አባታችን ጋይን ለእስራኤል አሳልፎ ሰጠ
አብ ጋይን ለሁለተኛ ጊዜ በድብቅ ጦርና በማስመሰል ሽሽት አሳልፎ ይሰጣል፣ ንጉሡም ይሰቀላል። ከዚያም በጦርነቶች መካከል በሚገርም ሁኔታ ጉባኤው ሁሉ፣ መጻተኞችም ጭምር፣ በሁለት ተራሮች ላይ ይቆማሉ፤ የሕጉም ቃል ሁሉ፣ በረከቱና መርገሙ፣ ጮክ ተብሎ ይነበባል።
8 1አባታችንም ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “አትፍራ፤ አትደንግጥም። ተዋጊዎቹን ሁሉ ይዘህ ወደ ጋይ ውጣ። የጋይን ንጉሥ፣ ሕዝቡን፣ ከተማውንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ። 2በኢያሪኮና በንጉሡ ላይ እንዳደረግህ፣ በጋይና በንጉሡ ላይም እንዲሁ አድርግ፤ ምርኮዋንና እንስሳቿን ግን ለራሳችሁ ውሰዱ። ከከተማዪቱ ኋላ አድብተህ ጠብቅ።”
3ኢያሱና ተዋጊዎቹ ሁሉ ወደ ጋይ ለመውጣት ተነሡ። ኢያሱም ሠላሳ ሺህ ኀያላን ተዋጊዎችን መርጦ በሌሊት ሰደዳቸው። 4እንዲህ ሲልም አዘዛቸው፤ “ከከተማዪቱ ኋላ አድብታችሁ ጠብቁ፤ ከከተማዪቱም እጅግ አትራቁ፤ ሁላችሁም ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ። 5እኔና ሕዝቤ ሁሉ ወደ ከተማዪቱ እንቀርባለን። እነርሱም እንደ ቀድሞው ሊወጉን ሲወጡ፣ ከፊታቸው እንሸሻለን። 6ከከተማዪቱ አርቀን እስክናወጣቸው ድረስ ይከተሉናል፤ ‘እንደ ቀድሞው ከፊታችን ይሸሻሉ’ ይላሉና። ስለዚህ ከፊታቸው እንሸሻለን። 7እናንተም ከምትደበቁበት ተነሥታችሁ ከተማዪቱን ያዟት፤ አባታችሁ በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣታልና። 8ከተማዪቱንም በያዛችሁ ጊዜ በእሳት አቃጥሉአት፤ አባታችን እንዳዘዘ አድርጉ። እነሆ፣ አዝዣችኋለሁ።”
9ኢያሱም ሰደዳቸው፤ እነርሱም ወደ ማድፈጫው ስፍራ ሄደው በቤቴልና በጋይ መካከል፣ ከጋይ በስተ ምዕራብ ተቀመጡ፤ ኢያሱ ግን በዚያች ሌሊት በሕዝቡ መካከል አደረ። 10ኢያሱም ማልዶ ተነሥቶ ሕዝቡን አሰባሰበ፤ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋርም ሆኖ ወደ ጋይ መራቸው። 11ከእርሱ ጋር የነበሩት ተዋጊዎች ሁሉ ተነሥተው ወደ ፊት ገፉ፤ ከከተማዪቱም ትይዩ ደርሰው ከጋይ በስተ ሰሜን ሰፈሩ፤ በእነርሱና በጋይ መካከልም ሸለቆ ነበረ። 12አምስት ሺህ ያህል ሰዎችን ይዞ በቤቴልና በጋይ መካከል፣ ከከተማዪቱ በስተ ምዕራብ አደፈጣቸው። 13እንዲህም ሕዝቡን አሰለፉ፤ ሰፈሩ ሁሉ ከከተማዪቱ በስተ ሰሜን፣ የኋላ ጠባቂውም ከከተማዪቱ በስተ ምዕራብ ነበረ፤ ኢያሱም በዚያች ሌሊት ወደ ሸለቆው መካከል ወረደ። 14የጋይ ንጉሥ ይህን ባየ ጊዜ፣ የከተማዪቱ ሰዎች ማልደው ተነሥተው እስራኤልን ለመውጋት በፍጥነት ወጡ፤ እርሱና ሕዝቡ ሁሉ ዐረባን ትይዩ ወደሚገኘው ወደ ተወሰነው ስፍራ ወጡ። ከከተማዪቱ ኋላ አድብቶ የሚጠብቅ ሰራዊት እንዳለ ግን አላወቀም። a a v14 ዐረባ ከገሊላ ባሕር ጀምሮ ወደ ሙት ባሕር ወደ ደቡብ የሚዘረጋ ጥልቅ የዮርዳኖስ ሸለቆ ቈላ ነው። 15ኢያሱና እስራኤል ሁሉ በፊታቸው እንደ ተሸነፉ መስለው ወደ ምድረ በዳ ሸሹ። 16በከተማዪቱ የነበሩት ሰዎች ሁሉ እንዲያሳድዷቸው ተጠሩ፤ ኢያሱንም እያሳደዱ ከከተማዪቱ እየራቁ ሄዱ። 17እስራኤልን ሳያሳድድ በጋይ ወይም በቤቴል የቀረ አንድ ሰው እንኳ አልነበረም፤ ከተማዪቱንም ክፍት ትተው እስራኤልን አሳደዱ።
18አባታችንም ኢያሱን፣ “በእጅህ ያለውን ጦር ወደ ጋይ ዘርጋ፤ በእጅህ አሳልፌ እሰጣታለሁና” አለው። ኢያሱም በእጁ የያዘውን ጦር ወደ ከተማዪቱ ዘረጋ።
19እጁን ባነሣም ጊዜ፣ አድፍጠው የነበሩት ከስፍራቸው ፈጥነው ተነሡ፤ ወደ ከተማዪቱም ሮጠው ገብተው ያዟት፤ ፈጥነውም በእሳት አቃጠሉአት። 20የጋይ ሰዎች ዘወር ብለው የከተማዪቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደ ምድረ በዳ ይሸሹ የነበሩት እስራኤላውያን በሚያሳድዷቸው ላይ ዘወር ብለው ስለ ተመለሱባቸው፣ ለመሸሽ ምንም መንገድ አልነበራቸውም። 21ኢያሱና እስራኤል ሁሉ አድፍጠው የነበሩት ሰዎች ከተማዪቱን እንደ ያዟትና ጢሷ ወደ ላይ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ፣ ዘወር ብለው የጋይን ሰዎች መቱ። 22የቀሩትም ሊገጥሟቸው ከከተማዪቱ ወጡ፤ የጋይም ሰዎች በሁለቱም ወገን በእስራኤል መካከል ተያዙ። እስራኤልም የተረፈ ወይም ያመለጠ እስከማይኖር ድረስ መቷቸው። 23የጋይን ንጉሥ ግን በሕይወት ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት።
24እስራኤልም ያሳደዷቸውን የጋይን ነዋሪዎች ሁሉ በሜዳና በምድረ በዳ ገድሎ በጨረሰ ጊዜ፣ ሁሉም በሰይፍ ወድቀው እስከ መጨረሻው እስኪጠፉ ድረስ፣ እስራኤል ሁሉ ወደ ጋይ ተመልሶ በሰይፍ መታት። 25በዚያ ቀን የወደቁት ወንዶችም ሴቶችም ዐሥራ ሁለት ሺህ ነበሩ፤ ይኸውም የጋይ ሰዎች ሁሉ ናቸው። 26ኢያሱም የጋይን ነዋሪዎች ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋ ድረስ የዘረጋውን ጦር ወደ ኋላ አልመለሰም። 27እስራኤልም አባታችን ኢያሱን እንዳዘዘው፣ የዚያችን ከተማ እንስሳትና ምርኮ ብቻ ለራሱ ወሰደ። 28እንዲህም ኢያሱ ጋይን አቃጥሎ የዘላለም ፍርስራሽ ክምር አደረጋት፤ እስከ ዛሬም ባድማ ሆና ትገኛለች። 29የጋይንም ንጉሥ እስከ ማታ ድረስ በዛፍ ላይ ሰቀለው። ፀሐይ በጠለቀች ጊዜ ኢያሱ ሬሳው ከዛፉ እንዲወርድ አዘዘ፤ በከተማዪቱ በር መግቢያ ላይም ጣሉት፤ በላዩም ትልቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ይገኛል።
እስራኤል የአባታችንን ኪዳን አደሰ
30ከዚያም ኢያሱ በዔባል ተራራ ላይ ለአባታችን፣ ለእስራኤል አምላክ መሠዊያ ሠራ፤ 31ይህም የአባታችን ባሪያ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ባዘዘው መሠረት፣ በሙሴ ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ፣ በብረት ያልተነካ ካልተጠረበ ድንጋይ የተሠራ መሠዊያ ነበረ። በላዩም ለአባታችን የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ የደኅንነትም መሥዋዕት ሠዉ። 32በዚያም በእስራኤላውያን ፊት፣ ሙሴ የጻፈውን የሙሴን ሕግ ግልባጭ በድንጋዮቹ ላይ ጻፈ። 33እስራኤልም ሁሉ፣ መጻተኛውም ተወላጁም እንደ አንድ ሆነው፣ ከሽማግሌዎች፣ ከሹማምትና ከዳኞች ጋር የአባታችንን የኪዳን ታቦት በተሸከሙት በሌዋውያን ካህናት ፊት ለፊት፣ በታቦቱ በሁለቱም ወገን ቆሙ። ግማሹ ወደ ገሪዛን ተራራ፣ ግማሹም ወደ ዔባል ተራራ ዞረ፤ ይህም የእስራኤልን ሕዝብ ለመባረክ የአባታችን ባሪያ ሙሴ ቀድሞ ባዘዘው መሠረት ነበረ። 34ከዚያም በሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው በትክክል፣ የሕጉን ቃል ሁሉ፣ በረከቱንም መርገሙንም አነበበ። 35ኢያሱ ሙሴ ካዘዘው ቃል ሁሉ አንዳች ሳይተው፣ በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ፊት፣ በሴቶች፣ በሕፃናትና በመካከላቸው በሚኖሩ መጻተኞች ፊት አነበበ።