አሳፍ በጨለማ ውስጥ ይጮኻል
ለመዘምራን አለቃ፤ እንደ ይዱቱን፤ የአሳፍ መዝሙር።
አሳፍ መተኛትም መናገርም አይችልም፤ ሰዎች ለመጠየቅ የሚፈሩትን ይጠይቃል፤ የአብ ፍቅር አልቋልን? ቸርነትን ማድረግ ረስቷልን? ከትዝታው በቀር ምንም አይለወጥም። ሆን ብሎ ባሕሩን ያስታውሳል፤ በዚያ መንገዱ እውነተኛ ነበር፣ ዱካው ግን አይታይም ነበር።
77 1ወደ አባታችን በታላቅ ድምፅ እጮኻለሁ፤ እርሱ ይሰማኝ ዘንድ ድምፄ ወደ አባታችን ከፍ ይላል። 2በመከራዬ ቀን ጌታ አባታችንን ፈለግሁ፤ በሌሊት እጄ ተዘርግታ አልታከተችም፤ ነፍሴም መጽናናትን እምቢ አለች። 3አባታችንን አስባለሁ፣ አቃስታለሁም፤ አሰላስላለሁ፣ መንፈሴም ይደክማል።
4የዐይኔን ሽፋሽፍት ገልጠህ ያዝህ፤ ተጨንቄም መናገር አልቻልሁም። 5ጥንት የነበሩትን ዘመናት፣ ከብዙ ጊዜ በፊት ያለፉትንም ዓመታት አሰብሁ። 6በሌሊት መዝሙሬን አስታወስሁ፤ በልቤም አሰላሰልሁ፣ መንፈሴም እንዲህ ሲል መረመረ፦ 7“ጌታ አባታችን ለዘላለም ይጥላልን፣ ዳግመኛም ሞገስን አያሳይምን? 8የኪዳኑ ፍቅር ለዘላለም አብቅቶአልን? የገባው ቃልስ ለትውልድ ሁሉ አልቆአልን? 9አባታችን ሞገስ ማድረግን ረስቶአልን? በቍጣውስ ርኅራኄውን ከልክሎአልን?”
10ከዚያም እንዲህ አልሁ፤ “ልመናዬ ይህ ነው፦ የልዑል ቀኝ እጅ ዓመታት።” a a v10 ልመናው ልዑል በኀያል እጁ ለሕዝቡ በኀይል ይሠራ ወደ ነበረባቸው ያለፉት ዓመታት ነው። 11የአባታችንን ሥራ አስባለሁ፤ አዎን፣ የጥንቱን ተኣምራትህን አስታውሳለሁ። 12ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፣ ኀያል ሥራዎችህንም አስተነትናለሁ። 13አባታችን ሆይ፣ መንገድህ ቅዱስ ነው። እንደ አባታችን ታላቅ የሆነ አምላክ ማን ነው? 14ተኣምራትን የምታደርግ አባታችን አንተ ነህ፤ ኀይልህን በሕዝቦች መካከል ገለጥህ። 15በክንድህ ሕዝብህን ተቤዠህ፣ የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች።
16አባታችን ሆይ፣ ውሃዎች አዩህ፤ ውሃዎች አዩህ ተጨነቁም፤ በእውነት፣ ጥልቆች ተንቀጠቀጡ። 17ደመናት ውሃ አፈሰሱ፤ ሰማያት በነጐድጓድ አስተጋቡ፤ ፍላጾችህ በየአቅጣጫው ተብለጨለጩ። 18የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነፋስ ውስጥ አስተጋባ፤ መብረቆችህ ዓለምን አበሩ፤ ምድር ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም። 19መንገድህ በባሕር ውስጥ ነበር፣ ፈለግህም በታላላቅ ውሃዎች ውስጥ ነበር፤ ነገር ግን የእግርህ ፋና አልታየም። 20ሕዝብህን በሙሴና በአሮን እጅ እንደ መንጋ መራህ።