በዙሪያህ ያለውን ቤተሰብ አክብር
ቤተ ክርስቲያን እንደ አባታችን ቤተሰብ መያዝ አለባት፤ ሽማግሌዎችን እንደ አባቶች፣ ወጣት ሴቶችን እንደ እኅቶች። ከዚያም ተግባራዊ ደንቦች፤ ቤተ ክርስቲያን የትኞቹን መበለቶች እንደምትረዳና የትኞቹ እንደገና ማግባት እንዳለባቸው፣ ለሽማግሌዎች ክብርና ጥበቃ፣ በኃጢአት ለሚጸኑ በሕዝብ ፊት መገሠጽ፣ ለጢሞቴዎስ ሆድም የወይን ጠጅ።
5 1ሽማግሌውን በኀይል አትገሥጽ፤ ነገር ግን እንደ አባት ለምነው፤ ጐልማሶችንም እንደ ወንድሞች፣ 2አረጋውያን ሴቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችንም በፍጹም ንጽሕና እንደ እኅቶች አድርገህ ለምናቸው።
3በእውነት መበለቶች የሆኑትን መበለቶች አክብር። 4አንዲት መበለት ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሯት ግን፣ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤታቸው አክብሮትን ማሳየትን፣ ለወላጆቻቸውም ብድራትን መመለስን ይማሩ፤ ይህ አባታችንን ደስ ያሰኛል። 5በእውነት መበለት የሆነችውና ብቻዋን የቀረችው ግን፣ ተስፋዋን በአባታችን ላይ አድርጋ ሌሊትና ቀን በልመናና በጸሎት ትጸናለች። 6ለገዛ ተድላዋ የምትኖረው መበለት ግን በሕይወት ሳለች እንኳ የሞተች ናት። 7ነቀፋ የሌለባቸው እንዲሆኑ ይህን ደግሞ አዝዛቸው። 8ማንም ለገዛ ወገኖቹ፣ ይልቁንም ለቤተሰቡ አባላት የማያስብ ቢሆን፣ ሃይማኖትን ክዷል፤ ከማያምንም ሰው ይልቅ የከፋ ነው።
9መበለት ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት የማያንስና ለአንድ ባል ታማኝ የነበረች ብትሆን ብቻ በመዝገብ ትመዝገብ፤ 10በመልካም ሥራዋም የተመሰከረላት ትሁን፤ ልጆችን ያሳደገች፣ እንግዶችን የተቀበለች፣ የቅዱሳንን እግር ያጠበች፣ የተቸገሩትን የረዳች፣ መልካሙንም ሥራ ሁሉ የተከታተለች ብትሆን ነው።
11ወጣት መበለቶችን ግን በመዝገብ ከመመዝገብ ተከልከል፤ ፍላጎታቸው ከክርስቶስ ሲስባቸው ማግባት ይፈልጋሉና፤ 12እንዲህም የመጀመሪያ ቃል ኪዳናቸውን በመተዋቸው በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ። a a v12 “የመጀመሪያ ቃል ኪዳናቸው” ማለት በመበለቶች መዝገብ ሲመዘገቡ ክርስቶስንና ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የገቡትን ቃል ያመለክታል። 13ደግሞም ከቤት ወደ ቤት እየተዘዋወሩ ሥራ ፈትተው መቀመጥን ይማራሉ፤ ሥራ ፈትተው ብቻ ሳይሆን የማይገባቸውን እየተናገሩ አሉባልተኞችና በሌሎች ጒዳይ ጣልቃ ገቢዎች ይሆናሉ። 14ስለዚህ ወጣት መበለቶች እንዲያገቡ፣ ልጆች እንዲወልዱ፣ ቤታቸውን እንዲያስተዳድሩ፣ ለጠላትም ለማማት ምንም አጋጣሚ እንዳይሰጡ እወዳለሁ። 15አንዳንዶች ፈቀቅ ብለው ሰይጣንን ለመከተል አስቀድመው ዘወር ብለዋልና። 16አንዲት አማኝ ሴት በዘመዶቿ መካከል መበለቶች ቢኖሩ፣ እርሷ ትደጉማቸው፤ ቤተ ክርስቲያን በእውነት መበለቶች የሆኑትን መደገፍ ትችል ዘንድ፣ ሸክም አይሁንባት።
17በመልካም የሚመሩ ሽማግሌዎች፣ ይልቁንም በስብከትና በማስተማር የሚደክሙት፣ የእጥፍ ክብር ይገባቸዋል። 18መጽሐፍ፣ “እህልን በሚያበራየው በሬ አፍ ላይ አፍ መያዣ አታድርግ” እንዲሁም “ሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” ይላልና።
19በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ምስክርነት ካልሆነ በቀር፣ በሽማግሌ ላይ የሚቀርብን ክስ አትቀበል። 20በኀጢአት የሚጸኑትን ግን ሌሎቹ እንዲፈሩ በሁሉ ፊት ገሥጻቸው።
21በአባታችን፣ በክርስቶስ ኢየሱስና በተመረጡት መላእክት ፊት፣ ይህን ትእዛዝ ያለአድልዎ እንድትጠብቅ፣ በወገንተኝነትም ምንም እንዳታደርግ አጥብቄ አዝሃለሁ። 22በማንም ላይ እጅህን ለመጫን አትቸኵል፤ በሌሎችም ኀጢአት አትተባበር፤ ራስህን ንጹሕ አድርገህ ጠብቅ።
23ከእንግዲህ ውኃ ብቻ አትጠጣ፤ ስለ ሆድህና አዘውትሮ ስለሚይዝህ ሕመም ጥቂት የወይን ጠጅ ተጠቀም።
24የአንዳንዶች ሰዎች ኀጢአት ግልጽ ሆኖ ወደ ፍርድ ይቀድማቸዋል፤ የሌሎች ኀጢአት ግን ኋላ ይከተላል። 25እንዲሁም መልካም ሥራ ግልጽ ነው፤ ግልጽ ያልሆነውም እንኳ ተሰውሮ ሊቀር አይችልም።