ሰናክሬም ወረረ፤ ሕዝቅያስም ተዘጋጀ
ሰናክሬም አድማሱን ይሞላል፤ ስለዚህ ሕዝቅያስ ምንጮቹን ይደፍናል፣ ቅጥሩን ያድሳል፣ ከእርሱ ጋር ካሉት ይልቅ ከእኛ ጋር ያሉት ይበዛሉ ብሎ ለሕዝቡ ይናገራል። አሦር በአብ ላይ ያደረገው ፌዝ በጸሎትና በመልአክ ምላሽ ያገኛል። በኋላም በሀብቱና በመልእክተኞቹ ምክንያት የተነሣው የራሱ ትዕቢት ደግሞ መዋረድ ያስፈልገዋል።
32 1ከእነዚህ ነገሮችና ከእነዚህ የታማኝነት ሥራዎች በኋላ፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ይሁዳን ወረረ፤ የተመሸጉ ከተሞቿን ከብቦ ለራሱ ሊይዛቸው አሰበ። 2ሕዝቅያስም ሰናክሬም መጥቶ ኢየሩሳሌምን ለመውጋት እንዳሰበ ባየ ጊዜ፣ 3ከከተማዪቱ ውጭ ያሉትን ምንጮች ስለ መድፈን ከሹማምቱና ከጦረኞቹ ጋር መከረ፤ እነርሱም ረዱት። 4ብዙ ሕዝብም ተሰብስቦ ምንጮችን ሁሉና በምድሪቱ መካከል የሚፈሰውን ወንዝ ደፈኑ፤ “የአሦር ነገሥታት መጥተው የተትረፈረፈ ውሃ ለምን ያገኛሉ?” አሉ።
5የፈረሱትን የቅጥሩን ክፍሎች ሁሉ መልሶ ለመሥራት ተጋ፤ በእርሱም ላይ ግንቦችን አነሣ፤ በውጭም ሌላ ቅጥር ሠራ፤ የዳዊትን ከተማ ሚሎ አጸና፤ ብዙ የጦር መሣሪያዎችንና ጋሻዎችን አዘጋጀ። a a v5 ሚሎ በዳዊት ከተማ ተራራማ ጎን ላይ የተሠራ የድልድል ዕርከኖችና የመደገፊያ ግንቦች ሥርዓት ነበር። 6በሕዝቡ ላይ የጦር አዛዦችን ሾመ፤ በከተማዪቱ በር አደባባይ ሰበሰባቸው፤ እንዲህ ብሎም አበረታታቸው፤ 7“በርቱ፤ ጠንክሩ። ከእርሱ ጋር ካሉት ይልቅ ከእኛ ጋር ያሉት ይበልጣሉና ከአሦር ንጉሥና ከሠራዊቱ ሁሉ የተነሣ አትፍሩ፤ አትደንግጡ። 8ከእርሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ ብቻ ነው፤ ከእኛ ጋር ግን የሚረዳንና ጦርነታችንን የሚዋጋልን አባታችን ነው።” ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ታመነ።
ሰናክሬም አባታችንን ዘለፈ
9ከዚህ በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ላኪሶን ከቦ ሳለ፣ አገልጋዮቹን ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በዚያ ወዳሉት ይሁዳ ሁሉ ላከ፤ እንዲህም አለ፤ 10“የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል፤ በኢየሩሳሌም ተከባችሁ ተቀምጣችሁ፣ በምን ትታመናላችሁ? 11‘እግዚአብሔር አምላካችን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል’ ብሎ፣ ሕዝቅያስ በራብና በጥም እንድትሞቱ አሳልፎ ሰጥቷችሁ፣ እያታለላችሁ አይደለምን? 12የእርሱን ኰረብታዎችና መሠዊያዎች ያስወገደ፣ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ‘በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በዚያም መሥዋዕት አሳርጉ’ ያለ ሕዝቅያስ ራሱ አይደለምን? 13እኔና አባቶቼ በሌሎች አገሮች ላሉ ሕዝቦች ሁሉ ያደረግነውን አታውቁምን? የእነዚያ ሕዝቦች አማልክት አገሮቻቸውን ከእጄ ማዳን ቻሉን? 14አባቶቼ ካጠፏቸው ሕዝቦች አማልክት ሁሉ፣ ሕዝቡን ከእጄ ማዳን የቻለ የትኛው አምላክ ነው? እንግዲህ አምላካችሁ ከእጄ እንዴት ሊያድናችሁ ይችላል? 15እንግዲህ ሕዝቅያስ እንዲህ አያታልላችሁ፤ አያሳስታችሁ፤ አትመኑትም፤ የማንም ሕዝብ ወይም መንግሥት አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ወይም ከአባቶቼ እጅ ማዳን አልቻለም፤ ይልቁንም አምላካችሁ ከእጄ ከቶ አያድናችሁም!”
16አገልጋዮቹም በአባታችንና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ከዚህ የባሰ ተናገሩ። 17ሰናክሬም ደግሞ የእስራኤል አምላክ የሆነውን አባታችንን የሚያዋርዱ ደብዳቤዎችን ጻፈ፤ በእርሱም ላይ፣ “የሕዝቦች አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ እንዳላዳኑ ሁሉ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ አያድንም” ብሎ ተናገረ። 18ከተማዪቱንም ለመያዝ፣ በቅጥሩ ላይ የነበሩትን የኢየሩሳሌምን ሰዎች ለማስፈራራትና ለማስደንገጥ በይሁዳ ቋንቋ ከፍ ባለ ድምፅ ጮኹባቸው። 19ስለ ኢየሩሳሌም አምላክ፣ በሰው እጅ እንደ ተሠሩ እንደ ምድር ሕዝቦች አማልክት አድርገው ተናገሩ።
20ንጉሡ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ጸለዩ፤ ወደ ሰማይም ጮኹ። 21አባታችንም መልአክ ላከ፤ እርሱም በአሦር ንጉሥ ሰፈር የነበሩትን ኀያላን ተዋጊዎች፣ አዛዦችና መኰንኖች ሁሉ ገደለ። ሰናክሬምም ተዋርዶ ወደ አገሩ ተመለሰ፤ ወደ አምላኩም ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ፣ ከገዛ ልጆቹ አንዳንዶቹ በዚያ በሰይፍ ገደሉት። 22አባታችንም ሕዝቅያስንና የኢየሩሳሌምን ሰዎች ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬምና ከሌሎች ሁሉ እጅ አዳናቸው፤ በየአቅጣጫውም ተንከባከባቸው። 23ብዙዎችም በኢየሩሳሌም ለአባታችን ገጸ በረከት፣ ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስም ውድ ስጦታዎች አመጡ፤ ከዚያም በኋላ አሕዛብ ሁሉ ሕዝቅያስን እጅግ አከበሩት።
የሕዝቅያስ ሕመም፣ ትዕቢትና ብልጽግና
24በዚያም ዘመን ሕዝቅያስ ለሞት እስኪቃረብ ድረስ ታመመ፤ ወደ አባታችንም ጸለየ፤ እርሱም መለሰለት፤ ምልክትም ሰጠው። 25ሕዝቅያስ ግን ለተደረገለት መልካም ነገር ብድራት አልመለሰም፤ ልቡ በትዕቢት ተነፋ፤ ስለዚህ በእርሱና በይሁዳ በኢየሩሳሌምም ላይ ቍጣ መጣ። 26ሕዝቅያስም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ትዕቢት ራሱን አዋረደ፤ ስለዚህ የአባታችን ቍጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልደረሰባቸውም።
27ሕዝቅያስ ታላቅ ሀብትና ክብር ነበረው። ለብር፣ ለወርቅ፣ ለከበሩ ድንጋዮች፣ ለሽቶዎች፣ ለጋሻዎችና ለሌሎች ውድ ነገሮች ማከማቻ ቤቶችን ሠራ፤ 28ለእህል ምርት፣ ለአዲስ የወይን ጠጅና ለዘይት ማከማቻ ቤቶችን፣ ለእንስሳት ሁሉ በረቶችን፣ ለመንጎችም ጓሮዎችን ሠራ። 29ለራሱም ከተሞችን ሠራ፤ አባታችን እጅግ ታላቅ ሀብት ስለ ሰጠው ብዙ መንጎችንና ከብቶችን አፈራ። 30ሕዝቅያስም የጊሆንን የላይኛውን መውጫ ደፈነ፤ ውሃውንም ወደ ዳዊት ከተማ ምዕራብ ወገን አወረደ። ባደረገውም ሁሉ ተከናወነለት። 31የባቢሎን መኳንንት በምድሪቱ ስለ ተደረገው ምልክት ይጠይቁ ዘንድ መልእክተኞችን በላኩለት ጊዜ፣ አባታችን ሊፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ያውቅ ዘንድ ለራሱ ተወው።
32የሕዝቅያስ ቀሪ ሥራዎችና የታማኝነት ሥራዎቹ፣ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ባየው ራእይ፣ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። 33ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ተቀበረ። ይሁዳ ሁሉና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በሞቱ ጊዜ አከበሩት። በእርሱም ፋንታ ልጁ ምናሴ ነገሠ።