ጠላቶች ሥራውን ሲያፌዙበት
ሰንባላጥ ቀበሮ እንኳ ቅጥሩን ይጥለዋል ብሎ ያላግጣል፤ ስድቡም ወደ ጥቃት ሴራ ይለወጣል። እነርሱ ወደ አብ ይጸልያሉ፤ ዘብም ያቆማሉ፤ እኩሌቶቹ ሲሠሩ እኩሌቶቹ ታጥቀው ይቆማሉ፤ እያንዳንዱም ሰይፍ ይዞ ከንጋት ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ ይሠራል።
4 1ሰንባላጥ ቅጥሩን መልሰን እየሠራን እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ፣ እጅግ ተቈጣ፤ በንዴትም ገነፈለ፤ አይሁድንም አፌዘባቸው። 2በወንድሞቹና በሰማርያ ሰራዊት ፊት እንዲህ አለ፤ “እነዚህ ደካሞች አይሁድ ምን እያደረጉ ነው? ቅጥሩን ለራሳቸው መልሰው ይሠራሉን? መሥዋዕት ያቀርባሉን? በአንድ ቀን ይጨርሳሉን? የተቃጠሉትን ድንጋዮች ከፍርስራሹ ክምር መልሰው ሕያው ሊያደርጓቸው ይችላሉን?”
3በአጠገቡ የነበረው አሞናዊው ጦብያም እንዲህ አለ፤ “ይህ እየሠሩት ያለው የድንጋይ ቅጥር ቀበሮ እንኳ ቢወጣበት ያፈርሰዋል!”
4አባታችን ሆይ፤ የተናቅን ነንና ስማን። ስድባቸውን ወደ ራሳቸው ራስ መልስ፤ ወደ ምርኮ ምድርም ተማርከው እንዲወሰዱ አሳልፈህ ስጣቸው። 5በደላቸውን አትሸፍን፤ ኀጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፤ ሠራተኞቹን ፊት ለፊት ተሳድበዋልና።
6ሕዝቡ በፍጹም ልባቸው ሠርተው ነበርና ቅጥሩን እስከ እኵሌታው ቍመት ድረስ ሁሉም እስኪጋጠም ዐደስን።
7ነገር ግን ሰንባላጥ፣ ጦብያ፣ ዐረቦች፣ አሞናውያንና አሽዶዳውያን የኢየሩሳሌም ቅጥር ጥገና እየተራመደ እንደ ሆነ፣ ክፍተቶቹም መዘጋት እንደ ጀመሩ በሰሙ ጊዜ፣ እጅግ ተቈጡ። 8ሁሉም በኢየሩሳሌም ላይ መጥተው ሊዋጉና ሊያደናግሩ አብረው አደሙ።
9እኛ ግን ወደ አባታችን ጸለይን፤ በእነርሱም ላይ ሌትና ቀን ዘብ አቆምን።
10በዚህ መካከል የይሁዳ ሰዎች እንዲህ አሉ፤ “ሠራተኞቹ ጒልበታቸው እየደከመ ነው፤ ፍርስራሹም እጅግ በዝቷል፤ ስለዚህ ቅጥሩን መልሰን ልንሠራ አንችልም።” 11ጠላቶቻችንም እንዲህ አሉ፤ “ሳያውቁ ወይም ሳያዩን በመካከላቸው እንደርሳለን፤ እንገድላቸዋለን፤ ሥራውንም እናስቆማለን።”
12ከዚያም በአጠገባቸው የሚኖሩ አይሁድ መጥተው ዐሥር ጊዜ፣ “ወደ የትም ብትዞሩ፣ በእኛ ላይ ይመጣሉ” ብለው ነገሩን።
13ስለዚህ ከቅጥሩ ዝቅተኛ ክፍሎች ኋላ፣ በተጋለጡት ስፍራዎች ሰዎችን አቆምሁ፤ በየወገናቸውም ከሰይፋቸው፣ ከጦራቸውና ከቀስታቸው ጋራ አሰለፍኋቸው። 14ነገሩን ከተመለከትሁ በኋላ፣ ተነሥቼ መኳንንቱን፣ ሹማምንቱንና የቀሩትን ሕዝብ እንዲህ አልኋቸው፤ “እነርሱን አትፍሩ። ታላቁንና የተፈራውን ገዥ አባታችንን አስቡ፤ ስለ ወንድሞቻችሁ፣ ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ስለ ሚስቶቻችሁና ስለ ቤቶቻችሁ ተዋጉ።”
15ጠላቶቻችን ሴራቸውን እንዳወቅን፣ አባታችንም እንዳከሸፈባቸው በሰሙ ጊዜ፣ ሁላችንም ወደ ቅጥሩ፣ እያንዳንዳችን ወደ ራሳችን ሥራ ተመለስን። 16ከዚያ ቀን ጀምሮ፣ ከሰዎቼ እኵሌቶቹ ሥራውን ይሠሩ ነበር፤ እኵሌቶቹ ግን በጦር፣ በጋሻ፣ በቀስትና በጥሩር ታጥቀው ነበር። አዛዦቹም ከይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ኋላ ተሰልፈው ነበር፤ 17እነርሱም ቅጥሩን ይሠሩ ነበር። ዕቃ የሚሸከሙትም በአንድ እጃቸው ሥራቸውን ይሠሩ፣ በሌላው እጃቸውም የጦር መሣሪያ ይይዙ ነበር፤ 18ከሠራተኞቹም እያንዳንዱ ሲሠራ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ነበር። መለከቱን የሚነፋው ሰው ግን በአጠገቤ ይቆም ነበር። 19ከዚያም መኳንንቱን፣ ሹማምንቱንና የቀሩትን ሕዝብ እንዲህ አልኋቸው፤ “ሥራው ታላቅና የተበተነ ነው፤ እኛም በቅጥሩ ላይ አንዳችን ከሌላችን ተራርቀናል። 20የመለከቱን ድምፅ በሰማችሁበት ስፍራ ሁሉ፣ በዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ። አባታችን ስለ እኛ ይዋጋል!”
21ስለዚህ ከሰዎቹ እኵሌቶቹ ከንጋት ጀምሮ እስከ ከዋክብት መውጣት ድረስ ጦር ይዘው፣ ሥራውን ቀጠልን። 22በዚያም ጊዜ ሕዝቡን እንዲህ አልኋቸው፤ “ሌሊት ዘብ ሆነው፣ ቀን ደግሞ ሠራተኛ ሆነው እንዲያገለግሉ፣ እያንዳንዱ ከረዳቱ ጋራ በኢየሩሳሌም ውስጥ ያድር።” 23ስለዚህ እኔም ሆንሁ ወንድሞቼ፣ ሰዎቼም ሆኑ የተከተሉኝ ዘቦች ልብሳችንን ከቶ አላወለቅንም፤ ውሃ ለመቅዳት እንኳ ሲሄድ እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ ይይዝ ነበር።