ለብንያም ተራፊዎች የተደረገ ምሕረት
እስራኤል ማንም ሴት ልጁን ለብንያማዊ እንዳይድር ስለ ማሉ፣ አንድ ነገድ እየጠፋ ነው ብለው በአብ ፊት ያለቅሳሉ፤ ጉዳቱንም በተጨማሪ ዓመፅ ይጠግኑታል፤ ለአራት መቶ ደናግሎቿ ሲሉ ኢያቢስ ገለዓድን ይጨፈጭፋሉ፤ የቀሩትም የሴሎን ዘፋኝ ልጃገረዶች አድፍጠው እንዲነጥቁ ይነገራቸዋል።
21 1የእስራኤል ሰዎች በምጽጳ፣ “ከእኛ አንዳችን ቢሆን ሴት ልጁን ለብንያም ሚስት አድርጎ አይሰጥም” ብለው ምለው ነበር። 2ሕዝቡም ወደ ቤቴል መጥተው እስከ ማታ ድረስ በአባታችን ፊት ተቀመጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አምርረው አለቀሱ። 3እንዲህም አሉ፤ “አባታችን ሆይ፤ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዲጐድል ይህ በእስራኤል ላይ ለምን ሆነ?”
4በማግሥቱ ሕዝቡ ማልደው ተነሥተው በዚያ መሠውያ ሠሩ፤ የሚቃጠልና የኅብረት መሥዋዕቶችንም አቀረቡ። 5የእስራኤልም ሰዎች፣ “ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ወደ ጉባኤው፣ ወደ አባታችን ያልወጣ ማን ነው?” ብለው ጠየቁ፤ ወደ ምጽጳ ወደ አባታችን ያልወጣ ሰው ፈጽሞ ይገደል ዘንድ ታላቅ መሐላ ምለው ነበርና። 6እስራኤላውያንም ስለ ወንድማቸው ስለ ብንያም አዘኑ፤ “ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ ተቈርጧል።” አሉ። 7“ሴቶች ልጆቻችንን እንዳንሰጣቸው በአባታችን ምለን ስለ ነበር፣ ለተረፉት እንዴት ሚስት ልናገኝ እንችላለን?” 8እንዲህም ብለው ጠየቁ፤ “ከእስራኤል ነገዶች ወደ ምጽጳ ወደ አባታችን ያልወጣ ማን ነው?” ከኢያቤስ ገለዓድ ወደ ሰፈሩ፣ ወደ ጉባኤው የመጣ አንድም አልነበረም። 9ሕዝቡ በተቈጠረ ጊዜ ከኢያቤስ ገለዓድ ነዋሪዎች አንድም በዚያ አልነበረምና። 10ጉባኤውም ከኀያላን ተዋጊዎቻቸው ዐሥራ ሁለት ሺሕ ወደዚያ ላከ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፤ “ሂዱ፤ የኢያቤስ ገለዓድን ነዋሪዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ጋር በሰይፍ ምቱ። 11የምታደርጉት ይህ ነው፤ ወንዱን ሁሉ፣ ከወንድ ጋር ተኝታ የምታውቅን ሴት ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ።” 12ከኢያቤስ ገለዓድ ነዋሪዎች መካከል ከወንድ ጋር ተኝተው የማያውቁ አራት መቶ ወጣት ደናግል አገኙ፤ በከነዓን ምድር ወደ ነበረው ወደ ሴሎ ሰፈር አመጧቸው።
13ከዚያም ማኅበሩ ሁሉ በሬሞን ዓለት ወዳሉት ብንያማውያን ልኮ ሰላምን አወጀላቸው። 14በዚያም ጊዜ ብንያም ተመለሰ፤ ከኢያቤስ ገለዓድ በሕይወት የተጠበቁትን ሴቶች ሰጧቸው፤ ነገር ግን ለሁሉ አልበቁአቸውም። 15አባታችን በእስራኤል ነገዶች መካከል ክፍተት አድርጎ ስለ ነበር ሕዝቡ ስለ ብንያም አዘኑ። 16የጉባኤውም ሽማግሌዎች፣ “የብንያም ሴቶች ጠፍተዋልና ለተረፉት እንዴት ሚስት እናገኝላቸዋለን?” አሉ። 17እንዲህም አሉ፤ “ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዳይደመሰስ ለብንያም ተራፊዎች ርስት ያስፈልጋቸዋል። 18እስራኤል፣ ‘ለብንያም ሚስት የሚሰጥ ሁሉ የተረገመ ይሁን’ ብሎ ምሎ ስለ ነበር፣ ሴቶች ልጆቻችንን ሚስት አድርገን ልንሰጣቸው አንችልም።” 19እንዲህም አሉ፤ “ከቤቴል በስተ ሰሜን፣ ከቤቴል ወደ ሴኬም ከሚወጣው መንገድ በስተ ምሥራቅ፣ ከለቦና በስተ ደቡብ ባለችው በሴሎ በየዓመቱ የአባታችን በዓል አለ።” 20ብንያማውያንንም፣ “ሂዱ፤ በወይን ተክል ቦታዎች ተደበቁ፤ 21ተመልከቱ፤ የሴሎ ወጣት ሴቶች ለዘፈን በወጡ ጊዜ ከወይኑ ተክል ቦታዎች ተወርውራችሁ ውጡ፤ እያንዳንዳችሁ ከሴሎ ወጣት ሴቶች ለራሳችሁ ሚስት ያዙ፤ ወደ ብንያም ምድርም ሂዱ። 22አባቶቻቸው ወይም ወንድሞቻቸው ሊከሱን ወደ እኛ በመጡ ጊዜ፣ ‘ስለ እኛ ብላችሁ ለእነርሱ ሞገስ አድርጉላቸው፤ በጦርነቱ ለእያንዳንዱ ሚስት አልማረክንላቸውምና፤ እናንተም ራሳችሁ ሚስት አልሰጣችኋቸውም፤ አለዚያማ አሁን በደለኞች በሆናችሁ ነበር’ እንላቸዋለን።”
23የብንያምም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ ከያዟቸው ዘፋኞች ለእያንዳንዳቸው አንዳንድ ሚስት ወሰዱ፤ ወደ ርስታቸውም ተመልሰው ከተሞቹን እንደ ገና ሠርተው በዚያ ኖሩ። 24በዚያም ጊዜ እስራኤላውያን እያንዳንዱ ወደ ነገዱና ወደ ወገኑ ከዚያ ወጡ፤ እያንዳንዱ ከዚያ ወደ ርስቱ ወጣ። 25በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በራሱ ዓይን ትክክል መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።