ምሕረት ፊቱን ይገታል
ምድሪቱን እንደሚያገኙ ነገር ግን የእርሱን መገኘት እንደማያገኙ ሲነገራቸው፣ ሕዝቡ አለቀሱ ጌጣቸውንም አወለቁ። ወዳጅ ከወዳጁ ጋር እንደሚነጋገር ከአብ ጋር ፊት ለፊት የሚነጋገረው ሙሴ ያለ እርሱ አንድ እርምጃ እንኳ ለመሄድ እምቢ አለ፤ ከዚያም ክብሩን ለማየት ለመነ፣ በዓለት ውስጥም ተሰወረ።
33 1አባታችን ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አንተና ከግብፅ ያወጣኸው ሕዝብ ከዚህ ተነሥታችሁ፣ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ‘ለዘርህ እሰጣታለሁ’ ብዬ ወደ ማልሁላት ምድር ውጡ። 2በፊትህም መልአክ እልካለሁ፤ ከነዓናውያንን፣ አሞራውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኄዋውያንንና ኢያቡሳውያንን አባርራለሁ። 3ወተትና ማር ወደምታፈስ ምድር ውጡ፤ ነገር ግን እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁና በመንገድ እንዳላጠፋችሁ እኔ በመካከላችሁ አልወጣም።”
4ሕዝቡም ይህን የሚያሳዝን ወሬ በሰሙ ጊዜ አዘኑ፤ ማንም ጌጡን አላጠለቀም።
5አባታችን ሙሴን እንዲህ ብሎት ነበርና፤ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፤ ‘እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፤ ለአንዲት ቅጽበት እንኳ በመካከላችሁ ብወጣ ኖሮ ባጠፋኋችሁ ነበር። አሁንም በእናንተ ላይ ምን እንደማደርግ እወስን ዘንድ ጌጣችሁን አውልቁ።’”
6ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ከኮሬብ ተራራ ጀምሮ ጌጣቸውን አወለቁ።
የመገናኛው ድንኳን
7ሙሴም ድንኳኑን ወስዶ ከሰፈሩ ውጭ፣ ከሰፈሩ ርቆ ይተክለው ነበር፤ የመገናኛውም ድንኳን ብሎ ጠራው። አባታችንን የሚሻ ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው የመገናኛ ድንኳን ይወጣ ነበር። 8ሙሴም ወደ ድንኳኑ በወጣ ጊዜ ሁሉ ሕዝቡ ሁሉ ተነሥተው እያንዳንዳቸው በየድንኳናቸው ደጃፍ ይቆሙ፣ ሙሴም እስኪገባ ድረስ ይከታተሉት ነበር። 9ሙሴም ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜ ሁሉ የደመናው ዐምድ ወርዶ በደጃፉ ይቆም፣ አባታችንም ከሙሴ ጋራ ይነጋገር ነበር። 10ሕዝቡም ሁሉ የደመናውን ዐምድ በድንኳኑ ደጃፍ ቆሞ ባዩ ጊዜ ተነሥተው እያንዳንዳቸው በየድንኳናቸው ደጃፍ ይሰግዱ ነበር። 11አባታችንም ሰው ከወዳጁ ጋራ እንደሚነጋገር ከሙሴ ጋራ ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር። ሙሴም ወደ ሰፈሩ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን ብላቴናው አገልጋዩ የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር። a a v11 “ፊት ለፊት” መነጋገር ማለት አባታችን እንደ ወዳጆች ከሙሴ ጋራ በቀጥታና በቅርበት ተነጋገረ ማለት ነው፤ ቍጥር 20 ማንም ሊያየው በሕይወት ሊተርፍ እንደማይችል የሚናገረውን የተገለጠ ፊቱን ሙሴ አየ ማለት አይደለም።
የአባታችን ፊት ከእኛ ጋራ
12ሙሴም አባታችንን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፣ ‘ይህን ሕዝብ አውጣ’ ትለኛለህ፤ ነገር ግን ከእኔ ጋራ የምትልከውን አላሳወቅኸኝም። ሆኖም ‘በስምህ ዐውቅሃለሁ፤ በፊቴም ሞገስ አግኝተሃል’ ብለሃል። 13አሁንም በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ አንተን ዐውቅ ዘንድና በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን እቀጥል ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ። ይህም ሕዝብ ወገንህ መሆኑን ዐስብ።”
14እርሱም፣ “ፊቴ ከአንተ ጋራ ይሄዳል፤ ዕረፍትም እሰጥሃለሁ” አለ።
15ሙሴም፣ “ፊትህ ከእኛ ጋራ የማይሄድ ከሆነ ከዚህ አታውጣን። 16እኔና ሕዝብህ በፊትህ ሞገስ ማግኘታችን በሌላ በምን ይታወቃል? እኔና ሕዝብህ በምድር ፊት ካሉ ሕዝቦች ሁሉ ተለይተን እንድንሆን አንተ ከእኛ ጋራ በመሄድህ አይደለምን?” አለው።
17አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በፊቴ ሞገስ አግኝተሃልና፣ በስምህም ዐውቅሃለሁና የጠየቅኸውን ይህን ነገር አደርጋለሁ።”
18ከዚያም ሙሴ፣ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ” አለ።
19እርሱም እንዲህ አለ፤ “በጎነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ ስሜንም በፊትህ አውጃለሁ። ለምምረው እምረዋለሁ፤ ለምራራውም እራራለታለሁ።” 20ነገር ግን፣ “ማንም አይቶኝ በሕይወት ሊኖር አይችልምና ፊቴን ልታይ አትችልም” አለ። 21አባታችንም እንዲህ አለ፤ “በእኔ አጠገብ ስፍራ አለ፤ አንተም በዐለቱ ላይ ትቆማለህ፤ 22ክብሬ ሲያልፍ በዐለቱ ንቃቃት ውስጥ አኖርሃለሁ፤ እስካልፍም ድረስ በእጄ እሸፍንሃለሁ። 23ከዚያም እጄን አነሣለሁ፤ አንተም ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።”