የኢዮብ የንጹሕ ልብ መሐላ
ኢዮብ በመሐላ ይደመድማል፤ ሕይወቱን አንድ በአንድ ይገልጣል። ምኞት የለም፤ ውሸት የለም፤ ለአገልጋይ ፍትሕን መንፈግ የለም፤ ድሀ አደግ ሲራብ ብቻውን መብላት የለም፤ በወርቅ መታመን የለም። ይፈርምበታል፤ የክስ ጽሑፉንም ይጠይቃል። ከዚያም ቃሉ እዚያው ያበቃል።
31 1“ከዐይኖቼ ጋራ ኪዳን አደረግሁ፤ ታዲያ እንዴት ድንግልን በፍትወት እመለከታለሁ? 2ከላይ ካለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምን ዕድል ፈንታ ይኖረኛል? ከከፍታ ካለው ሁሉን ቻይ ዘንድስ ምን ርስት? 3ለዐመፀኞች መዓት፣ ክፉ ለሚያደርጉም ጥፋት አይደለምን? 4መንገዶቼን አያይምን? ርምጃዬንም ሁሉ አይቈጥርምን?
5“በሐሰት ኖሬ እንደ ሆነ፣ እግሬም ወደ ተንኰል ፈጥኖ እንደ ሄደ፣ 6በትክክለኛ ሚዛን ይመዝነኝ፤ እግዚአብሔርም ንጽሕናዬን ይወቅ፤ 7ርምጃዬ ከመንገድ ፈቅቆ እንደ ሆነ፣ ልቤም ዐይኖቼን ተከትሎ እንደ ሆነ፣ እድፍም በእጆቼ ተጣብቆ እንደ ሆነ፣ 8እኔ ልዝራ ሌላውም ይብላ፤ የበቀለልኝም ተነቅሎ ይጣል።
9“ልቤ በሴት ተታሎ እንደ ሆነ፣ በባልንጀራዬም ደጃፍ አድፍጬ እንደ ሆነ፣ 10ሚስቴ ለሌላ ሰው ትገዛ፤ ሌሎችም ከእርሷ ጋራ ይተኙ። 11ይህ የሚያሳፍር ወንጀል ነውና፤ ፍርድም የሚገባው ኀጢአት ነው፤ 12እስከ ጥፋት ድረስ የሚበላ እሳት ነውና፤ መከሬንም ሁሉ ያቃጥል ነበር።
13“ወንድ ወይም ሴት አገልጋዬ በእኔ ላይ ክስ ባቀረቡ ጊዜ ፍትሕ ነፍጌአቸው እንደ ሆነ፣ 14ታዲያ እግዚአብሔር በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ? በሚመረምረኝም ጊዜ ምን እመልስለታለሁ? 15በማኅፀን ውስጥ የሠራኝ፣ አገልጋዬንም አልሠራውምን? በማኅፀንም ውስጥ ሁለታችንን የቀረጸ ያው አንዱ አይደለምን?
16“ድኾችን ከሚፈልጉት ነገር ከለከልኋቸው እንደ ሆነ፣ ወይም የመበለቲቱን ዐይኖች አደከምሁ እንደ ሆነ፣ 17እንጀራዬንም ብቻዬን በልቼ እንደ ሆነ፣ ድኻ ዐደግም ሳይበላ ቀርቶ እንደ ሆነ፣ 18ከሕፃንነቴ ጀምሮ እንደ አባት አሳድጌዋለሁና፣ ከእናቴም ማኅፀን ጀምሮ መበለቲቱን መርቻለሁ፤ 19ልብስ በማጣት የሚጠፋን ሰው አይቼ እንደ ሆነ፣ ወይም የሚከናነበው የሌለውን ችግረኛ አይቼ እንደ ሆነ፣ 20በበጎቼ ጸጉር ስላሟሟቅሁት ሰውነቱ ሁሉ ካልባረከኝ፣ 21በፍርድ ቤት ረዳት እንዳለኝ ዐይቼ፣ ድኻ ዐደግ ላይ እጄን አንሥቼ እንደ ሆነ፣ 22ትከሻዬ ከመሰኪያው ይውለቅ፤ ክንዴም ከመገጣጠሚያው ይሰበር። 23ከእግዚአብሔር የሚመጣ መዓት ያስፈራኝ ነበርና፤ በግርማውም ፊት ምንም ማድረግ አልችልም ነበር።
24“ወርቅን ተማምኜ እንደ ሆነ፣ ወይም ጥሩ ወርቅን፣ ‘አንተ ዋስትናዬ ነህ’ ብዬ እንደ ሆነ፣ 25ሀብቴ ብዙ ስለ ሆነ፣ እጄም እጅግ ስላተረፈች ተመክቼ እንደ ሆነ፣ 26ፀሓይን ስታበራ አይቼ እንደ ሆነ፣ ወይም ጨረቃን በክብር ስትንቀሳቀስ አይቼ እንደ ሆነ፣ 27ልቤም በስውር ተታልሎ እንደ ሆነ፣ እጄም እነርሱን ለማምለክ ከአፌ መሳም ልካ እንደ ሆነ፣ 28ይህም ፍርድ የሚገባው ኀጢአት ነው፤ ከላይ ያለውን እግዚአብሔርን ክጄ ነበርና።
29“በጠላኝ ሰው ጥፋት ደስ ተሰኝቼ እንደ ሆነ፣ ወይም ክፉ በደረሰበት ጊዜ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ። 30በነፍሱ ላይ እርግማንን በመጥራት አፌ ኀጢአትን እንዲሠራ ፈጽሞ አልፈቀድሁም፤ 31የቤቴ ሰዎች፣ ‘ከማዕዱ ያልጠገበ ማን ነው?’ ብለው አያውቁም እንደ ሆነ፣ 32እንግዳ በጎዳና ላይ አላደረም፤ በሬን ለመንገደኛ ከፍቼ ነበርና። 33እንደ ሰዎች ሁሉ ኀጢአቴን ሸፍኜ እንደ ሆነ፣ በደሌንም በልቤ ውስጥ ሰውሬ እንደ ሆነ፣ 34ብዙኃኑን እጅግ ፈርቼ ነበርና፣ የጐሠኞችም ንቀት አስደነገጠኝ፤ ስለዚህ ዝም አልሁ፤ ወደ ውጭም አልወጣሁም።
35“ምነው የሚሰማኝ በነበረ! እነሆ፣ ፊርማዬ ይህ ነው፤ ሁሉን ቻዩ ይመልስልኝ! ከሳሼም ክሱን ጽፎ ያቅርብ! 36በትከሻዬ ላይ በእርግጥ እሸከመው ነበር፤ እንደ ዘውድም አድርጌ በራሴ ላይ ባሰርሁት ነበር። 37ርምጃዬን ሁሉ በተራ በነገርሁት ነበር፤ እንደ መስፍንም ሆኜ ወደ እርሱ በቀረብሁ ነበር።
38“መሬቴ በእኔ ላይ ጮኻ እንደ ሆነ፣ ትልሞችዋም በአንድነት አልቅሰው እንደ ሆነ፣ 39ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ እንደ ሆነ፣ ወይም የባለቤቶችዋን ነፍስ አጥፍቼ እንደ ሆነ፣ 40በስንዴ ፈንታ እሾህ፣ በገብስም ፈንታ አረም ይብቀል።” የኢዮብ ቃል ተፈጸመ።