ጺቅላግ ተዘረፈ፤ ቤተ ሰቦችም ተማረኩ
ዳዊት ወደ ጺቅላግ ሲመለስ ከተማዪቱ ተቃጥላ ቤተሰቦችም ሁሉ ተማርከው ተወስደው አገኘ፤ የገዛ ሰዎቹም ሊወግሩት ተነጋገሩ፤ እርሱ ግን በአባታችን ራሱን አበረታ። በራብ የደከመ አንድ ግብፃዊ ባሪያ ወደ ወራሪዎቹ መራው። ሁሉም ነገር ተመለሰ፤ ደክመው ወደ ኋላ የቀሩትም ሰዎች እኩል ተካፈሉ።
30 1ዳዊትና ሰዎቹ በሦስተኛው ቀን ጺቅላግ ደረሱ፤ አማሌቃውያን ኔጌብንና ጺቅላግን ወርረው ነበር፤ ጺቅላግንም አጥቅተው በእሳት አቃጠሉት፤ 2በዚያ የነበሩትን ሴቶችና ታናሽ ታላቁን ሁሉ ማረኩ፤ ማንንም አልገደሉም፤ ነገር ግን እያነዱ ወስደው በመንገዳቸው ሄዱ። 3ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ከተማዪቱ ሲደርሱ በእሳት ተቃጥላ ነበር፤ ሚስቶቻቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው ነበር። 4ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ የሚያለቅሱበት ኀይል እስኪያጡ ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። 5የዳዊት ሁለቱ ሚስቶች፣ የኢይዝራኤሏ አኪኖዓምና የቀርሜሎሱ የናባል መበለት አቢግያ ደግሞ ተማርከው ነበር። 6ሕዝቡ ሊወግሩት ይነጋገሩ ስለ ነበር ዳዊት እጅግ ተጨነቀ፤ እያንዳንዱ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ መራራ ኀዘን ነበረበትና። ዳዊት ግን በአባታችን ራሱን አበረታ።
7ዳዊትም የአኪሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን፣ “ኤፉዱን አምጣልኝ” አለው። አብያታርም ኤፉዱን ወደ ዳዊት አመጣ።
8ዳዊትም አባታችንን፣ “እነዚህን ወራሪዎች ላሳድዳቸውን? እደርስባቸዋለሁን?” ብሎ ጠየቀ። እርሱም፣ “አሳድዳቸው፤ በእርግጥ ትደርስባቸዋለህ፤ ሁሉንም ታድናለህ” አለው።
9ስለዚህ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ወደ ቤሶር ሸለቆ መጡ፤ አንዳንዶችም በዚያ ቀሩ። 10ዳዊት ከአራት መቶ ሰዎች ጋር አሳደደ፤ ሁለት መቶዎች ግን ቤሶርን ሸለቆ ለማቋረጥ ከመድከማቸው የተነሣ ወደ ኋላ ቀሩ። 11በሜዳ ላይ አንድ ግብፃዊ አግኝተው ወደ ዳዊት አመጡት፤ እንጀራና ውሃ ሰጡት። 12ከበለስ ጥፍጥፍ አንድ ቍራጭ፣ ሁለት የዘቢብ ዘለላም ሰጡት። በልቶም ኀይሉ ተመለሰለት፤ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም ነበርና። 13ዳዊትም፣ “አንተ የማን ነህ? ከወዴትስ ነህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለ፤ “እኔ ግብፃዊ ጎበዝ ነኝ፤ የአንድ አማሌቃዊ ባሪያ ነኝ። ከሦስት ቀን በፊት በታመምሁ ጊዜ ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ።
14የኪሬታውያንን ኔጌብ፣ የይሁዳን አገር፣ የካሌብንም ኔጌብ ወረርን፤ ጺቅላግንም በእሳት አቃጠልን።”
15ዳዊትም፣ “ወደዚህ ወራሪ ጭፍራ ታወርደኛለህን?” አለው። እርሱም፣ “እንዳትገድለኝ፣ በጌታዬም እጅ አሳልፈህ እንዳትሰጠኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ፤ እኔም ወደ እነርሱ አወርድሃለሁ” አለ።
16ግብፃዊውም ዳዊትን አወረደው፤ እነሆም፣ ከፍልስጥኤምና ከይሁዳ አገር በወሰዱት እጅግ ብዙ ምርኮ እየተደሰቱ፣ እየበሉና እየጠጡ በምድሪቱ ሁሉ ተበትነው ነበር። 17ዳዊትም ከመሸ ጀምሮ እስከ ማግስቱ ምሽት ድረስ መታቸው፤ በግመሎች ተቀምጠው ካመለጡ አራት መቶ ጎበዛዝት በቀር ማንም አላመለጠም። 18ዳዊትም አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ መለሰ፤ ሁለቱንም ሚስቶቹን አዳነ። 19ታናሽም ታላቅም፣ ወንዶችም ሴቶችም ልጆች፣ ምርኮም፣ ከወሰዱትም ሌላ ማንኛውም ነገር ምንም አልጎደለም፤ ዳዊት ሁሉን መልሶ አመጣ። 20ዳዊትም በጎቹንና ከብቶቹን ሁሉ ወሰደ፤ ሰዎቹም ከሌላው እንስሳ ፊት እያነዱ፣ “ይህ የዳዊት ምርኮ ነው” አሉ።
21ዳዊትም ሊከተሉት ደክሟቸው በቤሶር ሸለቆ ቀርተው ወደ ነበሩት ወደ ሁለት መቶ ሰዎች ደረሰ። እነርሱም ዳዊትንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሊቀበሉ ወጡ፤ እርሱም እየቀረበ ሰላምታ ሰጣቸው። 22ነገር ግን ከዳዊት ተከታዮች መካከል ክፉዎችና ምናምንቴዎች የሆኑ ሁሉ፣ “ከእኛ ጋር ስላልሄዱ ከመለስነው ምርኮ ምንም አንሰጣቸውም፤ ለእያንዳንዱ ሚስቱንና ልጆቹን ብቻ ይዞ ይሂድ” አሉ።
23ዳዊት ግን እንዲህ አለ፤ “ወንድሞቼ ሆይ፣ አባታችን በሰጠን ነገር እንዲህ አታድርጉ። እርሱ ጠብቆናል፤ የመጡብንንም ወራሪዎች በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል። 24በዚህ ነገር ማን ይሰማችኋል? ወደ ውጊያ የሚወርደውና ከዕቃው ዘንድ የሚቀረው እኩል ይካፈላሉ።” 25ከዚያ ቀን ጀምሮ ዳዊት ይህን ለእስራኤል ሥርዐትና ፍርድ አድርጎ አጸና፤ እስከ ዛሬም ድረስ ጸንቶ ይኖራል።
26ዳዊትም ወደ ጺቅላግ በደረሰ ጊዜ ለወዳጆቹ ለይሁዳ ሽማግሌዎች ከምርኮው ላከ፤ “እነሆ፣ ከአባታችን ጠላቶች ምርኮ ለእናንተ ስጦታ” አለ። 27በቤቴል፣ በኔጌብ ራሞት፣ በኢያቲርም ላሉት ላከ፤ 28በአሮዔር፣ በሲፍሞት፣ በኤሽታሞዕ ላሉት፤ 29በራካል፣ በኢያራሕሜላውያን ከተሞችና በቄናውያን ከተሞች ላሉት፤ 30በሖርማ፣ በቦር አሳን፣ በአታክ ላሉት፤ 31በኬብሮንና ዳዊትና ሰዎቹ ይዘዋወሩባቸው በነበሩት ስፍራዎች ሁሉ ላሉት ላከ።