የሙሴ የመሰናበቻ ንግግር
ሙሴ በመቶ ሃያ ዓመቱ ሥራውን ያስረክባል። አብ ቀድሟችሁ ይሄዳል፤ ከቶም አይተዋችሁም፤ ኢያሱም ይመራችኋል። ሕጉ ተጽፎ በየሰባተኛው ዓመት ልጆችን ጨምሮ ለሁሉም ጮክ ተብሎ ይነበባል። አብ እንደሚያፈገፍጉ ስለሚያውቅ መዝሙር እንዲማሩ ይደረጋል።
31 1ሙሴም ሄዶ እነዚህን ቃሎች ለእስራኤል ሁሉ ተናገረ። 2እንዲህም አላቸው፤ “ዛሬ 120 ዓመት ሆኖኛል፤ ከእንግዲህ ወዲያ መውጣትና መግባት አልችልም፤ አባታችንም፣ ‘ይህን ዮርዳኖስ አትሻገርም’ ብሎኛል። 3አባታችሁ ራሱ በፊታችሁ ይሻገራል፤ እነዚህንም ሕዝቦች ከፊታችሁ ያጠፋል፤ እናንተም ታወጧቸዋላችሁ። ኢያሱ፣ አባታችን እንደ ተናገረ፣ በፊታችሁ ይሻገራል። 4አባታችን በአሞራውያን ነገሥታት በሴዎንና በዐግ፣ እንዲሁም በምድራቸው ባጠፋቸው ጊዜ እንዳደረገ፣ እነርሱንም እንዲሁ ያደርግባቸዋል። 5አባታችን አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ እኔም እንዳዘዝኋችሁ በትክክል ልታደርጉባቸው ይገባል። 6ጠንክሩ፤ ደፋርም ሁኑ። አትፍሩአቸው፤ አትደንግጡባቸውም፤ ምክንያቱም አባታችሁ ከእናንተ ጋራ ይሄዳልና፤ ከቶ አይተዋችሁም፤ አይጥላችሁምም።”
7ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “ጠንክር፤ ደፋርም ሁን፤ ምክንያቱም አባታችን ለአባቶቻቸው ሊሰጣቸው ወደ ማለላቸው ምድር ከዚህ ሕዝብ ጋራ ትገባለህ፤ አንተም ርስት እንዲሆናቸው ታካፍላቸዋለህ። 8አባታችን ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋራ ይሆናል። ከቶ አይተውህም፤ አይጥልህምም። አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ።”
ለእስራኤል በአደራ የተሰጠ ሕግ
9ሙሴም ይህን ሕግ ጽፎ የአባታችንን የኪዳን ታቦት ለሚሸከሙት ለሌዊ ልጆች ለካህናት፣ ለእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰጠ። 10ሙሴም እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “በየሰባት ዓመቱ መጨረሻ፣ በዕዳ ስረዛ ዓመት በተወሰነው ጊዜ፣ በዳስ በዓል ወቅት፣ a a v10 የዳስ በዓል፦ ቤተ ሰቦች የእስራኤልን የምድረ በዳ ጒዞ ለማስታወስ ጊዜያዊ ዳሶችን ሠርተው ይኖሩበት የነበረ፣ በመከር ወቅት የሚከበር የሳምንት በዓል። 11እስራኤል ሁሉ በሚመርጠው ስፍራ በአባታችሁ ፊት በሚመጣበት ጊዜ፣ ይህን ሕግ በእስራኤል ሁሉ ፊት ጮክ ብላችሁ አንብቡ። 12ሰምተው ተምረው አባታችሁንም እንዲፈሩ፣ የዚህንም ሕግ ቃላት ሁሉ ጠብቀው እንዲያደርጉ፣ ሕዝቡን—ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ በከተሞቻችሁም የሚኖረውን መጻተኛ—ሰብስቡ። 13ይህንም ሕግ የማያውቁ ልጆቻቸው፣ ለመውረስ ዮርዳኖስን የምትሻገሩላትን ምድር በምትኖሩባት ዘመን ሁሉ፣ ሰምተው አባታችሁን መፍራት ይማራሉ።”
አባታችን ኢያሱን ሾመ
14አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የሞትህ ቀን ቀርቦአል። ኢያሱን ጥራና በመገናኛው ድንኳን ቅረቡ፤ እኔም እሾመዋለሁ።” ሙሴና ኢያሱም ሄደው በመገናኛው ድንኳን ቀረቡ።
15አባታችንም በደመና ዐምድ ሆኖ በድንኳኑ ተገለጠ፤ የደመናውም ዐምድ በድንኳኑ መግቢያ ቆመ። 16አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ከአባቶችህ ጋራ ልትተኛ ነህ፤ ይህም ሕዝብ ተነሥቶ ወደሚገባባት ምድር ባዕዳን አማልክትን ተከትሎ ያመነዝራል፤ እኔንም ይተዋል፤ ከእነርሱም ጋራ የገባሁትን ኪዳን ያፈርሳል። 17በዚያም ቀን ቍጣዬ በእነርሱ ላይ ይነድዳል፤ እተዋቸዋለሁ፤ ፊቴንም ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይበላሉ። ብዙ መቅሠፍቶችና መከራዎች ይደርሱባቸዋል። በዚያም ቀን፣ ‘እነዚህ መቅሠፍቶች የደረሱብን አምላካችን ከእኛ ጋራ ስለሌለ አይደለምን?’ ይላሉ። 18በዚያም ቀን፣ ወደ ሌሎች አማልክት በመዞር ስላደረጉት ክፋት ሁሉ፣ ፊቴን ፈጽሞ እሰውራለሁ።
19አሁንም ይህን መዝሙር ለራሳችሁ ጻፉ፤ ለእስራኤላውያን አስተምሩት፤ በአፋቸውም አኑሩት፤ ይህ መዝሙር በእስራኤላውያን ላይ ለእኔ ምስክር ይሆን ዘንድ። 20ለአባቶቻቸው የማልሁላትን፣ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ባስገባኋቸው ጊዜ፣ ይበላሉ፤ ጠግበውም ይወፍራሉ፤ ወደ ሌሎች አማልክትም ዘወር ብለው ያገለግሏቸዋል፤ እኔንም ይንቃሉ፤ ኪዳኔንም ያፈርሳሉ። 21ብዙ መቅሠፍቶችና መከራዎች ባገኟቸው ጊዜ፣ ይህ መዝሙር ምስክር ሆኖ ይጋፈጣቸዋል፤ ምክንያቱም ከዘሮቻቸው አፍ አይረሳምና። ሊሰጣቸው ወደ ማልሁላት ምድር ሳላስገባቸው፣ ዛሬ የሚያስቡትን አውቃለሁና።”
22ሙሴም በዚያኑ ቀን ይህን መዝሙር ጽፎ ለእስራኤላውያን አስተማረው።
23አባታችንም የነዌን ልጅ ኢያሱን አዘዘው፤ “ጠንክር፤ ደፋርም ሁን፤ ሊሰጣቸው ወደ ማልሁላት ምድር እስራኤላውያንን ታስገባለህና፤ እኔም ራሴ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ።”
24ሙሴም የዚህን ሕግ ቃላት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በመጽሐፍ ጽፎ በጨረሰ ጊዜ፣ 25የአባታችንን የኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ 26“ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፤ በአባታችሁ የኪዳን ታቦት ጎን አኑሩት፤ በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኑር። 27ዐመፃችሁንና ዐንገተ ደንዳናነታችሁን አውቃለሁና። ዛሬ በሕይወት ከእናንተ ጋራ ሳለሁ እንኳ በአባታችን ላይ ዐምፃችኋል፤ ከሞቴ በኋላማ ይልቁን እንዴት ይሆን! 28እነዚህን ቃሎች ለእነርሱ እናገር ዘንድ፣ ሰማይንና ምድርንም በእነርሱ ላይ ምስክር እንዲሆኑ እጠራ ዘንድ፣ የነገዶቻችሁን ሽማግሌዎችና ሹማምት ሁሉ ወደ እኔ ሰብስቡ። 29ከሞቴ በኋላ ፈጽሞ እንደምትበላሹና ካዘዝኋችሁ መንገድ ፈቀቅ እንደምትሉ አውቃለሁና። በመጨረሻውም ዘመን መቅሠፍት ይደርስባችኋል፤ ምክንያቱም በአባታችን ፊት ክፉ የሆነውን በማድረግ፣ በእጆቻችሁ ሥራ ታስቈጡታላችሁና።”
30ሙሴም የዚህን መዝሙር ቃላት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ለእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ተናገረ።