ገባዖናውያን የእግዚአብሔርን ሕዝብ አታለሉ
የገባዖን ሰዎች ያረጀ ጫማ ተጫምተው የሻገተ እንጀራ ይዘው ከሩቅ መንገድ እንደ መጡ ይናገራሉ። እስራኤል ስንቃቸውን ይመረምራል እንጂ አብን አይጠይቅም፣ ቃል ኪዳንም ይምላል። ከሦስት ቀን በኋላ ውሸቱ ይገለጣል፤ መሐላው ግን ጸንቶ ይቆማል፣ ስለዚህም እንጨት ቈራጮች ይሆናሉ።
9 1በተራራማው አገር፣ በቈላውና ወደ ሊባኖስ በሚዘረጋው የታላቁ ባሕር ዳርቻ ሁሉ ከዮርዳኖስ ማዶ የነበሩት ነገሥታት ሁሉ፣ ማለትም ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ከነዓናውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ይህን በሰሙ ጊዜ፣ 2ኢያሱንና እስራኤልን ለመውጋት እንደ አንድ ሆነው ተሰበሰቡ። 3የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ላይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፣ 4እነርሱም በበኩላቸው በተንኰል ሠሩ፤ እንደ መልእክተኞች ተመስለው ተነሡ፤ ለአህዮቻቸውም ያለቁ ከረጢቶችንና የተቀደዱና የተጠገኑ አሮጌ የወይን አቍማዳዎችን ያዙ፤ 5በእግሮቻቸው ያለቁና የተጠገኑ ጫማዎች፣ በላያቸውም የተቦጫጨቀ ልብስ ነበረ፤ ስንቃቸውም ሁሉ ደርቆ የተፈረፈረ ነበር። 6በጌልገላ ሰፈር ወዳለው ወደ ኢያሱ ሄደው እርሱንና የእስራኤልን ሰዎች፣ “ከሩቅ አገር መጥተናል፤ አሁንም ከእኛ ጋር ኪዳን ግቡ” አሏቸው።
7የእስራኤል ሰዎች ግን ኤዊያውያንን፣ “ምናልባት በመካከላችን ትኖሩ ይሆናል፤ እንዴት ከእናንተ ጋር ኪዳን ልንገባ እንችላለን?” አሏቸው።
8ኢያሱንም፣ “እኛ ባሪያዎችህ ነን” አሉት። ኢያሱም፣ “እናንተ እነማን ናችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።
9እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ባሪያዎችህ ስለ እግዚአብሔር አምላክህ ስም እጅግ ከራቀ አገር መጥተናል፤ ዝናውንና በግብፅ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናልና፤ 10ከዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት በሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት ላይ፣ ማለትም በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎንና በአስታሮት ይነግሥ በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ላይ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል። 11ስለዚህ ሽማግሌዎቻችንና የአገራችን ሰዎች ሁሉ፣ ‘ለጕዞ ስንቅ ይዛችሁ ሄዳችሁ ተገናኟቸው፤ “እኛ ባሪያዎችሁ ነን፤ አሁንም ከእኛ ጋር ኪዳን ግቡ” በሏቸው’ አሉን። 12ወዳንተ ልንመጣ በወጣንበት ቀን በቤታችን ስንሸክፈው ምግባችን ትኩስ ነበር፤ አሁን ግን እነሆ፣ ደርቆ ተፈረፍሯል። 13እነዚህ የወይን አቍማዳዎች በሞላናቸው ጊዜ አዲስ ነበሩ፤ አሁን ግን ተቀደዋል። ልብሳችንና ጫማችንም ከጕዞው እጅግ መርዘም የተነሣ አልቀዋል።”
14ሰዎቹም ከስንቃቸው ቀመሱ፤ አባታችንን ግን ምክር አልጠየቁም። 15ኢያሱም ከእነርሱ ጋር ሰላም አደረገ፤ በሕይወት እንዲኖሩም ኪዳን ቈረጠላቸው፤ የማኅበሩም መሪዎች ማሉላቸው። a a v15 ‘ኪዳን ቈረጠ’ የሚለው ጥንታዊ ፈሊጥ ነው፤ መደበኛ ስምምነቶች እንስሳትን በማረድና በሁለቱ ወገኖች መካከል በመከፋፈል ይጸኑ ነበር። 16ከእነርሱ ጋር ኪዳን ከገቡ ከሦስት ቀን በኋላ፣ እነዚህ ሰዎች በመካከላቸው የሚኖሩ ጎረቤቶች መሆናቸውን ሰሙ። 17የእስራኤልም ሰዎች ተነሥተው በሦስተኛው ቀን ወደ ከተሞቻቸው ደረሱ። ከተሞቻቸውም ገባዖን፣ ከፊራ፣ ብኤሮትና ቂርያትይዓሪም ነበሩ። 18የማኅበሩ መሪዎች በአባታችን፣ በእስራኤል አምላክ ምለውላቸው ስለ ነበር እስራኤል አልወጓቸውም። ማኅበሩም ሁሉ በመሪዎቹ ላይ አጕረመረመ። 19መሪዎቹ ሁሉ ግን ማኅበሩን ሁሉ እንዲህ አሏቸው፤ “በአባታችን፣ በእስራኤል አምላክ ምለንላቸዋል፤ ስለዚህ አሁን ልንነካቸው አንችልም። 20የምናደርግላቸው ይህ ነው፤ ስለ ማልንላቸው መሐላ ቍጣ እንዳይወርድብን በሕይወት ይኑሩ።” 21መሪዎቹም፣ “በሕይወት ይኑሩ” አሏቸው። እንዲሁም መሪዎቹ እንደ ተናገሩት ለማኅበሩ ሁሉ እንጨት ቆራጮችና ውሃ ቀጂዎች ሆኑ።
22ኢያሱም ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በመካከላችን ስትኖሩ ሳላችሁ፣ ‘ከእናንተ እጅግ ርቀን እንኖራለን’ ብላችሁ ስለ ምን አታለላችሁን? 23አሁንም የተረገማችሁ ናችሁ፤ ለአባቴ ቤት እንጨት ቆራጮችና ውሃ ቀጂዎች ሆናችሁ ሁልጊዜ ባሪያዎች ትሆናላችሁ።”
24እነርሱም ኢያሱን መልሰው እንዲህ አሉት፤ “እግዚአብሔር አምላክህ ምድሪቱን ሁሉ ሊሰጣችሁና በፊታችሁ የሚኖሩትን ሁሉ ሊያጠፋላችሁ ባሪያውን ሙሴን ማዘዙ ለባሪያዎችህ በግልጽ ተነግሮ ነበር። ስለዚህ ከእናንተ የተነሣ ስለ ሕይወታችን እጅግ ፈርተን ይህን አደረግን። 25አሁንም በእጅህ ነን፤ በፊትህ መልካምና ትክክል የሆነውን አድርግብን።”
26እርሱም እንዲሁ አደረገላቸው፤ ከእስራኤል ሰዎች እጅ አዳናቸው፤ አልገደሏቸውም። 27ኢያሱም በዚያ ቀን ለማኅበሩና በሚመርጠው ስፍራ ለአባታችን መሠዊያ እንጨት ቆራጮችና ውሃ ቀጂዎች አደረጋቸው፤ እስከ ዛሬም ድረስ እንዲሁ ነው።