንዱ ይህን በሰማ ጊዜ፣ “በአባታችን መንግሥት ግብዣ የሚበላ ብፁዕ ነው!” አለው።
16ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አንድ ሰው ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ ብዙ ሰዎችንም ጠራ።
17የግብዣውም ሰዓት በደረሰ ጊዜ፣ ‘ኑ፤ አሁን ሁሉ ተዘጋጅቷል’ ብሎ ለተጠሩት እንዲነግራቸው አገልጋዩን ላከ። 18ሁሉም ግን አንድ በአንድ ይሳበቡ ጀመር። የመጀመሪያው፣ ‘እርሻ ገዝቻለሁ፤ ሄጄ ማየት አለብኝ፤ እባክህ ይቅር በለኝ’ አለው።
19ሌላውም፣ ‘አምስት ጥምድ በሬዎች ገዝቻለሁ፤ ልፈትናቸውም እየሄድኩ ነው፤ እባክህ ይቅር በለኝ’ አለ።
20ሌላውም፣ ‘አሁን ሚስት አግብቻለሁ፤ ስለዚህ ልመጣ አልችልም’ አለ።
21አገልጋዩም ተመልሶ ይህን ለጌታው ነገረው። የቤቱም ጌታ ተቈጥቶ አገልጋዩን፣ ‘ፈጥነህ ወደ ከተማዪቱ አደባባዮችና ጎዳናዎች ውጣ፤ ድኾችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ዕውሮችንና አንካሶችን አግባ’ አለው።
22አገልጋዩም፣ ‘ጌታዬ፣ ያዘዝከው ተፈጽሟል፤ ነገር ግን እስከ አሁን ስፍራ አለ’ አለ።
23ጌታውም አገልጋዩን እንዲህ አለው፤ ‘ቤቴ እንዲሞላ፣ ወደ መንገዶችና ወደ አገር ዳር ጎዳናዎች ውጣ፤ እንዲገቡም አስገድዳቸው። 24እላችኋለሁና፣ ከተጠሩት ሰዎች አንዱ እንኳ ከግብዣዬ አይቀምስም።’ ”
ኢየሱስን የመከተል ዋጋ
25ብዙ ሕዝብም ከእርሱ ጋራ ይጓዝ ነበር፤ ወደ እነርሱም ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፤
26“ማንም ወደ እኔ የሚመጣ አባቱንና እናቱን፣ ሚስቱንና ልጆቹን፣ ወንድሞቹንና እኅቶቹን፣ አዎን፣ ሕይወቱን እንኳ ሳይቀር ካልጠላ፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። a a v26 እዚህ ላይ “መጥላት” በንጽጽር እጅግ ያነሰ መውደድ ማለት የሆነ የዕብራይስጥ አነጋገር ነው፤ ኢየሱስ በቤተ ሰብ ላይ ጥላቻን እያዘዘ አይደለም፤ ነገር ግን ከሌላው ታማኝነት ሁሉ የሚልቅ ለእርሱ ያለ ፍቅርን ነው። 27መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ ሁሉ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። 28ከእናንተ አንዱ ግንብ ሊሠራ ቢፈልግ፣ ለመጨረስ የሚበቃ እንዳለው ለማየት አስቀድሞ ተቀምጦ ወጪውን አያሰላም? 29አለበለዚያ መሠረቱን ጥሎ መጨረስ ባይችል፣ የሚያየው ሁሉ ሊዘባበትበት ይጀምራል፤ 30‘ይህ ሰው መሥራት ጀመረ፤ መጨረስ ግን አልቻለም’ እያሉ። 31ወይም አንድ ንጉሥ ከሌላ ንጉሥ ጋራ ሊዋጋ ቢዘጋጅ፣ በሃያ ሺ ሰዎች የሚመጣበትን በዐሥር ሺ ሊገጥመው የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ አያስብም? 32ባይችልም፣ ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልእክተኞችን ልኮ የሰላም ውል ይለምናል። 33እንዲሁም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ማንም ቢሆን ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
34“ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨዋማነቱ ቢጠፋ፣ እንደ ገና በምን ይጣፍጣል? 35ለዐፈርም ሆነ ለፋግ ክምር አይበጅም፤ ወደ ውጭም ይጣላል። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”