አባታችን ልጅን ተስፋ ሰጠ
እስራኤል ለአርባ ዓመት በፍልስጥኤማውያን እጅ ይሰጣሉ። የአብ መልእክተኛ ለመካኒቱ ሴት ከማኅፀን ጀምሮ የተለየ ወንድ ልጅ ተስፋ ይሰጣታል፤ ማኑሄ ሲጠይቅም ተመልሶ ይመጣል። የጎብኚው ስም ከማስተዋል በላይ ነው፤ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ያርጋል። ሶምሶን ይወለዳል፣ ይባረካልም።
13 1እስራኤላውያን እንደገና በአባታችን ፊት ክፉ አደረጉ፤ ስለዚህ ለአርባ ዓመት በፊልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
2ማኑሔ የተባለ አንድ ሰው ከዳን ነገድ ከጾርዓ ነበር፤ ሚስቱም መካን ስለ ነበረች ልጅ አልወለደችም።
3የአባታችን መልአክ ለሴቲቱ ተገለጠላትና እንዲህ አላት፤ “አንቺ መካን ነሽ፤ ልጅም የለሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። 4አሁንም የወይን ጠጅ ወይም የሚያሰክር መጠጥ እንዳትጠጪ ተጠንቀቂ፤ ርኩስ የሆነውንም ነገር ሁሉ አትብዪ፤ 5ትፀንሻለሽና ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ። ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም፤ ብላቴናው ከማኅፀን ጀምሮ የአባታችን ናዝራዊ ይሆናልና፤ እስራኤልንም ከፊልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።”
6ሴቲቱም ሄዳ ለባሏ እንዲህ አለች፤ “የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፤ መልኩም እንደ አባታችን መልአክ መልክ እጅግ የሚያስፈራ ነበር። ከወዴት እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፤ እርሱም ስሙን አልነገረኝም። 7ነገር ግን እንዲህ አለኝ፤ ‘እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ አሁንም የወይን ጠጅ ወይም የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኩስ የሆነውንም ነገር አትብዪ፤ ብላቴናው ከማኅፀን ጀምሮ እስከ ሞቱ ቀን ድረስ የአባታችን ናዝራዊ ይሆናልና።’”
8ከዚያም ማኑሔ አባታችንን ለምኖ እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ አባት ሆይ፤ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እባክህ ዳግመኛ ወደ እኛ ይምጣ፤ ለሚወለደውም ብላቴና ምን ማድረግ እንዳለብን ያስተምረን።”
9አባታችንም የማኑሔን ድምፅ ሰማ፤ የአባታችን መልአክም በሜዳ ተቀምጣ ወደ ነበረችው ሴት ዳግመኛ መጣ፤ ባሏ ማኑሔ ግን ከእርሷ ጋራ አልነበረም። 10ሴቲቱም ፈጥና ሮጣ ለባሏ እንዲህ አለች፤ “እነሆ፣ ከዚህ በፊት ወደ እኔ የመጣው ሰው ተገልጦልኛል!”
11ማኑሔም ተነሥቶ ሚስቱን ተከትሎ ወደ ሰውየው መጣ፤ “ለሴቲቱ የተናገርህ ሰው አንተ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔ ነኝ” አለ።
12ማኑሔም እንዲህ አለ፤ “ቃልህ በሚፈጸምበት ጊዜ የብላቴናውን ኑሮና ሥራ የሚገዛው ምን ይሆናል?”
13የአባታችንም መልአክ ማኑሔን እንዲህ አለው፤ “ሴቲቱ ከነገርኋት ሁሉ ትጠንቀቅ። 14ከወይን ተክል የሚገኘውን ምንም አትብላ፤ የወይን ጠጅ ወይም የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤ ርኩስ የሆነውንም ነገር አትብላ፤ ያዘዝኋትን ሁሉ ትጠብቅ።”
15ማኑሔም የአባታችንን መልአክ እንዲህ አለው፤ “እባክህ እንድናቆይህ ፍቀድልን፤ ለአንተም የፍየል ጠቦት እናዘጋጃለን።”
16የአባታችንም መልአክ ማኑሔን እንዲህ አለው፤ “ብታቆየኝም እንኳ ከምግብህ አልበላም፤ የሚቃጠል መሥዋዕት ብታዘጋጅ ግን ለአባታችን አቅርበው።” ማኑሔ የአባታችን መልአክ እንደ ሆነ አላወቀም ነበርና።
17ማኑሔም የአባታችንን መልአክ፣ “ቃልህ በሚፈጸምበት ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው።
18የአባታችንም መልአክ፣ “ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? ለማስተዋል የሚያዳግት ነውና።” አለው።
19ስለዚህ ማኑሔ የፍየሉን ጠቦትና የእህል ቍርባን ወስዶ ድንቅ ለሚያደርገው ለአባታችን በዐለቱ ላይ አቀረበ፤ ማኑሔና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር። 20የመሠዊያው ነበልባል ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የአባታችን መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ። ማኑሔና ሚስቱም ይህን አይተው በግንባራቸው ወደ ምድር ወደቁ። 21የአባታችንም መልአክ ለማኑሔና ለሚስቱ ዳግመኛ አልተገለጠም። ያን ጊዜ ማኑሔ የአባታችን መልአክ እንደ ሆነ ዐወቀ። 22ማኑሔም ሚስቱን፣ “አባታችንን አይተናልና በእርግጥ እንሞታለን!” አላት።
23ሚስቱም እንዲህ አለችው፤ “አባታችን ሊገድለን ወዶ ቢሆን ኖሮ፣ ከእጃችን የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን ባልተቀበለ፤ ይህን ሁሉ ባላሳየን፤ አሁንም ይህን እንድንሰማ ባላደረገን ነበር።” 24ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሳምሶን ብላ ጠራች። ብላቴናውም አደገ፤ አባታችንም ባረከው። 25የአባታችንም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በማሃኔ ዳን ሊያነሣሣው ጀመረ።