ኢዮብ እንደ ገና ተናገረ
ኢዮብ ያጣውን ያስታውሳል፤ በዙሪያው የነበሩትን ልጆቹን፣ በድንኳኑ ላይ የነበረውን የእግዚአብሔርን ወዳጅነት፣ የአንድ ከተማ ሁሉ አክብሮት። ለዕውሩ ዓይን፣ ለችግረኛውም አባት ነበር። ክብሩ ሳይጠፋ በጎጆው ውስጥ አርጅቶ እንደሚሞት ይጠብቅ ነበር።
29 1ኢዮብም እንደ ገና ተናገረ፤ እንዲህም አለ፦ 2“ምነው እንደ ቀደሙት ወራት፣ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ በነበረበት ዘመን እንደ ነበርሁ በሆንሁ፤ 3መብራቱ በራሴ ላይ ባበራ ጊዜ፣ በብርሃኑም በጨለማ ውስጥ በተመላለስሁ ጊዜ፤ 4በብርታቴ ወራት እንደ ነበርሁ፣ የእግዚአብሔር የቅርብ ወዳጅነት በድንኳኔ ላይ ባረፈ ጊዜ፤ a a v4 ኢዮብ ቀድሞ ያውቀው የነበረውን ቅርበት — የእግዚአብሔርን የቅርብ ወዳጅነት በቤቱ ላይ ለማረፉ — ይናፍቃል። የናፈቀው እግዚአብሔር ልቡ ከእርሱ ፈጽሞ ያልተለየ አብ መሆኑን ገና አያውቅም፤ መጽሐፉ ከመፈጸሙም በፊት ራሱ እንደሚያየው ገና አያውቅም። 5ሁሉን ቻዩ ገና ከእኔ ጋራ በነበረ ጊዜ፣ ልጆቼ ሁሉ በዙሪያዬ በነበሩ ጊዜ፤ 6አረማመዴ በእርጎ በታጠበ ጊዜ፣ ዐለቱም የዘይት ወንዞችን ባፈሰሰልኝ ጊዜ። 7ወደ ከተማዋ በር በወጣሁ ጊዜ፣ በአደባባዩም መቀመጫዬን በያዝሁ ጊዜ፣ 8ጐበዞች አይተውኝ ፈቀቅ አሉ፤ ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ፤ 9መሳፍንት ንግግራቸውን አገዱ፤ እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ጫኑ፤ 10የመኳንንት ድምፅ ጸጥ አለ፤ ምላሳቸውም በላንቃቸው ተጣበቀ። 11ጆሮ በሰማ ጊዜ ብፁዕ አለኝ፤ ዐይንም ባየ ጊዜ መሰከረልኝ፤ 12የጮኸውን ድኻ ስላዳንሁ፣ ረዳት የሌለውንም ድኻ አደግ ስላዳንሁ ነው። 13ሊጠፋ የተቃረበው ሰው በረከት በእኔ ላይ መጣ፤ የመበለቲቱንም ልብ በደስታ አስዘመርሁ። 14ጽድቅን ተጐናጸፍሁ፣ እርሱም አለበሰኝ፤ ፍርዴ እንደ ልብስና እንደ ጥምጥም ነበረ። 15ለዕውሩ ዐይን፣ ለአንካሳውም እግር ነበርሁ። 16ለችግረኞች አባት ነበርሁ፤ የማላውቀውንም ሰው ጕዳይ መረመርሁ። 17የክፉውን መንጋጋ ሰበርሁ፤ ምርኮውንም ከጥርሱ መካከል ነጠቅሁ። 18ስለዚህ፣ ‘በገዛ ጎጆዬ እሞታለሁ፤ ዘመኔንም እንደ አሸዋ አበዛለሁ’ ብዬ አሰብሁ። 19ሥሮቼ ወደ ውሃ ተዘረጉ፤ ጠልም ሌሊቱን ሙሉ በቅርንጫፎቼ ላይ ዐደረ። 20ክብሬ በውስጤ ትኩስ ሆኖ ኖረ፤ ቀስቴም በእጄ ዘወትር አዲስ ነበረ። 21ሰዎች ያዳምጡኝ ነበር፤ ይጠባበቁም ነበር፤ ለምክሬም ዝም አሉ። 22ከተናገርሁ በኋላ ሌላ አልተናገሩም፤ ቃሌም በእነርሱ ላይ በቀስታ ወረደ። 23ዝናምን እንደሚጠብቁ ጠበቁኝ፤ የጸደይንም ዝናብ እንደሚጠብቁ አፋቸውን ከፈቱ። 24በፈገግታ ባያቸው ጊዜ፣ ለማመን አስቸገራቸው፤ የፊቴንም ብርሃን አጥብቀው ያዙ። 25መንገዳቸውን መረጥሁ፤ አለቃቸውም ሆኜ ተቀመጥሁ፤ በሰራዊቱ መካከል እንዳለ ንጉሥ ኖርሁ፤ ሐዘንተኞችን እንደሚያጽናና ሰውም ነበርሁ።”