በስሜ የተጠራችሁ
አብ እንደ ብረት የደነደኑ ብሎ ለሚጠራቸው ሕዝብ፣ ለጣዖቶቻቸው ምስጋና እንዳይሰጡ ሁሉን አስቀድሞ እንደ ተናገረ ይነግራቸዋል። በመከራ አጠራቸው፤ ሊኖራቸው ይችል ስለ ነበረውም ሰላም ያዝናል። ቢሆንም ቃሉ ይህ ነው፤ እንደ ተቤዣቸው እየተናገራችሁ ከባቢሎን ውጡ።
48 1የያዕቆብ ቤት ሆይ፣ ይህን ስሙ፤ በእስራኤል ስም የምትጠሩ፣ ከይሁዳ ዘር የወጣችሁ፤ በአባታችን ስም የምትምሉ አባታችንንም የምትጠሩ፤ ነገር ግን በእውነት ወይም በጽድቅ አይደለም። 2ራሳቸውን የቅድስቲቱ ከተማ ሰዎች ብለው ይጠራሉና፣ በአባታችንም ይደገፋሉ፤ ስሙ የሰማይ ሠራዊት አባት ነው።
3“ቀደምቶቹን ነገሮች ከጥንት ጀምሬ ተናግሬአለሁ፤ ከአፌ ወጡ፣ አስታወቅኋቸውም። ከዚያም በድንገት አደረግሁ፣ ተፈጸሙም። 4እንዴት እልኸኛ እንደ ሆንህ ዐውቄ ነበርና፤ የአንገትህ ጅማት እንደ ብረት የጠነከረ፣ ግምባርህም እንደ ናስ የደነደነ ነው።’ 5ይህን ነገር ከጥንት ጀምሬ ነገርሁህ፤ ከመሆናቸው በፊት አስታወቅሁህ፤ ስለዚህ እንዲህ ከቶ ልትል አትችልም፤ ‘ጣዖቴ አደረጋቸው፤ የተቀረጸው ምስሌና የቀለጠው ቅርጼ አዘዛቸው።” 6ይህን ሰምተሃል፤ አሁን ሁሉንም ተመልከት። አታረጋግጥምን? ከእንግዲህ ጀምሮ አዲስ ነገር እነግርሃለሁ፣ ከቶ ያላወቅኸውን የተሰወረ ነገር።’ 7እነዚህ አሁን ተፈጠሩ እንጂ ከጥንት አይደሉም፤ ከዛሬ በፊት ከቶ አልሰማሃቸውም ነበር፤ ስለዚህ ‘ዐውቄአቸው ነበር’ ብለህ ልትል አትችልም። 8ከቶ አልሰማህም፣ አላወቅህም፤ ከጥንት ጀምሮ ጆሮህ አልተከፈተም። እንዴት በክህደት እንደምትሠራ ዐውቄ ነበርና፤ ከተወለድህ ጀምሮ ዐመፀኛ ተብለሃል። 9ስለ ስሜ ስል ቍጣዬን እገታለሁ፤ ስለ ምስጋናዬም ለአንተ ብዬ እገታዋለሁ፤ እንዳላጠፋህ። 10እነሆ፣ አጠራሁህ፣ ነገር ግን እንደ ብር አይደለም፤ በመከራ እቶን ፈትኜሃለሁ። 11ስለ ራሴ ስል፣ ስለ ራሴ ስል አደርገዋለሁ፤ ስሜ ለምን ይረክሳል? ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም።
ፊተኛውና ኋለኛው እኔ ነኝ
12“ያዕቆብ ሆይ፣ አድምጠኝ፤ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፤ እኔ ነኝ፤ ፊተኛው እኔ ነኝ፣ ኋለኛውም እኔ ነኝ። 13እጄ የምድርን መሠረት ጣለች፤ ቀኜም ሰማያትን ዘረጋች፤ በጠራኋቸውም ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ።”
14እናንተ ሁላችሁ ተሰብሰቡ አድምጡም፤ ከእነርሱ መካከል ይህን የተናገረ ማን ነው? የምወደው እርሱ በባቢሎን ላይ ፈቃዴን ይፈጽማል፤ ክንዱም በባቢሎናውያን ላይ ይሆናል። a a v14 “የምወደው እርሱ” የሚለው ቂሮስን ያመለክታል፤ እርሱም እግዚአብሔር ባቢሎንን ድል ነሥቶ እስራኤልን ነጻ ሊያወጣ ያስነሣው የፋርስ ንጉሥ ነበር።
15እኔ፣ እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ አዎን፣ ጠርቼዋለሁ፤ አምጥቼዋለሁም፤ እርሱም በመንገዱ ይከናወንለታል።
16ወደ እኔ ቅረቡ፣ ይህን ስሙ፤ ከመጀመሪያው ጀምሮ በስውር አልተናገርሁም፤ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በዚያ ነበርሁ። አሁንም ጌታ አባት እኔንና መንፈሱን ላከ። b b v16 ብዙዎች በዚህ ስንኝ ኢየሱስ ሲናገር ይሰማሉ፤ እርሱም አባታችን በሚቀጥሉት ምዕራፎች ሊገልጠው ያለው፣ ከእርሱ ጋር ካለው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተላከ አገልጋይ ነው።
17አባታችን እንዲህ ይላል፤ ቤዛህ፣ የእስራኤል ቅዱስ፦ ለጥቅምህ የሚያስተምርህ፣ በምትሄድበትም መንገድ የሚመራህ አባትህ እኔ ነኝ። 18“ትእዛዜን ብታዳምጥ ኖሮ! ያን ጊዜ ሰላምህ እንደ ወንዝ በፈሰሰ ነበር፤ ጽድቅህም እንደ ባሕር ማዕበል በሆነ ነበር። 19ልጆችህ እንደ አሸዋ በሆኑ ነበር፤ ዘርህም እንደ አሸዋው ቅንጣቶች በሆነ ነበር፤ ስማቸውም ከፊቴ ከቶ ባልተቈረጠ፣ ባልጠፋም ነበር።”
20ከባቢሎን ውጡ! ከባቢሎናውያን ሽሹ! በደስታ ጩኸት ንገሩት፣ አውጁት፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ላኩት። ‘አባታችን ባሪያውን ያዕቆብን ተቤዠ!’ በሉ። 21በበረሃ በመራቸው ጊዜ አልተጠሙም፤ ከዐለት ውስጥ ውሃ አፈሰሰላቸው። ዐለቱን ሰነጠቀ፣ ውሃውም ፈለቀ።
22“ሰላም የለም፣” ይላል አባታችን፣ “ለክፉዎች።”