አባታችን ፀሐይን ያስቆማል
አምስት ነገሥታት ገባዖንን ስለ ከዳቻቸው ይወጓታል፤ ኢያሱም ያታለሉትን ሕዝብ ለመከላከል ሌሊቱን ሁሉ ይገሠግሣል። የአብ የበረዶ ድንጋይ ከሰይፍ ይልቅ ብዙ ይገድላል፣ ፀሐይም ቆማ ትቀራለች። አምስቱ በዋሻ ውስጥ ይገኛሉ፣ የደቡብ ከተሞችም በፍጥነት ይያዛሉ።
10 1የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒ ጼዴቅ፣ ኢያሱ ጋይን ይዞ ፈጽሞ እንዳጠፋት፣ ኢያሪኮንና ንጉሧን እንዳደረገ ሁሉ ጋይንና ንጉሧን እንዳደረገ፣ የገባዖንም ሰዎች ከእስራኤል ጋራ ዕርቅ አድርገው በመካከላቸው እንደ ተቀመጡ ሰማ። 2ገባዖን እንደ አንዷ የንጉሥ ከተማ ታላቅ ከተማ ስለ ነበረች፣ ከጋይም ስለምትበልጥ፣ ሰዎቿም ሁሉ ተዋጊዎች ስለ ነበሩ የኢየሩሳሌም ሰዎች እጅግ ፈሩ። 3ስለዚህ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒ ጼዴቅ ወደ ኬብሮን ንጉሥ ወደ ሆሃም፣ ወደ ያርሙት ንጉሥ ወደ ጲራም፣ ወደ ለኪስ ንጉሥ ወደ ያፊያ፣ ወደ ዔግሎንም ንጉሥ ወደ ዴቢር እንዲህ ሲል ላከ፤ 4“ገባዖን ከኢያሱና ከእስራኤል ሕዝብ ጋራ ዕርቅ አድርጋለችና ወደ እኔ ውጡ፤ እርዱኝም፤ ገባዖንንም እንውጋ።” 5ከዚያም አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት፣ የኢየሩሳሌም፣ የኬብሮን፣ የያርሙት፣ የለኪስና የዔግሎን ነገሥታት ተባብረው ከሠራዊታቸው ሁሉ ጋራ ወጡ፤ በገባዖን ላይ ሰፈሩ፤ ተዋጓትም። 6የገባዖን ሰዎች ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ወደ ኢያሱ እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ፤ “አገልጋዮችህን አትተዋቸው፤ ፈጥነህ መጥተህ አድነን፤ እርዳን፤ በተራራማው አገር ያሉ የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ ተባብረው ተነሥተውብናል።”
7ስለዚህ ኢያሱ ከተዋጊዎቹ ሁሉ ጋራ፣ ከኀያላን ጦረኞቹ ጋራ ከጌልገላ ወጣ።
8አባታችንም ኢያሱን፣ “አትፍራቸው፤ በእጅህ አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁና፤ ከእነርሱ አንዱም በፊትህ አይቆምም” አለው።
9ኢያሱም ሌሊቱን ሙሉ ከጌልገላ ወጥቶ ሄዶ ድንገት ወረደባቸው። 10አባታችንም በእስራኤል ፊት ደንጋጤ ላከባቸው፤ በገባዖንም በታላቅ መቅሠፍት መታቸው፤ ወደ ቤትኆሮን በሚወጣው መንገድ አሳደዳቸው፤ እስከ አዜቃና እስከ መቄዳ ድረስም ፈጃቸው። 11በእስራኤል ፊት በቤትኆሮን ቍልቍለት ሲሸሹ፣ አባታችን እስከ አዜቃ ድረስ ከሰማይ ታላላቅ ድንጋዮችን ጣለባቸው፤ ሞቱም። ከበረዶው ድንጋይ የተነሣ የሞቱት፣ የእስራኤል ሕዝብ በሰይፍ ከገደሉት ይበዛሉ።
12ከዚያም አባታችን አሞራውያንን ለእስራኤል ሕዝብ አሳልፎ በሰጠበት ቀን ኢያሱ ለአባታችን ተናገረ፤ በመላው እስራኤልም ፊት እንዲህ አለ፤ “ፀሐይ ሆይ፣ በገባዖን ላይ ቁሚ፤ ጨረቃም ሆይ፣ በአያሎን ሸለቆ ላይ።” 13ፀሐይም ቆመ፤ ሕዝቡም በጠላቶቹ ላይ በቀል እስኪፈጽም ድረስ ጨረቃ ዐረፈ። ይህ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይ በሰማይ መካከል ቆመ፤ ሊጠልቅም ወደ አንድ ሙሉ ቀን ያህል አልቸኰለም። a a v13 የያሻር መጽሐፍ የጥንት የዕብራውያን የግጥሞችና የመዝሙሮች ስብስብ ነበር፤ አሁን ጠፍቷል። 14አባታችን የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚህ ያለ ቀን ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ኖሮ አያውቅም፤ አባታችን ስለ እስራኤል ተዋግቷልና።
15ከዚያም ኢያሱ ከእርሱም ጋራ የነበሩት እስራኤል ሁሉ ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ተመለሱ።
አምስቱ ነገሥታት ተዋረዱ
16እነዚህ አምስቱ ነገሥታት ግን ሸሽተው በመቄዳ ባለው ዋሻ ውስጥ ተሸሽገው ነበር። 17ኢያሱም፣ “አምስቱ ነገሥታት በመቄዳ ባለው ዋሻ ውስጥ ተሸሽገው ተገኝተዋል” ተብሎ ተነገረው።
18ኢያሱም፣ “በዋሻው አፍ ላይ ታላላቅ ድንጋዮችን አንከባልሉ፤ እንዲጠብቋቸውም ሰዎችን በአጠገቡ አቁሙ። 19እናንተ ግን በዚያ አትቈዩ፤ ጠላቶቻችሁን አሳድዱ፤ ከኋላቸውም ምቷቸው፤ ወደ ከተሞቻቸው እንዲደርሱ አትፍቀዱ፤ አባታችሁ በእጃችሁ ሰጥቷቸዋልና” አለ።
20ኢያሱና የእስራኤል ሕዝብ በታላቅ መቅሠፍት መተዋቸው፤ ፈጅተዋቸውም፤ ሆኖም ጥቂት ተራፊዎች ወደ ተመሸጉ ከተሞች አመለጡ። 21ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ መቄዳ ወዳለው ሰፈር ወደ ኢያሱ በሰላም ተመለሱ፤ በማንኛውም እስራኤላዊ ላይ አንዲትም ቃል ለመናገር የደፈረ አልነበረም። 22ከዚያም ኢያሱ፣ “የዋሻውን አፍ ክፈቱ፤ እነዚያንም አምስቱን ነገሥታት ወደ እኔ አውጡልኝ” አለ። 23እነርሱም አምስቱን ነገሥታት ከዋሻው ወደ እርሱ አወጡ፤ የኢየሩሳሌምን፣ የኬብሮንን፣ የያርሙትን፣ የለኪስንና የዔግሎንን ነገሥታት። 24እነዚህን ነገሥታት ወደ ኢያሱ ባወጧቸው ጊዜ የእስራኤልን ሰዎች ሁሉ ጠራ፤ ከእርሱም ጋራ የሄዱትን የጦር አለቆች፣ “ቅረቡ፤ እግሮቻችሁን በእነዚህ ነገሥታት ዐንገት ላይ አድርጉ” አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሮቻቸውን በዐንገታቸው ላይ አደረጉ።
25ኢያሱም፣ “አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ በርቱ፤ ጠንከሩም፤ አባታችን በምትዋጓቸው ጠላቶች ሁሉ ላይ የሚያደርገው ይህ ነው” አላቸው።
26ከዚያ በኋላ ኢያሱ ነገሥታቱን መታ፤ ገደላቸውም፤ በአምስት ዛፎችም ላይ ሰቀላቸው፤ እስከ ማታም ድረስ በዚያ ተሰቅለው ቈዩ። 27ፀሐይ በጠለቀች ጊዜ ኢያሱ ሬሳዎቻቸው ከዛፎቹ እንዲወርዱና ነገሥታቱ ተሸሽገውበት ወደ ነበረው ዋሻ እንዲጣሉ አዘዘ። በዋሻውም አፍ ላይ ታላላቅ ድንጋዮችን አኖሩ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ።
28በዚያም ቀን ኢያሱ መቄዳን ያዘ፤ እርሷንና ንጉሧን በሰይፍ መታ፤ በውስጧ ያለውንም ሰው ሁሉ አጠፋ፤ ተራፊም አላስቀረም። የኢያሪኮን ንጉሥ እንዳደረገ ሁሉ የመቄዳን ንጉሥ አደረገ።
አባታችን የደቡብ ከተሞችን ይሰጣል
29ከዚያም ኢያሱ ከእርሱም ጋራ የነበሩት እስራኤል ሁሉ ከመቄዳ ወደ ልብና ተሻገሩ፤ ልብናንም ተዋጉ። 30አባታችንም እርሷንና ንጉሧን ደግሞ ለእስራኤል አሳልፎ ሰጠ። ኢያሱም እርሷንና በውስጧ ያለውን ሰው ሁሉ በሰይፍ ስለት መታ፤ ተራፊም አላስቀረም። የኢያሪኮን ንጉሥ እንዳደረገ ሁሉ ንጉሧንም አደረገ።
31ከዚያም ኢያሱ ከእርሱም ጋራ የነበሩት እስራኤል ሁሉ ከልብና ወደ ለኪስ ተጓዙ፤ በእርሷም ላይ ሰፈሩ፤ ተዋጓትም። 32አባታችንም ለኪስን ለእስራኤል አሳልፎ ሰጠ፤ ኢያሱም በሁለተኛው ቀን ያዛት፤ ልብናን እንዳደረገ ሁሉ እርሷንና በውስጧ ያለውን ሁሉ በሰይፍ መታ። 33ከዚያም የጌዤር ንጉሥ ሆራም ለኪስን ሊረዳ ወጣ፤ ኢያሱ ግን እርሱንና ሕዝቡን መታ፤ ተራፊም አላስቀረም።
34ኢያሱ ከእርሱም ጋራ የነበሩት እስራኤል ሁሉ ከለኪስ ወደ ዔግሎን ተሻገሩ፤ በእርሷም ላይ ሰፈሩ፤ ተዋጓትም። 35በዚያም ቀን ያዟት፤ በሰይፍ ስለትም መቷት። ለኪስን እንዳደረገ ሁሉ በዚያ ቀን በውስጧ ያለውን ሰው ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ።
36ከዚያም ኢያሱ ከእስራኤል ሁሉ ጋራ ከዔግሎን ወደ ኬብሮን ወጣ፤ ተዋጋትም። 37ያዟትም፤ በሰይፍ ስለትም መቷት፤ ንጉሧን፣ ከተሞቿን ሁሉ፣ በውስጧ ያለውንም ሁሉ መቱ። ዔግሎንን እንዳደረገ ሁሉ ተራፊ አላስቀረም፤ እርሷንና በውስጧ ያለውን ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ።
38ከዚያም ኢያሱ ከእርሱም ጋራ የነበሩት እስራኤል ሁሉ ወደ ዴቢር ተመለሱ፤ ተዋጓትም። 39እርሷን፣ ንጉሧንና መንደሮቿን ሁሉ ያዘ፤ በሰይፍም መታቸው፤ በውስጧ ያለውንም ሰው ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ፤ ተራፊም አልቀረም። ለኬብሮንና ለልብና ከነንጉሧ እንዳደረገ ሁሉ ለዴቢርና ለንጉሧ አደረገ። 40ኢያሱም አገሩን ሁሉ፣ ተራራማውን አገር፣ ኔጌብን፣ ቈላውንና ተዳፋቱን፣ ነገሥታቸውንም ሁሉ መታ። ተራፊ አላስቀረም፤ የእስራኤል አምላክ አባታችን እንዳዘዘው እስትንፋስ ያለውን ሁሉ አጠፋ። 41ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ አንሥቶ እስከ ጋዛ ድረስ፣ የጎሳንንም አገር ሁሉ እስከ ገባዖን ድረስ መታቸው። 42ኢያሱ እነዚህን ነገሥታት ሁሉና አገራቸውን በአንድ ጊዜ ያዘ፤ የእስራኤል አምላክ አባታችን ስለ እስራኤል ተዋግቷልና። 43ከዚያም ኢያሱ ከእርሱም ጋራ የነበሩት እስራኤል ሁሉ ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ተመለሱ።