ለፊልጵስዩስ ቅዱሳን
ከእስር ቤት የተጻፈ የደስታ መልእክት፤ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ በጌታ ደስ እንዲላትና የክርስቶስ አሳብ እንዲኖራት ያሳስባል።
1 1የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋዮች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ፤ በፊልጵስዩስ ለሚገኙ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉ ቅዱሳን ሁሉ፣ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር፦ 2ከአባታችንና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ስለ ወንጌል አጋሮች ምስጋና
3ባስታወስኋችሁ ጊዜ ሁሉ አባቴን አመሰግናለሁ፤ 4ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ ነው፤ 5ይህም ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በወንጌል ባላችሁ ኅብረት ምክንያት ነው። 6ይህንኑ ነገር እርግጠኛ ነኝ፤ በእናንተ መልካሙን ሥራ የጀመረው እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ይፈጽመዋል። 7ስለ እናንተ እንዲህ ማሰቤ ተገቢ ነው፤ በልቤ ይዤአችኋለሁና። ሁላችሁም በሰንሰለቴ፣ ወንጌልንም በመከላከልና በማጽናት፣ በጸጋ ከእኔ ጋር ተካፋዮች ናችሁ። 8ሁላችሁንም በክርስቶስ ኢየሱስ ጥልቅ ፍቅር እንዴት እንደምናፍቃችሁ አባታችን ምስክሬ ነውና።
9ጸሎቴም ይህ ነው፤ ፍቅራችሁ በዕውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ አብዝቶ እንዲበዛ፤ 10ይህም የሚበልጠውን ነገር ለይታችሁ ማወቅ እንድትችሉ፣ እስከ ክርስቶስ ቀን ድረስ ንጹሓንና ነውር የሌለባችሁ ሆናችሁ ትኖሩ ዘንድ ነው። 11በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ ተሞልታችሁ፣ ለአባታችን ክብርና ምስጋና ይሆን ዘንድ ነው።
ወንጌልን የሚያስፋፉ ሰንሰለቶች
12ወንድሞችና እኅቶች ሆይ፤ የደረሰብኝ ነገር ይልቁንም ወንጌልን ለማስፋፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ 13ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የታሰርሁ መሆኔ በመላው የቤተ መንግሥት ዘበኛና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ታወቀ። 14ከወንድሞችና ከእኅቶች አብዛኞቹ በሰንሰለቴ ምክንያት በጌታ ተረጋግተው፣ ቃሉን ያለ ፍርሃት ለመናገር አሁን ይበልጥ ይደፍራሉ። 15አንዳንዶች በእርግጥ ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ፤ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ይሰብካሉ። 16እነዚህ ወንጌልን ለመከላከል እንደ ተሾምሁ አውቀው ከፍቅር የተነሣ ያደርጉታል። 17እነዚያ ግን በሰንሰለቴ ላይ መከራ ሊጨምሩብኝ እያሰቡ፣ ከራስ ወዳድነት የተነሣ፣ ያለ ቅንነት ክርስቶስን ይሰብካሉ።
18ታዲያ ምን ይሆናል? በማስመሰል ቢሆን ወይም በእውነት፣ ክርስቶስ በማናቸውም መንገድ ይሰበካል፤ በዚህም ደስ ይለኛል። አዎን፣ ደስ መሰኘቴን እቀጥላለሁ። 19ይህም በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እርዳታ ለመዳኔ እንዲሆን ዐውቃለሁና። 20የጽኑ ናፍቆቴና ተስፋዬም ይህ ነው፤ በምንም ፈጽሞ አላፍርም፤ ነገር ግን ሁልጊዜ እንደ ሆነ አሁንም በፍጹም ድፍረት፣ በሕይወት ቢሆን ወይም በሞት፣ ክርስቶስ በሰውነቴ ይከብራል።
21ለእኔ መኖር ክርስቶስ፣ መሞትም ትርፍ ነውና። 22በሥጋ መኖርን ብቀጥል፣ ይህ ፍሬያማ ሥራ ይሆንልኛል። ነገር ግን የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። 23በሁለቱ መካከል ተወጥሬአለሁ፤ ልሄድና ከክርስቶስ ጋር ልሆን እመኛለሁ፤ ይህ እጅግ የተሻለ ነውና፤ 24ነገር ግን በሥጋ መቅረቴ ስለ እናንተ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። 25ይህንም ስለ ተረዳሁ፣ ለእናንተ እድገትና በእምነት ለሆነ ደስታችሁ፣ እንደምኖርና ከሁላችሁም ጋር እንደምቆይ ዐውቃለሁ፤ 26ይህም እንደ ገና ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ፣ በእኔ ምክንያት በክርስቶስ ኢየሱስ የምትመኩበት ትምክህታችሁ አብዝቶ እንዲበዛ ነው።
ለወንጌል በሚገባ መኖር
27ብቻ ለክርስቶስ ወንጌል በሚገባ ኑሩ፤ ይህም መጥቼ ባያችሁ ወይም ርቄ ብኖር፣ በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ እንደምትቆሙ፣ ለወንጌል እምነት በአንድ ልብ ሆናችሁ አብራችሁ እንደምትጋደሉ እንድሰማ ነው፤ 28በተቃዋሚዎቻችሁም ምንም ሳትፈሩ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋታቸው፣ ለእናንተ ግን የመዳናችሁ ምልክት ነው፤ ይህም ከአባታችን ነው። 29ስለ ክርስቶስ፣ በእርሱ ማመን ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ መከራ መቀበልም በጸጋ ተሰጥቷችኋልና፤ 30በእኔ ያያችሁትን፣ አሁንም እንዳለብኝ የምትሰሙትን ያንኑ ተጋድሎ እያሳለፋችሁ ነው።