ያንብቡ። ይቀበሉ። ይጠቁሙ።

♥ አስተያየቶች

መሳፍንት 19

መጽሐፍ

በእስራኤል ንጉሥ ባልነበረበት ዘመን

ወደ አብ ቤት የሚሄድ አንድ ሌዋዊ የኰበለለችውን ቁባቱን ይመልሳል፤ የሚቀበለውም አንድ ሽማግሌ መጻተኛ ብቻ ያገኛል። የከተማው ሰዎች ቤቱን ይከብባሉ፤ ሌዋዊውም እርሷን ገፍቶ ያወጣታል። ሲነጋ በደጃፉ ተጋድማ ትገኛለች። እርሱም አሥራ ሁለት ቦታ ይቈርጣታል።

ምዕራፍ 19።

በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም። በኤፍሬም ተራራማ አገር ራቅ ባለ ክፍል የሚኖር አንድ ሌዋዊ ከይሁዳ ቤተ ልሔም ቁባት አገባ። ቁባቱም ታማኝ ባለመሆኗ ትታው በይሁዳ ቤተ ልሔም ወደ አባቷ ቤት ሄደች፤ በዚያም አራት ወር ቈየች። ባልዋም ልቧን ለማባበልና ሊመልሳት ከሎሌውና ከሁለት አህዮች ጋር ተከትሎአት ሄደ። እርሷም ወደ አባቷ ቤት አስገባችው፤ የብላቴናዪቱም አባት ባየው ጊዜ ደስ አለው። አማቱም የብላቴናዪቱ አባት እንዲቀር ግድ አለው፤ ከእርሱም ጋር ሦስት ቀን ተቀመጠ፤ በዚያም እየበሉና እየጠጡ አደሩ።

በአራተኛውም ቀን ማለዳ ተነሡ፤ እርሱም ሊሄድ ተነሣ። የብላቴናዪቱ አባት ግን አማቹን፣ “ጥቂት እንጀራ ቈርሰህ ብላ፤ ከዚያም ትሄዳለህ” አለው። ሁለቱም ተቀምጠው አብረው በሉ፤ ጠጡ። የብላቴናዪቱም አባት ሰውየውን፣ “እባክህ፣ ይህችን ሌሊት እደር፤ ልብህም ደስ ይበለው” አለው። ሰውየውም ሊሄድ ተነሣ፤ አማቹ ግን አጥብቆ ለመነው፤ ስለዚህ እንደ ገና በዚያ አደረ። በአምስተኛውም ቀን ሊሄድ ማልዶ ተነሣ፤ የብላቴናዪቱም አባት፣ “እባክህ፣ ራስህን አበርታ፤ እስከ ቀትር ድረስም ቈይ” አለው። ስለዚህ ሁለቱም በሉ። ሰውየውም ከቁባቱና ከሎሌው ጋር ሊሄድ በተነሣ ጊዜ፣ አማቹ የብላቴናዪቱ አባት፣ “እነሆ፣ ቀኑ ሊመሽ ተቃርቧል፤ ይህችን ሌሊት እደር። እነሆ፣ ቀኑ ሊያልቅ ነው፤ እዚህ አድረህ ደስ ይበልህ። ነገ ማልደህ ተነሥተህ መንገድህን ሂድ፤ ወደ ቤትህም ትሄዳለህ” አለው። ሰውየው ግን በዚያች ሌሊት ሊያድር እምቢ አለ፤ ተነሥቶ ሄደ፤ ኮርቻ ከተጫኑ ከሁለቱ አህዮቹና ከቁባቱ ጋር ኢያቡስ (ኢየሩሳሌም) ትይዩ ደረሰ። ወደ ኢያቡስም በቀረቡ ጊዜ ቀኑ እጅግ መሽቶ ነበር፤ ሎሌውም ጌታውን፣ “እባክህ፣ ና፤ ወደዚህ ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ ገብተን እናድር” አለው።

ጌታውም መልሶ፣ “ከእስራኤል ልጆች ወዳልሆነች ወደ መጻተኛ ከተማ አንገባም፤ ወደ ጊብዓ እናልፋለን” አለው። ሎሌውንም፣ “ና፤ ከእነዚህ ስፍራዎች ወደ አንዱ ደርሰን በጊብዓ ወይም በራማ እናድር” አለው። ስለዚህ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ በብንያም ካለችው ከጊብዓም አጠገብ ፀሐይ ጠለቀችባቸው። በጊብዓም ሊያድሩ ገቡ። ገብቶም በከተማዪቱ አደባባይ ተቀመጠ፤ ነገር ግን ወደ ቤቱ አስገብቶ የሚያሳድራቸው ማንም አልነበረም።

በመሸም ጊዜ አንድ ሽማግሌ ከዕርሻ ሥራው ተመለሰ። እርሱም ከኤፍሬም ተራራማ አገር የመጣ፤ በጊብዓም እንደ መጻተኛ የሚኖር ነበር፤ የአገሩ ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ። ሽማግሌውም ቀና ብሎ በከተማዪቱ አደባባይ መንገደኛውን አየ፤ “ወዴት ትሄዳለህ? ከወዴትስ መጣህ?” ብሎም ጠየቀው።

እርሱም፣ “ከይሁዳ ቤተ ልሔም ተነሥተን ወደ ኤፍሬም ተራራማ አገር ራቅ ወዳለ ክፍል እንጓዛለን፤ መኖሪያዬ በዚያ ነው። ወደ ይሁዳ ቤተ ልሔም ሄጄ ነበር፤ አሁንም ወደ አባታችን ቤት እሄዳለሁ፤ ነገር ግን ወደ ቤቱ የሚያስገባኝ ማንም የለም። ለአህዮቻችን ገለባም መኖም አለን፤ ለእኔም፣ ለገረድህም፣ ከባሪያዎችህ ጋር ላለው ጐበዝም እንጀራና የወይን ጠጅ አለን። ምንም አይጐድለንም” አለው።

ሽማግሌውም፣ “ሰላም ለአንተ ይሁን። የሚያስፈልግህን ሁሉ እኔ አሟላልሃለሁ፤ ብቻ በአደባባይ አታድር” አለው። ወደ ቤቱም አስገባው፤ ለአህዮቹም መኖ ሰጠ፤ እግራቸውንም ታጥበው በሉ፤ ጠጡም።

ደስ እያላቸውም ሳለ፣ እነሆ የከተማዪቱ ምናምንቴ ሰዎች ቤቱን ከበቡ፤ በሩንም ያንኳኩ ነበር። ባለ ቤቱንም ሽማግሌውን፣ “ከእርሱ ጋር እንድንተኛ ወደ ቤትህ የገባውን ሰው አውጣልን” ብለው ጮኹበት።

ባለ ቤቱም ወደ እነርሱ ወጥቶ፣ “አይሆንም ወንድሞቼ፤ ይህ ሰው ወደ ቤቴ ገብቷልና እባካችሁ ክፉ ነገር አታድርጉ፤ ይህን አሳፋሪ ነገር አትሥሩ። እነሆ፣ ድንግል ልጄና የእርሱ ቁባት አሉ፤ ላውጣቸው። አዋርዱአቸው፤ መልካም የመሰላችሁንም ሁሉ አድርጉባቸው፤ ነገር ግን በዚህ ሰው ላይ ይህን አሳፋሪ ነገር አታድርጉ” አለ።

ሰዎቹ ግን ሊሰሙት አልወደዱም። ስለዚህ ሰውየው ቁባቱን ይዞ ወደ እነርሱ ገፍቶ አወጣት፤ እነርሱም ሌሊቱን ሁሉ እስኪነጋ ድረስ ደፈሩአት፤ አንገላቱአትም፤ ከዚያም ለቀቁአት። ጎህ ሲቀድ ሴቲቱ መጥታ ጌታዋ ባለበት በሰውየው ቤት ደጃፍ ላይ ወደቀች፤ ብርሃንም እስኪሆን ድረስ እዚያ ቀረች። ጌታዋም ማልዶ ተነሥቶ የቤቱን በሮች ከፈተ፤ መንገዱንም ሊሄድ ወጣ፤ እነሆም ቁባቱ እጆቿን በመድረኩ ላይ አድርጋ በቤቱ መግቢያ ላይ ወድቃ ነበር። እርሱም፣ “ተነሺ፤ እንሂድ” አላት። ምንም መልስ ግን አልነበረም። ስለዚህ በአህያው ላይ ጫናት፤ ወደ ቤቱም ሄደ።

ወደ ቤቱም በደረሰ ጊዜ ቢላዋ አነሣ፤ ቁባቱንም ይዞ ብልት በብልት ወደ ዐሥራ ሁለት ቁራጭ ቈረጣት፤ ወደ እስራኤልም አገር ሁሉ ላካት። ያዩትም ሁሉ፣ “የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ተደርጎም ታይቶም አያውቅም። ይህን ነገር ተመልከቱ፤ ተማከሩበት፤ ተናገሩም” አሉ።

A young man reading the Father's Heart Bible (FHB) print edition in a coffee shop አሁን በኅትመት ይገኛል

አስተያየቶች

ሐሳብ፣ ጥያቄ፣ ወይም ይህ ምዕራፍ በልብዎ ያነሣሣው ቃል — እዚህ ያካፍሉ። እያንዳንዱ አስተያየት ስምዎን በአስተዋጽኦ አበርካቾች ግድግዳ ላይ ያሰፍራል።

ማንበብ፣ ማዳመጥ፣ መቅዳትና ማጋራት ለሁሉም ክፍት ነው — መለያ አያስፈልግም። አስተያየት መስጠት፣ ቁጥሮችን ማድመቅና የደረሱበትን ቦታ ምልክት ማድረግ ከነጻ መለያ ጋራ ይመጣሉ፤ እያንዳንዱ አስተያየትም ስምዎን በአስተዋጽኦ አበርካቾች ግድግዳ ላይ ያሰፍራል።

ቤተሰቡን ይቀላቀሉ — በነጻ ነው →
  • እስካሁን ምንም አስተያየት የለም። ድምፅዎን በማሰማት የመጀመሪያው ይሁኑ።