አባቴ፣ ኀይሌ
ለመዘምራን አለቃ። እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉና ከሳኦል እጅ ባዳነው ቀን ይህን ቃል ለአባታችን የዘመረ፣ የአባታችን አገልጋይ የዳዊት መዝሙር።
ዳዊት ከሳኦል እጅ ከዳነ በኋላ ታሪኩን ሁሉ ይተርካል። በሞት ገመዶች ውስጥ እየሰጠመ ነበር፤ ጩኸቱም አብን በነፋስ ላይ፣ በጢስና በበረዶ ከሰማይ አወረደው፤ ከጥልቅ ውኃ አውጥቶም በከፍታዎች ላይ አቆመው።
18 1አባቴ ሆይ፣ ኀይሌ፣ እወድሃለሁ። 2አባቴ ዐለቴ፣ ምሽጌ፣ አዳኜም ነው፤ የምጠጋበት አባቴ ዐለቴ፣ ጋሻዬ፣ የመዳኔ ኀይል፣ መጠጊያዬ ነው። 3ምስጋና የሚገባውን አባቴን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ።
4የሞት እስራት ከበቡኝ፤ የጥፋት ጎርፍ አስጨነቀኝ። 5የሲኦል እስራት ተብትበውኝ ነበር፤ የሞት ወጥመድ ተጋረጠብኝ። 6በመከራዬ ጊዜ አባቴን ጠራሁ፤ ወደ አባቴም ለእርዳታ ጮኽሁ። ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ወደ እርሱ የቀረበው ጩኸቴም ጆሮው ደረሰ።
7ያን ጊዜ ምድር ተንገዳገደች፤ ተናወጠችም፤ የተራሮችም መሠረት ተንቀጠቀጠ፤ ተናወጠም፤ እርሱ ተቈጥቶ ነበርና። 8ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፤ ከአፉም የሚበላ እሳት ወጣ፤ የሚንበለበል ፍም ከእርሱ ነደደ። 9ሰማያትን ዝቅ አድርጎ ወረደ፤ ድቅድቅ ጨለማም ከእግሩ በታች ነበር። 10በኪሩብ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስ ክንፍ ላይ ሆኖ ተንሳፈፈ። 11ጨለማን መከለያው አደረገ፤ በዙሪያውም ድንኳኑ አደረገው—የጨለሙ ውሆችና የሰማይ ጥቅጥቅ ደመናዎች። 12በፊቱ ካለው ድምቀት የተነሣ ደመናዎቹ ጥሰው ወጡ፤ ከበረዶና ከእሳት ፍም ጋራ። 13አባቴም በሰማያት አንጐደጐደ፤ ልዑልም ድምፁን ከፍ አደረገ፤ ከበረዶና ከእሳት ፍም ጋራ። 14ፍላጻዎቹን ልኮ በተናቸው፤ ብዙ መብረቅ ወርውሮ አባረራቸው። 15ያን ጊዜ የባሕር መተላለፊያዎች ታዩ፤ በተግሣጽህ የዓለም መሠረቶች ተገለጡ፤ አባቴ፣ ከአፍንጫህ እስትንፋስ ነፋስ የተነሣ።
16ከላይ ሰዶ ያዘኝ፤ ከብዙ ውሆችም መዘዘኝ። 17ከኀያሉ ጠላቴ፣ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፤ ከእኔ ይልቅ በርትተው ነበርና። 18በመከራዬ ቀን ተጋፈጡኝ፤ አባቴ ግን ደጋፊዬ ነበር። 19ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤ በእኔ ደስ ስለ አለው አዳነኝ።
20አባቴ እንደ ጽድቄ አደረገልኝ፤ እንደ እጆቼ ንጽሕና ዋጋ ከፈለኝ። 21የአባቴን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ በክፋትም ከአባቴ ፈቀቅ አላልሁም። 22ፍርዶቹ ሁሉ በፊቴ ነበሩና፤ ሕጎቹንም ከእኔ አላራቅሁም። 23በፊቱ ነውር የሌለብኝ ነበርሁ፤ ራሴንም ከበደል ጠበቅሁ። 24ስለዚህ አባቴ እንደ ጽድቄ ዋጋ ከፈለኝ፤ በፊቱ እንዳለው የእጆቼ ንጽሕና።
25ከታማኝ ጋራ ታማኝ ሆነህ ትታያለህ፤ ነውር ከሌለበትም ጋራ ነውር የሌለብህ ሆነህ ትታያለህ፤ 26ከንጹሑ ጋራ ንጹሕ ሆነህ ትታያለህ፤ ከጠማማው ጋራ ግን ብልኀተኛ ሆነህ ትታያለህ። 27ትሑት ሕዝብን ታድናለህና፤ ትዕቢተኛ ዓይኖችን ግን ዝቅ ታደርጋለህ። 28መብራቴን የምታበራ አንተ ነህና፤ አባቴ ጨለማዬን ያበራል። 29በአንተ ሰራዊትን እወጋለሁና፤ በአባቴም ቅጥርን እዘልላለሁ።
30አባቴ—መንገዱ ፍጹም ነው፤ የአባቴ ቃል የተፈተነ ነው፤ በእርሱ ለሚጠጉ ሁሉ ጋሻ ነው። 31ከአባቴ በቀር አባታችን ማን ነው? ከአባታችንም በቀር ዐለት ማን ነው? 32በኀይል የሚያስታጥቀኝ አባቴ ነው፤ መንገዴንም ነውር የሌለበት ያደርጋል። 33እግሮቼን እንደ ዋላ እግር ያደርጋል፤ በከፍታ ቦታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል። 34እጆቼን ለሰልፍ ያሠለጥናል፤ ክንዶቼም የናስ ቀስት እንዲያጥፉ ያደርጋል። 35የመዳንህን ጋሻ ሰጠኸኝ፤ ቀኝህ ይደግፈኛል፤ ገርነትህም ከፍ አደረገኝ። 36ከእግሬ በታች ለእርምጃዬ ሰፊ ቦታ አደረግህ፤ እግሮቼም አይናወጡም።
37ጠላቶቼን አሳደድሁ፤ ደረስሁባቸውም፤ እስኪጠፉም ድረስ አልተመለስሁም። 38መነሣት እንዳይችሉ መታኋቸው፤ ከእግሮቼ በታችም ወደቁ። 39ለሰልፍ በኀይል አስታጠቅኸኝ፤ የተነሡብኝንም ከእግሮቼ በታች እንዲወድቁ አደረግህ። 40ጠላቶቼ ጀርባቸውን እንዲያዞሩልኝ አደረግህ፤ የሚጠሉኝንም አጠፋኋቸው። 41ለእርዳታ ጮኹ፤ የሚያድን ግን አልነበረም፤ ወደ አባቴ ጮኹ፤ እርሱ ግን አልመለሰላቸውም። 42በነፋስ ፊት እንደሚበን አቧራ አደቀቅኋቸው፤ እንደ መንገድ ጭቃም አፈሰስኋቸው። 43ከሕዝብ ጥል አዳንኸኝ፤ የአሕዛብ ራስ አደረግኸኝ፤ ያላወቅሁት ሕዝብ አሁን ያገለግለኛል። 44ስለ እኔ እንደ ሰሙ ይታዘዙኛል፤ መጻተኞችም እየተሸማቀቁ ወደ እኔ ይመጣሉ። 45መጻተኞች ይጠወልጋሉ፤ ከምሽጎቻቸውም እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ።
46አባቴ ሕያው ነው! ዐለቴ ይባረክ፤ የሚያድነኝም አባት ከፍ ከፍ ይበል፤ 47ፍትሕን የሚሰጠኝ፣ ሕዝቦችንም ከእኔ በታች የሚያስገዛ አባት፤ 48ከጠላቶቼ ያዳነኝ። አዎን፣ ከተነሡብኝ በላይ ከፍ አደረግኸኝ፤ ከዐመፀኛውም ሰው አዳንኸኝ። 49ስለዚህ አባቴ፣ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ።
50ለንጉሡ ታላቅ ድልን ይሰጣል፤ ለቀባውም የኪዳን ፍቅርን ያሳያል፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም።