ቤተ ሰቡ ቅጥሩን በአንድነት እንደ ገና ሠራ
በር በበር፣ ክፍል በክፍል፣ ከተማዪቱ ሁሉ መሣሪያ ታነሣለች፤ ካህናት፣ አንጥረኞች፣ ሽቶ ቀማሚ፣ የአውራጃ ገዦች፣ የኢያሪኮና የቴቁሔ ሰዎች፣ ሰሎምም ከሴቶች ልጆቹ ጋር ይሠራል። ለሥራው ራሳቸውን ዝቅ ለማድረግ እምቢ ያሉት የቴቁሔ መኳንንት ብቻ ናቸው።
3 1ሊቀ ካህናቱ ኤልያሲብና ባልንጀሮቹ ካህናት ተነሥተው የበጎችን በር ሠሩ። ቀደሱትም፤ መዝጊያዎቹንም አቆሙ፤ እስከ መቶው ግንብ፣ እስከ ሐናንኤል ግንብ ድረስ ቀደሱት። 2በአጠገባቸውም የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ በአጠገባቸውም የአምሪ ልጅ ዛኩር ሠራ።
3የሃሰናአ ልጆች የዓሣ በርን እንደ ገና ሠሩ፤ ግንዶቹን ጣሉ፤ መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን አቆሙ። 4በአጠገባቸውም የኮስ የልጅ ልጅ፣ የኦርዮ ልጅ ሜሬሞት ጠገነ። በአጠገባቸውም የመሼዛቤል የልጅ ልጅ፣ የበራክያ ልጅ መሱላም ጠገነ። በአጠገባቸውም የባዓና ልጅ ሳዶቅ ጠገነ። 5በአጠገባቸውም ተቆዓውያን ጠገኑ፤ መኳንንቶቻቸው ግን ለጌቶቻቸው ሥራ ጫንቃቸውን አላስገዙም።
6የፋሴሕ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ መሱላም አሮጌውን በር ጠገኑ፤ ግንዶቹን ጣሉ፤ መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን አቆሙ። 7በአጠገባቸውም ገባዖናዊው መላጥያና ሜሮኖታዊው ያዶን፣ የገባዖንና የሚጽጳ ሰዎች፣ ከወንዝ ማዶ ያለውን አገር የሚገዛው ገዥ ወንበር የሚገኝበትን ክፍል ጠገኑ። a a v7 “ከወንዝ ማዶ ያለው አገር” ይሁዳን ጨምሮ ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ምዕራብ ያሉትን አገሮች ሁሉ ያጠቃለለ የፋርስ የአስተዳደር ክልል ነበር። 8በአጠገቡም ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ የሆነው የሃርሃያ ልጅ ዩዚኤል ጠገነ። በአጠገቡም ሽቶ ቀማሚው ሐናንያ ጠገነ። ኢየሩሳሌምንም እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ መለሱ። 9በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የሁር ልጅ ሬፋያ ጠገነ። 10በአጠገባቸውም የሃሩማፍ ልጅ ይዳያ ከቤቱ ትይዩ ጠገነ፤ በአጠገቡም የሃሻብንያ ልጅ ሃጡስ ጠገነ። 11የሃሪም ልጅ መልክያና የጳሃት ሞዓብ ልጅ ሃሱብ ሌላውን ክፍልና የእቶኖችን ግንብ ጠገኑ። 12በአጠገቡም የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የሃሎሔስ ልጅ ሻሉም እርሱና ሴቶች ልጆቹ ጠገኑ።
13ሃኑንና የዛኖሐ ሰዎች የሸለቆውን በር ጠገኑ፤ እንደ ገና ሠርተው መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን አቆሙ፤ እስከ ጕድፍ በር ድረስም 1,500 ጫማ ያህል ቅጥር ጠገኑ።
14የቤትከሬም አውራጃ ገዥ የሆነው የራካብ ልጅ መልክያ የጕድፍን በር ጠገነ፤ እንደ ገና ሠርቶም መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን አቆመ።
15የሚጽጳ አውራጃ ገዥ የሆነው የኮልሖዜ ልጅ ሻሉን የምንጭን በር ጠገነ፤ እንደ ገና ሠርቶ ጣሪያ ሠራለት፤ መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን አቆመ። ደግሞም በንጉሡ የአትክልት ስፍራ አጠገብ ያለውን የሰሊሆምን ኵሬ ቅጥር ከዳዊት ከተማ እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ ጠገነ። 16ከእርሱም በኋላ የቤትጹር አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የዐዝቡቅ ልጅ ነህምያ ከዳዊት መቃብሮች ትይዩ፣ እስከ ሠራሽ ኵሬውና እስከ ኀያላን ቤት ድረስ ጠገነ። 17ከእርሱም በኋላ ሌዋውያን ጠገኑ፤ የባኒ ልጅ ረሁም ጠገነ። በአጠገቡም የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው ሐሻብያ ስለ አውራጃው ጠገነ። 18ከእርሱም በኋላ ባልንጀሮቻቸው ሌዋውያን ጠገኑ፤ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የሔናዳድ ልጅ ቢኑዪ ጠገነ። 19በአጠገቡም የሚጽጳ ገዥ የሆነው የኢያሱ ልጅ ዔዘር በማዕዘኑ ካለው የጦር ዕቃ ቤት ዕርገት ትይዩ ሁለተኛውን ክፍል ጠገነ። 20ከእርሱም በኋላ የዛባይ ልጅ ባሮክ ከማዕዘኑ ጀምሮ እስከ ሊቀ ካህናቱ ኤልያሲብ ቤት መግቢያ ድረስ ሌላውን ክፍል በትጋት ጠገነ። 21ከእርሱም በኋላ የኮስ የልጅ ልጅ፣ የኦርዮ ልጅ ሜሬሞት ከመግቢያው ጀምሮ እስከ ኤልያሲብ ቤት መጨረሻ ድረስ ሌላውን ክፍል ጠገነ። 22ከእርሱም በኋላ በዙሪያው ካለው ሜዳ የመጡ ካህናት ጠገኑ። 23ቀጥሎም ብንያምና ሃሱብ ከቤታቸው ትይዩ ጠገኑ። ቀጥሎም የዐናንያ የልጅ ልጅ፣ የመዓሤያ ልጅ ዐዛርያ ከገዛ ቤቱ አጠገብ ጠገነ። 24ከእርሱም በኋላ የሔናዳድ ልጅ ቢኑዪ ከዐዛርያ ቤት ጀምሮ እስከ ማዕዘኑና እስከ ጥጉ ድረስ ሌላውን ክፍል ጠገነ። 25የኡዛይ ልጅ ፓላል ከማዕዘኑና ከንጉሡ የላይኛ ቤተ መንግሥት ከወጣው ግንብ ትይዩ፣ በዘበኞች አደባባይ አጠገብ ጠገነ። ከእርሱም በኋላ የፋሮስ ልጅ ፈዳያ ጠገነ። 26በዖፌል የሚኖሩ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች በስተ ምሥራቅ ካለው የውሃ በር ትይዩና ከወጣው ግንብ ድረስ ጠገኑ። 27ከእነርሱም በኋላ ተቆዓውያን ከወጣው ታላቅ ግንብ ትይዩ ጀምሮ እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ሁለተኛውን ክፍል ጠገኑ።
28ከፈረስ በር በላይ ካህናት እያንዳንዳቸው ከየራሳቸው ቤት ትይዩ ጠገኑ። 29ከእርሱም በኋላ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ ከቤቱ ትይዩ ጠገነ። ከእርሱም በኋላ የምሥራቅ በር ጠባቂ የሆነው የሰኬንያ ልጅ ሸማያ ጠገነ። 30ከእርሱም በኋላ የሼሌምያ ልጅ ሐናንያና የጻላፍ ስድስተኛ ልጅ ሃኑን ሌላውን ክፍል ጠገኑ። ከእነርሱም በኋላ የበራክያ ልጅ መሱላም ከመኖሪያ ክፍሉ ትይዩ ጠገነ። 31ከእርሱም በኋላ ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ የሆነው መልክያ ከፍተሻ በር ትይዩ እስከ ቤተ መቅደስ አገልጋዮችና ነጋዴዎች ቤት ድረስ፣ እስከ ጥጉም ላይኛ ክፍል ድረስ ጠገነ። 32በጥጉ ላይኛ ክፍልና በበጎች በር መካከል ያለውን የወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎች ጠገኑ።