የአባት ትእዛዛት፣ የልጅ ሕይወት
ለልጅ የተሰጠ ምክር፣ በአብዛኛው ስለ መታመን፦ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፣ አብን በገቢህ አክብር፣ ተግሣጹን አትጥላ። ከዚያም ዋጋዋ ከብር በላይ የሆነ ጥበብ፣ ስለ ጎረቤትም ቀጥተኛ ሕግጋት፣ ያለብህን ከነገ ይልቅ ዛሬ መክፈልን ጨምሮ።
3 1ልጄ ሆይ፣ ትምህርቴን አትርሳ፤ ልብህ ግን ትእዛዜን ይጠብቅ፤ 2እነርሱ የዕድሜን ርዝመት፣ የሕይወት ዘመናትንና ሰላምን ይጨምሩልሃልና። 3ምሕረትና ታማኝነት አይለዩህ፤ በአንገትህ ላይ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ላይ ጻፋቸው። 4እንዲህም በአባታችንና በሰዎች ፊት ሞገስንና መልካም ስምን ታገኛለህ።
5በፍጹም ልብህ በአባታችን ታመን፤ በራስህ ማስተዋልም አትደገፍ። 6በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።
7በራስህ ዐይን ጥበበኛ አትሁን፤ አባታችንን ፍራ፤ ከክፋትም ራቅ። 8ይህም ለሰውነትህ ፈውስን፣ ለዐጥንቶችህም እረፍትን ያመጣል።
9አባታችንን በሀብትህ፣ ከፍሬህም ሁሉ በበኵራት አክብረው፤ a a v9 በኵራት ከመከሩ ፊተኛውና ምርጡ ድርሻ ነበሩ፤ ከእርሱም ምንም ሳይውል አስቀድመው ለአባታችን ይቀርቡ ነበር። 10ያን ጊዜ ጐተራዎችህ በትርፍ ይሞላሉ፤ መጥመቂያዎችህም በአዲስ ወይን ይጐርፋሉ።
11ልጄ ሆይ፣ የአባታችንን ተግሣጽ አትናቅ፤ በዘለፋውም አትታክት፤ 12አባታችን ልቡ የሚወደውን ይገሥጻልና፤ አባት ደስ የሚለውን ልጁን እንደሚገሥጽ።
13ጥበብን የሚያገኝ፣ ማስተዋልንም የሚያተርፍ ሰው ብፁዕ ነው፤ 14ከእርስዋ የሚገኘው ትርፍ ከብር ይበልጣልና፤ ፍሬዋም ከወርቅ ይሻላል። 15ከዕንቍዎች ይልቅ ውድ ናት፤ የምትመኘው ሁሉ ከእርስዋ ጋራ ሊወዳደር አይችልም። 16ረጅም ዕድሜ በቀኝ እጅዋ ነው፤ ብልጥግናና ክብርም በግራ እጅዋ ናቸው። 17መንገዶችዋ ደስ የሚያሰኙ ናቸው፤ ጎዳናዎችዋም ሁሉ ሰላም ናቸው። 18ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፤ አጥብቀው የሚይዟትም ብፁዓን ይባላሉ።
19አባታችን በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና፤ 20በዕውቀቱ ጥልቆች ተከፈቱ፤ ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ።
21ልጄ ሆይ፣ እነዚህን ከዐይንህ አትለያቸው፤ ጤናማ ጥበብንና ልባምነትን ጠብቅ፤ 22ለነፍስህ ሕይወት፣ ለአንገትህም ጌጥ ይሆናሉ። 23ያን ጊዜ በመንገድህ ተማምነህ ትሄዳለህ፤ እግርህም አይሰናከልም። 24በተኛህ ጊዜ አትፈራም፤ ተኝተህም እንቅልፍህ ጣፋጭ ይሆናል። 25ድንገተኛ ድንጋጤን፣ በክፉዎች ላይ የሚመጣውንም ጥፋት አትፍራ፤ 26አባታችን አመኔታህ ይሆናልና፤ እግርህም እንዳይያዝ ይጠብቃል።
27ልታደርገው በእጅህ ኀይል ሳለ፣ መልካምን ለሚገባቸው ሰዎች አትከልክል። 28ከአንተ ጋራ ሳለ፣ ለባልንጀራህ፣ “ሂድና ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው። 29በባልንጀራህ ላይ ክፉ አታስብ፤ 30ክፉ ባላደረገብህ ጊዜ፣ ከማንም ሰው ጋራ ያለ ምክንያት አትጣላ።
31ዐመፀኛ ሰውን አትቅና፤ ከመንገዶቹም አንዱን እንኳ አትምረጥ፤ 32ጠማማ ሰው በአባታችን ዘንድ የተጠላ ነውና፤ ቅኖችን ግን ወደ ምሥጢሩ ያቀርባል። 33የአባታችን እርግማን በክፉ ሰው ቤት ላይ ነው፤ የጻድቃንን መኖሪያ ግን ይባርካል። 34ዘባቾችን ይዘብትባቸዋል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 35ጥበበኞች ክብርን ይወርሳሉ፤ ሰነፎች ግን ውርደትን ብቻ ያገኛሉ።