የመለኪያ ገመድ የያዘ ሰው
አንድ ቀያሽ ኢየሩሳሌምን ሊለካ ይወጣል፤ እንዳይደክም ይነገረዋል፤ ከተማይቱ ከማንኛውም ቅጥር ተርፋ ትሞላለችና። አብ ራሱ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር፣ በውስጧም ክብር ይሆናል፤ ብዙ አሕዛብም ከእርሱ ጋር ይተባበራሉ፤ ልጆቹም ይሆናሉ።
2 1ቀና ብዬ ስመለከት፣ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ ሰው አየሁ። 2እኔም፣ “ወዴት ትሄዳለህ?” ብዬ ጠየቅሁ። እርሱም፣ “ኢየሩሳሌምን ለመለካት፣ ስፋቷና ርዝመቷ ምን ያህል እንደ ሆነ ለማየት” አለኝ።
3ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጣ፤ ሊቀበለውም ሌላ መልአክ ወጣ፤ 4“ሩጥ፤ ይህን ጐበዝ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘በውስጧ ያሉት ሰዎችና እንስሳት እጅግ ስለሚበዙ፣ ኢየሩሳሌም እንደ ክፍት ሜዳ ትቀመጣለች።’ ” አለው።
5“‘እኔ ራሴ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፤ ይላል አባታችን፤ በውስጧም ክብር እሆናለሁ።’ ”
6“ኑ! ኑ! ከሰሜን ምድር ሽሹ፤ ይላል አባታችን፤ እንደ ሰማይ አራት ነፋሳት በትኜአችኋለሁና፤ ይላል አባታችን። 7ነዪ፣ ጽዮን ሆይ! ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋራ የምትኖሪ ሆይ፤ አምልጪ!
8የሰማይ ሠራዊት አባት እንዲህ ይላል፤ ከክብሩ በኋላ የዘረፉአችሁን አሕዛብ ለመቃወም ላከኝ፤ የሚነካችሁ ሁሉ የዐይኑን ብሌን ይነካል፦
9እነሆ፣ እጄን በእነርሱ ላይ አወዛውዛለሁ፤ ላገለገሉአቸውም ዘረፋ ይሆናሉ። የሰማይ ሠራዊት አባት እንደ ላከኝ ያን ጊዜ ታውቃላችሁ።
10አንቺ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፤ ዘምሪ ደስም ይበልሽ! እነሆ፣ በመካከልሽ ልኖር እመጣለሁና፤ ይላል አባታችን።
11“በዚያን ቀን ብዙ አሕዛብ ከአባታችን ጋራ ይተባበራሉ፤ ልጆቼም ይሆናሉ። በመካከልሽ እኖራለሁ፤ የሰማይ ሠራዊት አባትም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂያለሽ። 12አባታችንም በተቀደሰችው ምድር ይሁዳን ድርሻው አድርጎ ይወስዳል፤ ኢየሩሳሌምንም እንደ ገና ይመርጣል።
13ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአባታችን ፊት ዝም ይበል፤ ከተቀደሰ ማደሪያው ተነሥቶአልና።”