አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሷል
ኢየሱስ በፊታቸው በድምፅ ይጸልያል። ሥራው እንደ ተፈጸመ ለአብ ይነግረዋል፣ እነዚህ ሰዎች በአብ ስም እንዲጠበቁና ከክፉው እንዲጋረዱ ይለምናል፣ በኋላም ለሚያምኑ ሁሉ አንድ እንዲሆኑ ይጸልያል።
17 1ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ አሻቅቦ ተመለከተ፤ እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሷል። ልጁ አንተን እንዲያከብር ልጅህን አክብረው፤ a a v1 ዮሐንስ 17 ኢየሱስ ለአብ ካቀረባቸው ጸሎቶች ሁሉ ተመዝግቦ የሚገኘው ረዥሙ ነው፤ ይህም ከመስቀሉ በፊት በነበረችው ሌሊት የተነገረ ሆኖ፣ አባት፣ ቅዱስ አባት፣ ጻድቅ አባት ብሎ ለሚጠራው ልቡን የከፈተበት ነው። 2ለሰጠኸውም ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጥ፣ በሰዎች ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥተኸዋልና። 3የዘላለም ሕይወት ይህች ናት፤ አንተን ብቸኛውን እውነተኛ አባት፣ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው። 4እንዳደርግ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርሁህ። 5አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋራ በነበረኝ ክብር አሁን ከራስህ ጋራ አክብረኝ።
6ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁ። የአንተ ነበሩ፤ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል። 7አሁን የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ ዐውቀዋል፤ 8የሰጠኸኝን ቃላት ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉ፤ ከአንተ ዘንድ እንደ መጣሁ በእውነት ዐወቁ፤ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። 9እኔ ስለ እነርሱ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አይደለም፤ ነገር ግን ስለ ሰጠኸኝ ስለ እነርሱ ነው፤ የአንተ ናቸውና። 10የእኔ የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተውም የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ። 11ከእንግዲህ በዓለም የለሁም፤ እነርሱ ግን በዓለም ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፣ እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱ ደግሞ አንድ እንዲሆኑ፣ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው። 12ከእነርሱ ጋራ ሳለሁ፣ በሰጠኸኝ በስምህ ጠበቅኋቸው። ጠበቅኋቸው፤ መጽሐፉም ይፈጸም ዘንድ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ አንድ እንኳ አልጠፋም። b b v12 “የጥፋት ልጅ” የሚለው ኢየሱስን አሳልፎ ለሰጠው ለአስቆሮቱ ይሁዳ የተሰጠ ስም ነው። 13አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ደስታዬም በእነርሱ ዘንድ ተፈጽሞ እንዲገኝ ይህን በዓለም ሳለሁ እናገራለሁ። 14ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ እነርሱም ከዓለም ስላልሆኑ ዓለም ጠላቸው። 15ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም፤ ነገር ግን ከክፉው እንድትጠብቃቸው እለምናለሁ። 16እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ እነርሱ ከዓለም አይደሉም። 17በእውነት ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። 18አንተ ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ፣ እኔ ደግሞ እነርሱን ወደ ዓለም ላክኋቸው። 19እነርሱ ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ፣ ስለ እነርሱ ራሴን እቀድሳለሁ።
20ስለ እነዚህ ብቻ አይደለም የምለምነው፤ ነገር ግን በቃላቸው በእኔ ስለሚያምኑትም ጭምር ነው። 21አባት ሆይ፣ አንተ በእኔ እኔም በአንተ እንዳለሁ፣ እነርሱ ሁሉ አንድ ይሁኑ፤ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሁኑ፤ ዓለምም አንተ እንደ ላክኸኝ ያምን ዘንድ ነው። 22እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ፣ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። 23እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ ሆነህ፣ ፍጹም አንድ እንዲሆኑ፤ ዓለምም አንተ እንደ ላክኸኝና እኔን እንደ ወደድኸኝ እነርሱንም እንደ ወደድህ ያውቅ ዘንድ ነው። 24አባት ሆይ፣ የሰጠኸኝ እኔ ባለሁበት ከእኔ ጋራ እንዲሆኑ፣ ክብሬንም እንዲያዩ እወዳለሁ፤ ይህም ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝ ክብር ነው። 25ጻድቅ አባት ሆይ፣ ዓለም አያውቅህም፤ እኔ ግን ዐውቅሃለሁ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ ዐውቀዋል። 26ስምህን አስታወቅኋቸው፤ ወደ ፊትም አስታውቀዋለሁ፤ ይህም የወደድኸኝ ፍቅር በእነርሱ እንዲኖር እኔም በእነርሱ እንድኖር ነው።”