ኤሊሁ ለኢዮብ ተናገረ
ኤሊሁ እርሱም ደግሞ ጭቃ ብቻ እንደ ሆነና ሊፈራው እንደማይገባ ለኢዮብ ይነግረዋል። መልሱም እግዚአብሔር ሰውን ከጕድጓድ ለመመለስ በሕልምና በሕመም አልጋ ላይ በሥቃይ ይናገራል የሚል ነው። አማላጅም፣ ራራለት፤ ቤዛ አግኝቻለሁ ሊል ይችላል።
33 1“አሁን ግን፣ ኢዮብ ሆይ፣ ቃሌን ስማ፤ የምናገረውን ሁሉ አድምጥ። 2እነሆ፣ አፌን ከፍቻለሁ፤ ምላሴም በትናጋዬ ቃላትን ትቀርጻለች። 3ቃሌ ከቅን ልብ ይወጣል፤ ከንፈሮቼም የሚያውቁትን በቅንነት ይናገራሉ። 4የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፤ የሁሉን ቻይ አምላክም እስትንፋስ ሕይወትን ይሰጠኛል። 5ከቻልህ መልስልኝ፤ በፊቴ ነገርህን አስተካክለህ ተነሥተህ ቁም። 6እነሆ፣ በእግዚአብሔር ፊት እንደ አንተ ነኝ፤ እኔም ደግሞ ከሸክላ የተቈነጠስሁ ነኝ። 7የእኔ ፍርሃት አያስፈራህ፤ የእኔም ጫና አይከብድብህ።
8“በርግጥ እኔ እየሰማሁ ተናግረሃል፤ የቃላትህንም ድምፅ ሰምቻለሁ። 9‘ንጹሕ ነኝ፣ ዐመፅም የለብኝም፤ ጽዱ ነኝ፣ በደልም በእኔ ዘንድ የለም። 10ይሁን እንጂ እርሱ ነቀፋ ያገኝብኛል፤ እንደ ጠላቱም ይቈጥረኛል። 11እግሮቼን በግንድ ያስራል፤ መንገዶቼንም ሁሉ ይጠባበቃል።’
12“በዚህ ነገር ግን ልክ አይደለህም እልሃለሁ፤ እግዚአብሔር ከማንም ሟች ይበልጣልና። 13እርሱ ለሰው ቃል አንዳች አይመልስም ብለህ ለምን ትከራከረዋለህ? 14እግዚአብሔር በአንድ መንገድ፣ ከዚያም በሌላ ይናገራልና፤ ሰው ግን አያስተውለውም። 15በሕልም፣ በሌሊት ራእይ፣ ሰዎች በመኝታቸው ላይ ሳሉ ከባድ እንቅልፍ በወደቀባቸው ጊዜ፣ 16ያን ጊዜ ጆሮአቸውን ይከፍታል፤ ማስጠንቀቂያውንም ያተምባቸዋል፤ 17ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልስ ዘንድ፣ ትዕቢትንም ከሰው ይከለክል ዘንድ፤ 18ነፍሳቸውን ከጒድጓድ ይጠብቃል፤ ሕይወታቸውንም በሰይፍ ከመጥፋት ይከለክላል።
19“ሰውም ደግሞ በመኝታው ላይ በሕመም ይገሠጻል፤ በአጥንቶቹም ውስጥ የማያቋርጥ ሕመም አለ፤ 20ስለዚህም ሕይወቱ እንጀራን ትጸየፋለች፤ ነፍሱም የተመረጠውን ምግብ ትጸየፋለች። 21ሥጋው ይከሳል፤ ተሰውረው የነበሩ አጥንቶቹም ይወጣሉ። 22ነፍሱ ወደ ጒድጓድ ትቀርባለች፤ ሕይወቱም ሞትን ወደሚያመጡት ትቀርባለች።
23“ለእርሱ መልእክተኛ፣ ከሺህ አንዱ የሆነ አማላጅ ቢኖር፣ ለሰውም የሚገባውን ነገር ሊነግረው፣ 24ይራራለትና እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ ጒድጓድ ከመውረድ ታደገው፤ ቤዛ አግኝቻለሁና።’ a a v24 ነፍስን ከጒድጓድ የሚያድነው ቤዛ፣ ከኤሊሁ ቃላት አልፎ አባታችን አንድ ቀን በኢየሱስ ወደሚያዘጋጀው ቤዛ ይጠቍማል፤ እርሱም ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሰጠ። 25ያን ጊዜ ሥጋው ከሕፃን ሥጋ ይልቅ ይለመልማል፤ ወደ ወጣትነቱ ዘመንም ይመለሳል። 26ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፤ አምላኪውም በእርሱ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኛል፤ አምላኪው የእግዚአብሔርን ፊት በደስታ ጩኸት ያያል፤ እግዚአብሔርም ጽድቁን ለዚያ ሰው ይመልሳል። 27በሰዎች ፊት እየዘመረ እንዲህ ይላል፤ ‘ኀጢአት ሠራሁ፣ ቅኑንም ነገር አጣመምሁ፤ ነገር ግን ብድራት አልተከፈለኝም። 28ነፍሴን ወደ ጒድጓድ ከመውረድ ተቤዠ፤ እኔም ብርሃንን አያለሁ።’
29“እነሆ፣ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ከሰው ጋር ደጋግሞ ያደርጋል፤ 30ነፍሱን ከጒድጓድ ይመልስ ዘንድ፤ በሕያዋን ብርሃንም ይበራ ዘንድ።
31“ኢዮብ ሆይ፣ አድምጥ፤ ስማኝ፤ ዝም በል፣ እኔም እናገራለሁ። 32የምትለው ነገር ቢኖርህ መልስልኝ፤ ተናገር፤ ጻድቅ ሆነህ ማየትን እወዳለሁና። 33ያለዚያ ግን ስማኝ፤ ዝም በል፣ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።”