ዐሥራ ሁለቱ ተላኩ
አሥራ ሁለቱ በስማቸው ተጠርተው ያለ ገንዘብና ያለ ትርፍ ልብስ በሩን ሊዘጉባቸው ወደሚችሉ ከተሞች ይላካሉ። ኢየሱስ ስለ ግርፋት፣ ስለ ፍርድ ቤቶችና እርስ በርሳቸው ስለሚነሣሡ ቤተሰቦች በግልጽ ይናገራል። ሆኖም ያለ አብ አንዲት ድንቢጥ እንኳ አትወድቅም፤ የራሳቸውም ጠጉር ሁሉ የተቈጠረ ነው።
10 1ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፣ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያወጡና በሽታን ሁሉ፣ ደዌን ሁሉ እንዲፈውሱ በእነርሱ ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። 2የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን፣ ወንድሙም እንድርያስ፤ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብ፣ ወንድሙም ዮሐንስ፤ 3ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፤ ቶማስና ቀራጩ ማቴዎስ፤ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ፤ 4ቀነናዊው ስምዖንና አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።
5ኢየሱስ እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ላከ፤ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ወደ አሕዛብ አገር አትሂዱ፤ ወደ ሰማርያ ከተማም አትግቡ። 6ይልቁንም ወደ እስራኤል ቤት ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ። 7ስትሄዱም እንዲህ የሚለውን መልእክት አውጁ፤ ‘የአባታችን መንግሥት ቀርቧል።’ a a v7 “የአባታችን መንግሥት” የሚለው፣ ማቴዎስ በወንጌሉ ሁሉ የሚጠቀምበትን ይበልጥ የታወቀውን “የሰማይ መንግሥት” የሚለውን ይተካል። ሁለቱም ሐረጎች አንድን እውነታ ይሰይማሉ፤ ይኸውም የአባታችን ግዛት ወደ ዓለም መግባቱን ነው። 8የታመሙትን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ። በነጻ ተቀብላችኋል፤ በነጻ ስጡ። 9በመቀነታችሁ ወርቅ ቢሆን ብር ቢሆን መዳብ ቢሆን አትያዙ። 10ለመንገድ ከረጢት ቢሆን ሁለተኛ እጀ ጠባብ ቢሆን ጫማ ቢሆን በትር ቢሆን አትያዙ፤ ሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና። 11በማንኛውም ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ፣ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ አጣሩ፤ ከዚያ እስክትወጡ ድረስም በዚያው ተቀመጡ። 12ወደ ቤቱም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ። 13ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይውረድበት፤ የማይገባው ቢሆን ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ። 14ማንም ባይቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን ባይሰማ፣ ከዚያ ቤት ወይም ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ። 15እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ ይቀልላቸዋል።
16እነሆ፣ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች፣ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ። 17ከሰዎች ተጠንቀቁ፤ ለሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋልና፤ በምኵራባቸውም ይገርፏችኋል። 18ስለ እኔም ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን በገዦችና በነገሥታት ፊት ትቀርባላችሁ። 19አሳልፈው በሚሰጧችሁ ጊዜ፣ ምን እንደምትናገሩ ወይም እንዴት እንደምትናገሩ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና፤ 20የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ በእናንተ ሆኖ ነውና እንጂ፣ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁም።
21ወንድም ወንድሙን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ አባትም ልጁን፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ፤ እንዲገደሉም ያደርጋሉ። 22ስለ ስሜም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። 23በአንዲቱ ከተማ ሲያሳድዷችሁ ወደ ሌላዪቱ ሽሹ። እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጅ ሳይመጣ የእስራኤልን ከተሞች አትዘልቁም።
24ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም። 25ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፣ ባሪያም እንደ ጌታው ቢሆን ይበቃዋል። የቤቱን ባለቤት ብዔልዜቡል ካሉት፣ የቤቱን ሰዎችማ እንደ ምን አብልጠው ይሉ!
26ስለዚህ አትፍሯቸው። የማይገለጥ የተሸፈነ፣ የማይታወቅም የተሰወረ ነገር የለምና። 27በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮአችሁ የሚሹከሹከውን ከሰገነት ላይ ሆናችሁ አውጁ። 28ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንም ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ።
29ሁለት ድንቢጦች በአንድ ሳንቲም አይሸጡምን? ከእነርሱም አንዲቱ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ወደ ምድር አትወድቅም። 30የራሳችሁ ጠጉር እንኳ ሁሉ ተቈጥሯል። 31ስለዚህ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ።
32ስለዚህ በሰዎች ፊት የሚመሰክርልኝን ሁሉ፣ እኔ ደግሞ በሰማይ ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ። 33በሰዎች ፊት የሚክደኝን ግን፣ እኔ ደግሞ በሰማይ ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።
34በምድር ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን ለማምጣት እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። 35ሰውን ከአባቱ፣ ሴት ልጅን ከእናቷ፣ ምራትንም ከአማቷ ጋር ላጣላ መጥቻለሁና፤ 36የሰውም ጠላቶቹ የገዛ ቤተ ሰዎቹ ይሆናሉ። 37ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ አይገባውም። 38መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ ለእኔ አይገባውም። 39ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፤ ስለ እኔም ነፍሱን የሚያጠፋ ያገኛታል።
40እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። 41ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ያገኛል። 42ከእነዚህም ከታናናሾቹ ለአንዱ፣ ደቀ መዝሙሬ ስለ ሆነ ብቻ አንዲት ጽዋ ቀዝቃዛ ውሃ የሚያጠጣ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋው ከቶ አይጠፋበትም።”