የምትጠማ ነፍስ
ለመዘምራን አለቃ፤ የቆራ ልጆች የጥበብ መዝሙር።
ከመቅደሱ ተለይቶ 'አምላክህ የት ነው?' እየተባለ ሲዘበትበት፣ ዘማሪው ዳግመኛ ሊቀላቀለው የማይችለውን የበዓል ሕዝብ ይመራ እንደ ነበር ያስታውሳል። የተዋረደችውን ነፍሱን ሁለት ጊዜ ይጠይቃታል፤ ሁለቱንም ጊዜ በአንድ መልስ ይመልስላታል፦ በአብ ተስፋ አድርጊ፤ ዳግመኛ አመሰግነዋለሁ።
42 1ዋላ የውሃ ምንጭን እንደምትናፍቅ፣ እንዲሁ ነፍሴ አንተን ትናፍቃለች፣ አባቴ።
2ነፍሴ አባቴን ትጠማለች፣ ሕያውን አባት ትጠማለች። መቼ መጥቼ በፊቱ እቀርባለሁ? 3እንባዬ ቀንና ሌሊት ምግቤ ሆኖአል፤ ቀኑን ሙሉ፣ “አምላክህ የት አለ?” እያሉኝ ነው።
4ነፍሴን ሳፈስስ እነዚህን ነገሮች አስባለሁ፤ ከሕዝቡ ብዛት ጋር እንዴት እሄድ እንደ ነበር፣ በደስታ ጩኸትና በምስጋና መዝሙር በዓል ከሚያከብር ታላቅ ሕዝብ ጋር በሰልፍ ወደ አባታችን ቤት እንዴት እመራቸው እንደ ነበር።
5ነፍሴ ሆይ፣ ለምን ትተክዣለሽ? በውስጤስ ለምን ትታወኪያለሽ? አባታችንን ተስፋ አድርጊ፤ መድኃኒቴንና አባቴን ዳግመኛ አመሰግነዋለሁና።
6አባቴ ሆይ፣ ነፍሴ በውስጤ ተክዛለች፤ ስለዚህ ከዮርዳኖስና ከአርሞን ምድር፣ ከሚጻር ተራራ አስብሃለሁ።
7ጥልቅ በፏፏቴህ ድምፅ ጥልቅን ይጠራል፤ ሞገዶችህና ማዕበሎችህ ሁሉ በላዬ አለፉ። 8ቀን አባታችን የኪዳኑን ፍቅር ያዝዛል፤ ሌሊትም መዝሙሩ ከእኔ ጋር ነው፤ ለሕይወቴ አባት የሚቀርብ ጸሎት።
9ዐለቴ ለሆነው ለአባቴ እንዲህ እላለሁ፤ “ለምን ረሳኸኝ? በጠላት ጭቆና ምክንያት እያዘንኩ ለምን እዞራለሁ?” 10በዐጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገዳይ ቍስል፣ ባላጋራዎቼ ይሳለቁብኛል፤ ቀኑን ሙሉ፣ “አምላክህ የት አለ?” እያሉኝ።
11ነፍሴ ሆይ፣ ለምን ትተክዣለሽ? በውስጤስ ለምን ትታወኪያለሽ? አባታችንን ተስፋ አድርጊ፤ መድኃኒቴንና አባቴን ዳግመኛ አመሰግነዋለሁና።