ማዕድን ቈፋሪ ሊያወጣው የማይችለው
ማዕድን አውጪዎች ጭልፊት ወዳላየው ስፍራ እየሄዱ ለብርና ለሰንፔር ዓለትን ይቦረቡራሉ። ጥበብ ግን ተቈፍራ አትወጣም፤ በገንዘብም አትገዛም። ጥልቁና ባሕሩ እዚህ የለችም ይላሉ። ስፍራዋን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ለሰውም፣ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ከክፉም ራቅ አለው።
28 1“ለብር ማዕድን ማውጫ፣ ወርቅም የሚነጥርበት ስፍራ በእርግጥ አለ። 2ብረት ከዐፈር ይወጣል፤ መዳብም ከዐለት ይቀልጣል። 3ሰው ለጨለማ ድንበር ያበጃል፤ በጭጋግና በጥልቅ ጥላ ውስጥ ያለውን ማዕድን እስከ መጨረሻው ዳርቻ ድረስ ይፈልጋል። 4ሰዎች ከሚኖሩበት ሩቅ፣ እግር ረግጦት በማያውቅ ስፍራ የማዕድን ጒድጓድ ይቈፍራል፤ በዚያም ከማንም ሰው ርቀው ተንጠልጥለው ይወዛወዛሉ። 5ምድር — ከእርሷ ምግብ ይገኛል፤ ከበታችዋ ግን በእሳት እንደ ተገለበጠ ይሆናል። 6ዐለቶቿ ሰንፔር ይይዛሉ፤ ዐፈሯም ወርቅ ይዟል። 7ይህ ዐዳኝ ወፍ የማያውቀው፣ የጭልፊትም ዐይን አይቶት የማያውቀው መንገድ ነው። 8ትዕቢተኛ አራዊት አልረገጡትም፤ አንበሳም በእርሱ ላይ አልተንጎማለለም። 9ሰው እጁን ወደ ጠጣር ዐለት ይዘረጋል፤ ተራሮችንም ከሥራቸው ይገለብጣል። 10በዐለቶች ውስጥ መተላለፊያዎችን ይቈርጣል፤ ዐይኑም እጅግ የከበረውን ነገር ሁሉ ያያል። 11የሚንጠባጠቡትን ምንጮች ይገድባል፤ የተሰወሩትንም ነገሮች ወደ ብርሃን ያወጣል።
12“ጥበብ ግን የት ትገኛለች? የማስተዋልስ ስፍራ የት ነው? 13ሰው ዋጋዋን አያውቅም፤ በሕያዋን ምድርም አትገኝም። 14ጥልቁ፣ ‘በእኔ ውስጥ የለችም’ ይላል፤ ባሕሩም፣ ‘ከእኔ ዘንድ የለችም’ ይላል። 15በጥሩ ወርቅ ልትገዛ አትችልም፤ ዋጋዋም በብር ሊመዘን አይችልም። 16በኦፊር ወርቅ ዋጋዋ ሊተመን አይችልም፤ በከበረ መረግድ ወይም በሰንፔርም አይሆንም። 17ወርቅና ብርሌ ሊተካከሏት አይችሉም፤ በጥሩ ወርቅ ዕቃዎችም ልትለወጥ አትችልም። 18ኮራልና ብርሌ ሊጠቀሱ አይገባም፤ የጥበብ ዋጋ ከሩቢ ይበልጣል። 19የኵሽ ቶጳዝዮን ሊተካከላት አይችልም፤ በጥሩ ወርቅም ዋጋዋ ሊተመን አይችልም።
20“እንግዲህ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች? የማስተዋልስ ስፍራ የት ነው? 21ከሕያዋን ሁሉ ዐይን ተሰውራለች፤ ከሰማይ ወፎችም እንኳ ተደብቃለች። 22ጥፋትና ሞት እንዲህ ይላሉ፤ ‘ዝናዋን በጆሮዋችን ሰምተናል።’
23“እግዚአብሔር ወደ እርሷ የሚወስደውን መንገድ ያስተውላል፤ ስፍራዋንም ያውቃል። 24እርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይመለከታልና፤ ከሰማያት በታች ያለውንም ሁሉ ያያል። 25ለነፋስ ክብደቱን ሲሰጥ፣ ውኆችንም በመስፈሪያ ሲለካ፣ 26ለዝናብ ሥርዐት ሲሠራ፣ ለመብረቅም መንገድ ሲያበጅ፣ 27ያን ጊዜ ጥበብን አይቶ ተናገራት፤ አጸናትም፤ መረመራትም።
28ለሰው ልጆችም እንዲህ አለ፤ ‘እግዚአብሔርን መፍራት፣ ጥበብ ያ ነው፤ ከክፋትም መራቅ ማስተዋል ነው።’”