በከተሞቻቸው ማስተማር
በእስር ቤት ያለው ዮሐንስ ኢየሱስ በእርግጥ የሚመጣው እርሱ እንደ ሆነ ለመጠየቅ ይልካል። መልሱ ማጽናኛ ሳይሆን እየሆነ ያለው ነገር ዝርዝር ነው። ከዚያም ኢየሱስ ተአምራቱን አይተው ሳይለወጡ የቀሩትን ከተሞች ይወቅሳል፣ አብን ያመሰግናል፣ ለደከመም ሁሉ ዕረፍትን ያቀርባል።
11 1ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማስተማር ከጨረሰ በኋላ፣ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ ወጣ።
የዮሐንስ ጥያቄ ከእስር ቤት
2ዮሐንስ በእስር ቤት ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ፣ በደቀ መዛሙርቱ አማካይነት መልእክት ላከ፤ 3እንዲህም ሲል ጠየቀው፤ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?”
4ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ለዮሐንስ ንገሩት፦
5“ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ይሄዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኆችም ወንጌል ይሰበካል፤ 6በእኔም የማይሰናከል ሁሉ ብፁዕ ነው።”
7እነርሱም ሲሄዱ፣ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ ለሕዝቡ እንዲህ ማለት ጀመረ፤ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዝ ሸምበቆ? 8ታዲያ ለምን ወጣችሁ? ለስላሳ ልብስ የለበሰ ሰው ልታዩ? እነሆ፣ ለስላሳ ልብስ የሚለብሱ በነገሥታት ቤተ መንግሥት ይኖራሉ። 9ነገር ግን ለምን ወጣችሁ? ነቢይ ልታዩ? አዎን እላችኋለሁ፣ ከነቢይም እጅግ የሚበልጥ። 10ስለ እርሱ እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው፦ ‘እነሆ፣ መልእክተኛዬን ከፊትህ እልካለሁ፤ እርሱም መንገድህን በፊትህ ያዘጋጃል።’ 11እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ ነገር ግን በአባታችን መንግሥት ውስጥ ከሁሉ የሚያንሰው ከእርሱ ይበልጣል። 12ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ፣ የአባታችን መንግሥት በኀይል ትገፋለች፤ ኀይለኞችም ይነጥቋታል። 13ነቢያቱ ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋልና፤ 14ልትቀበሉትም ብትወዱ፣ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ እርሱ ነው። 15የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
16ይህን ትውልድ ከምን ጋራ አመሳስለዋለሁ? በገበያ ቦታ ተቀምጠው ሌሎችን የሚጣሩ ልጆችን ይመስላል፤ 17‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ የሙሾ ዝማሬ ዘመርንላችሁ፤ እናንተ ግን አላለቀሳችሁም።’ 18ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና፣ ‘ጋኔን አለበት’ ይላሉ። 19የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፣ ‘እነሆ፣ ሆዳምና ጠጪ፣ የቀራጮችና የኀጢአተኞች ወዳጅ!’ ይላሉ። ነገር ግን ጥበብ በሥራዋ ጸደቀች።”
ንስሓ ላልገቡ ከተሞች ወዮ
20ከዚያም አብዛኛውን ተአምራቱን ያደረገባቸውን ከተሞች ንስሓ ስላልገቡ ይወቅሳቸው ጀመር።
21“አንቺ ኮራዚን፣ ወዮልሽ! አንቺ ቤተ ሳይዳ፣ ወዮልሽ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ፣ ከብዙ ጊዜ በፊት ማቅ ለብሰውና አመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር። 22ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። 23አንቺም ቅፍርናሆም፣ እስከ ሰማይ ከፍ ከፍ ትያለሽን? እስከ ሲኦል ድረስ ትወርጃለሽ። በአንቺ የተደረጉት ተአምራት በሰዶም ተደርገው ቢሆን ኖሮ፣ እስከ ዛሬ በቆመች ነበር። 24ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ምድር ይቀልላታል።”
አብ በወልድ መገለጡ
25በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “አባት ሆይ፣ የሰማይና የምድር ጌታ፣ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህ አመሰግንሃለሁ። 26አዎን አባት ሆይ፣ ይህ በፊትህ መልካም ሆኖ ታይቶአልና። 27ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጠኝ። ወልድንም ከአብ በቀር ማንም አያውቀውም፤ አብንም ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚወድደው በቀር ማንም አያውቀውም።
28“እናንተ ደካሞችና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። 29ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህና በልቤ ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ። 30ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”