አንበጣ በአድማስ ላይ
አብ በረዶው የተረፈውን ሁሉ የሚበሉ አንበጦችን ይልካል፤ አንዳች ለምለም ነገር አይቀርም፤ የፈርዖን ሹማምንት ግብፅ መጥፋቷን አያይምን ብለው ይጠይቁታል። ከዚያም የሚዳሰስ ድቅድቅ ጨለማ ግብፅን ሦስት ቀን ይይዛል፤ እስራኤል ግን ብርሃን አላቸው። ድርድሩም ፈርዖን የሙሴን ሕይወት በማስፈራራት ያበቃል።
10 1አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ፈርዖን ሂድ፤ ምልክቶቼን በመካከላቸው ለማሳየት የእርሱንና የባሪያዎቹን ልብ አደንድኛለሁና። 2ግብፃውያንን እንዴት እንደ ተሣለቅሁባቸው፣ ምልክቶቼንም በመካከላቸው እንዳደረግሁ ለልጅህና ለልጅ ልጅህ ንገር፤ እኔ አባታችሁ እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ።”
3ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገብተው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አባት እንዲህ ይላል፤ ‘እስከ መቼ በፊቴ ራስህን ከማዋረድ እምቢ ትላለህ? ሊያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ።’ 4ሕዝቤን ለመልቀቅ እምቢ ብትል፣ እነሆ ነገ በግዛትህ ላይ አንበጣ አመጣለሁ። 5የምድሩንም ፊት ይሸፍናሉ፤ መሬቱም እንዳይታይ ያደርጋሉ፤ ከበረዶ የተረፈላችሁን ይበላሉ፤ በሜዳ ለእናንተ የሚበቅለውንም ዛፍ ሁሉ ይበላሉ። 6ቤቶችህን፣ የባሪያዎችህንም ቤቶች፣ የግብፃውያንን ሁሉ ቤቶች ይሞላሉ፤ ይህም አባቶችህና የአባቶችህ አባቶች በምድር ላይ ከኖሩበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያላዩት ነው።” ከዚያም ዞሮ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።
7የፈርዖንም ሹማምት እንዲህ አሉት፤ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ሆኖብን ይኖራል? ሕዝቡ አምላካቸውን ሊያገለግሉ ይሂዱ፤ ግብፅ መጥፋቷን ገና አላወቅህምን?”
8ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ተመለሱ፤ እርሱም “ሂዱ፤ እግዚአብሔርን አገልግሉ” አላቸው። “ነገር ግን የሚሄዱት እነማን ናቸው?”
9ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ከወጣቶቻችንና ከሽማግሌዎቻችን ጋር እንሄዳለን፤ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆቻችን፣ ከበጎቻችንና ከከብቶቻችን ጋር እንሄዳለን፤ ለአባታችን በዓል አለብንና።”
10እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ እናንተንና ሕፃናቶቻችሁን የምለቅ መስሎአችኋልን! እነሆ፣ ክፉ ነገር በልባችሁ አላችሁ። 11አይሆንም! የምትፈልጉት ይህ ስለ ሆነ እናንተ ወንዶች ሄዳችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ።” ፈርዖንም ከፊቱ አባረራቸው።
12አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አንበጣ በግብፅ ላይ ይወጣ ዘንድ፣ ከበረዶውም የተረፈውን የምድሪቱን ቡቃያ ሁሉ ይበላ ዘንድ እጅህን በግብፅ ላይ ዘርጋ።”
13ሙሴም በትሩን በግብፅ ላይ ዘረጋ፤ አባታችንም ቀኑን ሙሉና ሌሊቱን ሙሉ የምሥራቅ ነፋስን በምድሪቱ ላይ አመጣ፤ በነጋም ጊዜ ነፋሱ አንበጣውን ይዞ መጣ። 14አንበጣውም በግብፅ ሁሉ ላይ ወጣ፤ በግዛቷም ሁሉ ላይ ሰፈረ፤ እጅግ ብዙ ነበር፤ እንደዚህ ያለ አስቀድሞ ሆኖ አያውቅም፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አይሆንም። 15የምድሪቱንም ፊት ሁሉ ሸፈኑ፤ አጨለሟትም፤ የምድሪቱንም ቡቃያ ሁሉ፣ ከበረዶውም የተረፈውን የዛፍ ፍሬ ሁሉ በሉ፤ በግብፅም ምድር ሁሉ በዛፍም ሆነ በሜዳ ቡቃያ ላይ አንዳች አረንጓዴ አልቀረም። 16ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ፈጥኖ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “በአምላካችሁና በእናንተ ላይ ኀጢአት ሠርቻለሁ። 17እባካችሁ፣ አሁን ይህን ጊዜ ብቻ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝ፤ ይህን ሞት ብቻ ከእኔ ያርቅ ዘንድ አምላካችሁን ለምኑ።”
18ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወጥቶ አባታችንን ለመነ። 19አባታችንም ነፋሱን እጅግ ኀይለኛ ወደ ሆነ የምዕራብ ነፋስ መለሰው፤ ነፋሱም አንበጣውን አንሥቶ ወደ ቀይ ባሕር ጣለው፤ በግብፅም ግዛት ሁሉ አንዲት አንበጣ እንኳ አልቀረችም። 20አባታችን ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ የእስራኤልንም ልጆች አልለቀቀም።
ሦስት ቀናት ጨለማ
21አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ጨለማ በግብፅ ምድር ላይ ይሆን ዘንድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፤ ጨለማውም ሊዳሰስ የሚችል ድቅድቅ ይሁን።”
22ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ ድቅድቅ ጨለማም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሦስት ቀን ሆነ። 23ለሦስት ቀን ማንም ሌላውን ሊያይ አልቻለም፤ ማንም ከስፍራው አልተነሣም፤ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ግን በመኖሪያቸው ብርሃን ነበራቸው።
24ፈርዖንም ሙሴን ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ሂዱ፤ አምላካችሁን አገልግሉ፤ ሕፃናቶቻችሁም እንኳ ይሂዱ፤ በጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ብቻ ተዉ።”
25ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ለአባታችን የምናቀርበውን መሥዋዕትና የሚቃጠል መባም ደግሞ ልትሰጠን ይገባል። 26እንስሶቻችንም ከእኛ ጋር መሄድ አለባቸው፤ አንዲት ኰቴ እንኳ አትቀርም፤ አባታችንን ለማገልገል ከእነርሱ እንወስዳለን፤ እዚያ እስክንደርስ ድረስ እርሱን ለማገልገል የሚያስፈልገንን አናውቅምና።”
27አባታችን ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ እርሱም ሊለቃቸው አልወደደም። 28ፈርዖንም እንዲህ አለው፤ “ከእኔ ተለይ! ተጠንቀቅ፤ ዳግመኛ ፊቴን እንዳታይ፤ ፊቴን ባየህ ቀን ትሞታለህና።”
29ሙሴም እንዲህ አለ፤ “በትክክል ተናግረሃል፤ ዳግመኛ ፊትህን ከቶ አላይም።”