ሞትና ሕይወት በምላስ
ንግግርና ብቸኝነት። ቃላት ሞትን ወይም ሕይወትን የሚሸከሙ ጥልቅ ውኆች ናቸው፤ የሰነፍ አፍ የራሱ ወጥመድ ነው፤ ሳይሰሙ መመለስም ውርደት ነው። ጉዳዩን አስቀድሞ የሚያቀርብ እስኪጠየቅ ድረስ ትክክል እንደሚመስል፣ የተበደለ ወንድምም መመለሱ አስቸጋሪ እንደ ሆነ ያስተውላል።
18 1ራሱን የሚያገል ሰው የገዛ ምኞቱን ይከተላል፤ በጤናማ ጥበብ ሁሉ ላይም ይነሣል። 2ተላላ ሰው በማስተዋል ደስ አይለውም፤ የገዛ ሐሳቡን በመግለጥ እንጂ። 3ክፋት ሲመጣ፣ ንቀትም አብሮ ይመጣል፤ ከውርደትም ጋራ ነቀፋ ይመጣል። 4ከሰው አፍ የሚወጣ ቃል ጥልቅ ውሃ ነው፤ የጥበብ ምንጭ የሚፈስ ወንዝ ነው። 5ለክፉ ሰው አድልዎ ማሳየት፣ ለጻድቁም ፍርድ መንሣት መልካም አይደለም። 6የተላላ ሰው ከንፈር ጠብን ያመጣል፤ አፉም ድብደባን ይጋብዛል። 7የተላላ ሰው አፍ ጥፋቱ ነው፤ ከንፈሩም ለነፍሱ ወጥመድ ነው። 8የሐሜተኛ ቃል እንደ ጣፋጭ ጉርሻ ነው፤ ወደ ውስጠኛው ሆድም ጥልቅ ይወርዳል። 9በሥራው የሚዝል ሰው ለሚያጠፋ ሰው ወንድም ነው። 10የአባታችን ስም የጸና ግንብ ነው፤ ጻድቁ ወደ እርሱ ሮጦ ይጠበቃል። 11የሀብታም ሰው ሀብት የተመሸገ ከተማው ነው፤ በሐሳቡም እንደ ረጅም ቅጥር ነው። 12ከጥፋት በፊት የሰው ልብ ይታበያል፤ ትሕትና ግን ከክብር ይቀድማል። 13ሳይሰማ የሚመልስ ሰው፣ ይህ ሞኝነቱና ውርደቱ ነው። 14የሰው መንፈስ በበሽታው ጊዜ ይደግፈዋል፤ የተሰበረ መንፈስን ግን ማን ሊሸከመው ይችላል? 15አስተዋይ ልብ ዕውቀትን ያገኛል፤ የጥበበኛም ጆሮ ይፈልገዋል። 16የሰው ስጦታ መንገድ ይከፍትለታል፤ በታላላቅ ሰዎችም ፊት ያቀርበዋል። 17ነገሩን መጀመሪያ የሚያቀርብ ትክክል ይመስላል፤ ሌላው መጥቶ እስኪመረምረው ድረስ። 18ዕጣ መጣል ክርክርን ይፈታል፤ ኀያላን ተከራካሪዎችንም ይለያያል። 19የተከፋ ወንድም ከተመሸገ ከተማ ይልቅ ለማግባባት ይከብዳል፤ ክርክርም እንደ ምሽግ መወርወሪያ ነው። 20ከሰው አፍ ፍሬ ሆዱ ይጠግባል፤ በከንፈሩ ምርትም ይረካል። 21ሞትና ሕይወት በምላስ ኀይል ውስጥ ናቸው፤ ምላስን የሚወድዱም ፍሬዋን ይበላሉ። 22ሚስት የሚያገኝ መልካም ነገርን ያገኛል፤ ከአባታችንም ሞገስን ይቀበላል። 23ድኻ ሰው ምሕረትን ይለምናል፤ ሀብታም ግን በብርቱ ይመልሳል። 24ብዙ ባልንጀሮች ያሉት ሰው ወደ ጥፋት ሊመጣ ይችላል፤ ከወንድም ይልቅ ተጠግቶ የሚኖር ወዳጅ ግን አለ።