ለቲቶ፣ ለእውነተኛ ልጄ
በቀርጤስ ደሴት ሽማግሌዎችን ስለ መሾምና ጤናማ ትምህርትን ስለ ማስተማር ለቲቶ የተሰጠ መመሪያ።
1 1የአባታችን አገልጋይ፣ የኢየሱስ ክርስቶስም ሐዋርያ የሆንሁ ጳውሎስ፤ ይህም የአባታችን ለተመረጡት እምነትና ወደ እግዚአብሔር መገዛት ለሚመራ የእውነት ዕውቀት ነው፤ 2ይህም ፈጽሞ የማይዋሽ አባታችን ዘመናት ከመጀመራቸው አስቀድሞ ተስፋ በሰጠው በዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ ነው፤ 3በራሱም ጊዜ፣ በመድኀኒታችን በአባታችን ትእዛዝ ለእኔ በአደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ። 4በጋራ እምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለቲቶ፤ ከአባታችንና ከመድኀኒታችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ይሁን።
የአብን ባሕርይ የሚያንጸባርቁ ሽማግሌዎች
5በቀርጤስ የተውኩህ ስለዚህ ምክንያት ነበር፤ ይኸውም የቀረውን ነገር ትፈጽም ዘንድ፣ ባዘዝሁህም መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን ትሾም ዘንድ ነው። 6ሽማግሌ ነውር የሌለበት፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ በመዳራት ወይም በዐመፅ የማይከሰሱ ታማኝ ልጆች ያሉት ሊሆን ይገባል። 7ኤጲስ ቆጶስ እንደ አባታችን መጋቢ ነውር የሌለበት ሊሆን ይገባልና፤ ትዕቢተኛ፣ ቁጡ፣ ሰካራም፣ ጨካኝ ወይም ነውረኛ ረብ የሚመኝ አይሁን፤ 8ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፣ መልካሙን የሚወድድ፣ ራሱን የሚገዛ፣ ቅን፣ ቅዱስና ሥርዐታማ ይሁን። 9እንደተማረው የታመነውን ቃል አጥብቆ ሊይዝ ይገባዋል፤ ይኸውም በቀና ትምህርት ሊያበረታታ፣ የሚቃወሙትንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ ነው።
10ዐመፀኞች የሆኑ፣ ከንቱ የሚናገሩና ሌሎችን የሚያስቱ ብዙዎች አሉና፤ ይልቁንም ከተገረዙት ወገን የሆኑ። a a v10 ‘ከተገረዙት ወገን’ የሚለው፣ አሕዛብ አማኞች በእውነት ለመዳን መገረዝ አለባቸው ብለው አጥብቀው የሚያስተምሩ፣ ከአይሁድ ባሕል የመጡ አስተማሪዎችን ያመለክታል። 11እነዚህን አፋቸውን ማስያዝ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ለሚያሳፍር ረብ ሲሉ ሊያስተምሩ የማይገባቸውን በማስተማር ቤተ ሰቦችን በሙሉ ያፈርሳሉ። 12ከእነርሱው ነቢያት አንዱ እንዲህ ብሏል፤ “የቀርጤስ ሰዎች ሁልጊዜ ውሸታሞች፣ ክፉ አራዊት፣ ሰነፍ ሆዳሞች ናቸው።” 13ይህ ምስክርነት እውነት ነው። ስለዚህ በእምነት የቀኑ ይሆኑ ዘንድ አጥብቀህ ውቀሳቸው፤ 14የአይሁድን ተረቶችና እውነትን ከሚጥሉ ሰዎች የመጡ ትእዛዛትን ቸል ይሉ ዘንድ። 15ለንጹሐን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤ ለረከሱትና ለማያምኑት ግን ምንም ንጹሕ የለም፤ አእምሮአቸውም ኅሊናቸውም ረክሰዋልና። 16አባታችንን እናውቃለን ይላሉ፤ በሥራቸው ግን ይክዱታል፤ አስጸያፊዎች፣ የማይታዘዙና ለማንኛውም መልካም ሥራ የማይበቁ ናቸው።