ፈጽሞ አለመርካት
ሰው ሀብት፣ ክብርና መቶ ልጆች ኖረውት ከእነዚህ በአንዱም እንዲደሰት ላይፈቀድለት ይችላል። ሰባኪው ከእርሱ ይልቅ ሞቶ የተወለደ ሕፃን የበለጠ ዕረፍት አለው ይላል። ምኞት ፈጽሞ አይጠግብም፤ ጥበብ ምንም ብልጫ አታስገኝም፤ ከዚያ በኋላ የሚሆነውንም ማንም አያውቅም።
6 1ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፤ በሰው ልጆችም ላይ እጅግ ይከብዳል፦ 2እግዚአብሔር ሀብትን፣ ብልጽግናንና ክብርን የሚሰጠው፣ ነፍሱ ከምትመኘውም ነገር ሁሉ ምንም የማይጐድልበት ሰው አለ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከዚህ እንዲበላ አይፈቅድለትም፤ በእርሱ ፈንታ መጻተኛ ይበላዋል። ይህ ከንቱ፣ የከፋ ደዌ ነው።
3አንድ ሰው መቶ ልጆችን ቢወልድ፣ ብዙ ዓመታትም ቢኖር፣ ዕድሜው ምንም ያህል ረጅም ቢሆን፣ ነፍሱ ግን በመልካም ነገር ካልረካች፣ እርሱም ባይቀበር፣ ጨንግፎ የተወለደ ልጅ ከእርሱ ይሻላል እላለሁ። 4በከንቱ ይመጣል፤ ወደ ጨለማም ይሄዳል፤ ስሙንም ጨለማ ይሸፍነዋል። 5ፀሐይን ፈጽሞ ባያይ፣ ምንም ባያውቅም እንኳ፣ ከዚያ ሰው ይልቅ ዕረፍት አለው። 6ሺህ ዓመት ሁለት እጥፍ ቢኖር እንኳ፣ መልካምን ነገር ፈጽሞ ሳይደሰትበት ቢቀር፣ ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ አይሄዱምን? 7የሰው ድካም ሁሉ ለአፉ ነው፤ ምኞቱ ግን ከቶ አይጠግብም። 8ጠቢቡ ከሰነፉ የሚበልጥበት ጥቅም ምንድን ነው? ድኻውስ በሰዎች ፊት እንዴት መመላለስ እንዳለበት በማወቁ ምን ያተርፋል? 9ዐይን የሚያየው ከምኞት መንከራተት ይሻላል። ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 10ያለው ሁሉ አስቀድሞ ስም ተሰጥቶታል፤ ሰውም ምን እንደ ሆነ ይታወቃል፤ ከእርሱ ከሚበረታም ጋር ሊከራከር አይችልም።
11ቃላት በበዙ ቍጥር ከንቱነቱ ይጨምራል፤ ይህስ ለማንም ምን ይጠቅማል? 12እንደ ጥላ በሚያልፈው በከንቱ ሕይወቱ ጥቂት ዘመን ውስጥ፣ ለሰው መልካም የሆነውን ማን ያውቃል? ከእርሱ በኋላ ከፀሐይ በታች ምን እንደሚሆን ለሰው ማን ሊነግረው ይችላል?