በሰንበት የተመለሰ ሕይወት
ኢየሱስ በሰንበት የሰለለች እጅ ይፈውሳል፤ ፈሪሳውያንም ሊገድሉት ይማከሩ ጀመር። አሥራ ሁለቱን ይሾማል። ጸሐፍት ጋኔን አለበት ይላሉ፤ የገዛ ቤተሰቡም አእምሮውን ስቷል ይላሉ፤ እርሱም የአብ አባታችንን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ቤተሰቤ ነው ብሎ ይመልሳል።
3 1ኢየሱስ እንደገና ወደ ምኵራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለ ሰው ነበረ። 2ኢየሱስን ይከሱት ዘንድ፣ በሰንበት ሰውየውን ይፈውሰው እንደሆነ በጥንቃቄ ይከታተሉት ነበር።
3ኢየሱስም እጁ የሰለለውን ሰው፣ “ተነሥተህ ወደ መካከል ና” አለው። 4ከዚያም፣ “በሰንበት መልካም ማድረግ ተፈቅዷል ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱ ግን ዝም አሉ። 5በልባቸው መደንደን አዝኖ በቍጣ ዙሪያውን ተመለከታቸው፤ ሰውየውንም፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም ዘረጋ፤ እጁም ዳነ።
6ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያውኑ እንዴት እንደሚያጠፉት ከሄሮድሳውያን ጋራ መማከር ጀመሩ።
ሕዝቡ ፈዋሹን ይከተላል
7ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ባሕር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላም ታላቅ ሕዝብ ተከተለው፤ ከይሁዳም፣ 8ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስ፣ ከዮርዳኖስ ማዶ፣ ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢም ያደረገውን ሁሉ ሰምተው ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ መጡ። 9ስለ ሕዝቡ ብዛት እንዳያጨናንቁት ትንሽ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። 10ብዙዎችን ፈውሶ ነበርና በሽታ ያለባቸው ሁሉ ሊነኩት ይገፋፉ ነበር። 11ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ ሁሉ በፊቱ ወድቀው፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉ ይጮኹ ነበር። 12እርሱ ግን እንዳይገልጡት አጥብቆ አስጠነቀቃቸው።
ዐሥራ ሁለቱ ተሾሙ
13ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጥቶ የወደዳቸውን ጠራ፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ። 14ከእርሱ ጋራ እንዲሆኑ፣ ሊሰብኩም ሊልካቸው ዐሥራ ሁለቱን ሾመ፤ ሐዋርያትም ብሎ ሰየማቸው፤ 15አጋንንትንም ለማውጣት ሥልጣን እንዲኖራቸው። 16የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤ ጴጥሮስ ብሎ ስም የሰጠው ስምዖን፤ 17የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብ፣ ወንድሙም ዮሐንስ፤ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፤ 18እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ቀናተኛው ስምዖን፣ 19አሳልፎም የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።
የማይወድቅ መንግሥት
20ወደ ቤትም ገባ፤ ሕዝቡ እንደገና ስለ ተሰበሰበ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ እንኳ ሊበሉ አልቻሉም። 21ቤተ ዘመዶቹም ይህን ሰምተው፣ “አእምሮውን ስቷል” ይሉ ነበርና ሊይዙት ወጡ። 22ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጸሐፍትም፣ “ብዔል ዜቡል አለበት” አሉ፤ ደግሞም፣ “አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ።
23ኢየሱስም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን ሰይጣንን እንዴት ሊያወጣ ይችላል? 24አንድ መንግሥት እርስ በርሱ ከተከፋፈለ ያ መንግሥት ሊቆም አይችልም። 25አንድ ቤትም እርስ በርሱ ከተከፋፈለ ያ ቤት ሊቆም አይችልም። 26ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተከፋፈለ ሊቆም አይችልም፤ ፍጻሜው ደርሷል። 27ማንም ኀይለኛውን አስቀድሞ ሳያስር ወደ ኀይለኛው ሰው ቤት ገብቶ ንብረቱን ሊወስድ አይችልም፤ ከዚያም ቤቱን ይበዘብዛል።
28እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጆች የሚናገሩት ሁሉ፣ ኀጢአታቸውም ሆነ በእግዚአብሔር ላይ የሚሳደቡት ስድብ ሁሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ 29መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ግን ከቶ ይቅርታ የለውም፤ የዘላለም ኀጢአት ዕዳ አለበት።”
30ይህን ያለው፣ “ርኩስ መንፈስ አለበት” ይሉ ነበርና።
የአባታችን ቤተሰብ
31እናቱና ወንድሞቹም መጡ፤ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። 32በዙሪያውም የተቀመጠው ሕዝብ፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ በውጭ ሆነው ይፈልጉሃል” አለው።
33እርሱም መልሶ፣ “እናቴና ወንድሞቼ እነማን ናቸው?” አላቸው። 34በዙሪያው ተቀምጠው የነበሩትን ተመልክቶ፣ “እነሆ፣ እናቴና ወንድሞቼ! 35የአባታችንን ፈቃድ የሚያደርግ ማንም ቢሆን፣ እርሱ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴ ነው።”