ያንብቡ። ይቀበሉ። ይጠቁሙ።

♥ አስተያየቶች

ማቴዎስ 19

መጽሐፍ

ለጋብቻ የአባታችን ዕቅድ

ኢየሱስ ጋብቻን አብ በመጀመሪያ እንዴት እንደ ፈጠራቸው ላይ ይመሠርታል፤ ደቀ መዛሙርቱ ያባርሯቸው የነበሩትን ሕፃናት ይቀበላል፤ ጨዋና ባለጠጋ ለሆነ ጐበዝም ያለውን ሁሉ እንዲሸጥ ይነግረዋል። እርሱም እያዘነ ይሄዳል። በሰዎች ዘንድ የማይቻለው በአብ ዘንድ ይቻላል።

ምዕራፍ 19።

ኢየሱስ ይህን ቃል ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ገሊላን ትቶ በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ አገር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፤ በዚያም ፈወሳቸው።

ፈሪሳውያንም ሊፈትኑት መጥተው፣ “ሰው ሚስቱን በማናቸውም ምክንያት ቢፈታ ተፈቅዶለታልን?” ብለው ጠየቁት።

እርሱም መልሶ፣ “በመጀመሪያ የፈጠራቸው አባታችን ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? እንዲህም ብሎ፣ ‘ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋራ ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ያለውን? ስለዚህ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ አባታችን ያጣመረውን ማንም አይለያየው።”

እነርሱም፣ “ታዲያ ሙሴ ሰው የፍች ወረቀት ሰጥቶ እንዲያሰናብታት ለምን አዘዘ?” አሉት።

እርሱም፣ “ሙሴ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ የፈቀደላችሁ ልባችሁ ደንዳና ስለ ነበር ነው፤ ከመጀመሪያው ግን እንደዚህ አልነበረም። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሚስቱን ከዝሙት ኀጢአት በቀር ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።”

ደቀ መዛሙርቱም፣ “በባልና በሚስት መካከል ነገሩ እንደዚህ ከሆነ፣ አለማግባት ይሻላል” አሉት።

እርሱም፣ “ይህን ቃል ሁሉም ሰው አይቀበለውም፤ የተሰጣቸው ብቻ እንጂ። ከእናታቸው ማኅፀን እንደዚያ ሆነው የተወለዱ ጃንደረቦች አሉ፤ በሰዎች እንደዚያ የተደረጉ ጃንደረቦችም አሉ፤ ስለ አባታችን መንግሥት ራሳቸውን እንደዚያ ያደረጉ ጃንደረቦችም አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው።”

ኢየሱስ ሕፃናትን ተቀበለ

ከዚያም እጁን ጭኖ እንዲጸልይላቸው ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን የሚያመጡአቸውን ገሠጹአቸው።

ኢየሱስ ግን፣ “ሕፃናቱ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሉአቸው፤ የአባታችን መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና” አለ።

እጆቹንም ጭኖባቸው ከዚያ ሄደ።

የጎደለው አንድ ነገር

በዚህ ጊዜም አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት ምን መልካም ነገር ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው።

እርሱም፣ “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንዱ ብቻ ነው። ወደ ሕይወት መግባት ከፈለግህ ትእዛዛትን ጠብቅ” አለው።

“የትኞቹን?” ብሎ ጠየቀ። ኢየሱስም፣ “አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” አለ።

ጐበዙም፣ “ይህን ሁሉ ጠብቄአለሁ፤ ደግሞ ምን ይጐድለኛል?” አለው።

ኢየሱስም፣ “ፍጹም መሆን ከፈለግህ፣ ሂድና ያለህን ሽጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይም መዝገብ ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው።

ጐበዙም ይህን በሰማ ጊዜ ብዙ ሀብት ነበረውና እያዘነ ሄደ።

ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ ባለጠጋ ሰው ወደ አባታችን መንግሥት መግባት ይቸግረዋል። ደግሞ እላችኋለሁ፤ ባለጠጋ ወደ አባታችን መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል” አለ።

ደቀ መዛሙርቱም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደንቀው፣ “እንግዲያውስ ማን ሊድን ይችላል?” ብለው ጠየቁ።

ኢየሱስም ተመልክቶአቸው፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በአባታችን ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል” አለ።

ጴጥሮስም መልሶ፣ “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንግዲህ ምን እናገኛለን?” አለው።

ኢየሱስም፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፣ የተከተላችሁኝ እናንተ ደግሞ በዐሥራ ሁለት ዙፋኖች ተቀምጣችሁ የእስራኤልን ዐሥራ ሁለት ነገድ ትፈርዳላችሁ።

“ስለ ስሜ ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል። ነገር ግን ብዙ ፊተኞች የኋለኞች፣ ብዙ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።”

A young man reading the Father's Heart Bible (FHB) print edition in a coffee shop አሁን በኅትመት ይገኛል

አስተያየቶች

ሐሳብ፣ ጥያቄ፣ ወይም ይህ ምዕራፍ በልብዎ ያነሣሣው ቃል — እዚህ ያካፍሉ። እያንዳንዱ አስተያየት ስምዎን በአስተዋጽኦ አበርካቾች ግድግዳ ላይ ያሰፍራል።

ማንበብ፣ ማዳመጥ፣ መቅዳትና ማጋራት ለሁሉም ክፍት ነው — መለያ አያስፈልግም። አስተያየት መስጠት፣ ቁጥሮችን ማድመቅና የደረሱበትን ቦታ ምልክት ማድረግ ከነጻ መለያ ጋራ ይመጣሉ፤ እያንዳንዱ አስተያየትም ስምዎን በአስተዋጽኦ አበርካቾች ግድግዳ ላይ ያሰፍራል።

ቤተሰቡን ይቀላቀሉ — በነጻ ነው →
  • እስካሁን ምንም አስተያየት የለም። ድምፅዎን በማሰማት የመጀመሪያው ይሁኑ።