ተነሥቷል
ሴቶቹ ሽቱ ይዘው ይመጣሉ፤ ድንጋዩ ተንከባሎ፣ አንድ ጐበዝም ተነሥቷል ሲል ያገኛሉ፤ ፈርተውም ይሸሻሉ፤ ለማንም አይናገሩም። ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያምና ለሌሎች ይገለጣል፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን አያምኗቸውም፤ ከዚያም አሥራ አንዱን ወደ ፍጥረት ሁሉ ይልካቸዋል።
16 1ሰንበት ባለፈ ጊዜ፣ መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ ሄደው ሊቀቡት ሽቶ ገዙ። 2ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እጅግ ማልደው፣ ፀሓይ ልክ እንደ ወጣች ወደ መቃብሩ ሄዱ። 3እርስ በርሳቸውም፣ “ድንጋዩን ከመቃብሩ መግቢያ ማን ያንከባልልልናል?” ተባባሉ። 4ቀና ብለው ሲመለከቱ ግን እጅግ ትልቅ የነበረው ድንጋይ አስቀድሞ ተንከባልሎ አዩ።
5ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የለበሰ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩ፤ ደነገጡም። 6እርሱም፣ “አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን ናዝራዊውን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቷል፤ በዚህ የለም። እነሆ፣ ያኖሩት ስፍራ።” አላቸው። 7“ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ፣ ‘ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው።”
8ሴቶቹም እየተንቀጠቀጡና እየተደነቁ ከመቃብሩ ሸሹ፤ ይፈሩ ነበርና ለማንም ምንም አልተናገሩም።
9ኢየሱስ ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ማልዶ ተነሥቶ፣ ሰባት አጋንንት አውጥቶላት ለነበረችው ለመግደላዊት ማርያም አስቀድሞ ተገለጠላት። a a v9 ጥንታዊዎቹ ቅጂዎች የማርቆስን ወንጌል በቍጥር 8 ይደመድማሉ። ቍጥር 9-20 በአብዛኞቹ በኋለኞቹ ቅጂዎች ይገኛሉ፤ እንደ አብዛኞቹ ዘመናዊ መጻሕፍት ቅዱሳት እዚህ ተጽፈዋል። 10እርሷም ሄዳ ከእርሱ ጋር ለነበሩት ለሚያዝኑትና ለሚያለቅሱት ነገረቻቸው። 11እነርሱም ኢየሱስ በሕይወት እንዳለና በእርሷ እንደ ታየ ሲሰሙ አላመኑም።
12ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገጠር ሲሄዱ ከእነርሱ ለሁለቱ በሌላ መልክ ተገለጠላቸው። 13እነርሱም ተመልሰው ለሌሎቹ ነገሯቸው፤ ነገር ግን እነርሱንም ደግሞ አላመኗቸውም።
14በኋላም ኢየሱስ ዐሥራ አንዱ በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ተገለጠላቸው፤ ተነሥቶ ያዩትን ስላላመኑ አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ገሠጻቸው።
15እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ወደ ዓለም ሁሉ ሄዳችሁ ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን ስበኩ። 16ያመነና የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይኰነናል። 17ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያስወጣሉ፤ በአዲስ ልሳኖች ይናገራሉ፤ 18እባቦችን በእጆቻቸው ያነሣሉ፤ ገዳይ መርዝም ቢጠጡ አይጐዳቸውም፤ እጆቻቸውን በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይድናሉ።”
19ጌታ ኢየሱስም ከተናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባታችንም ቀኝ ተቀመጠ። b b v19 ወልድ ሥራውን በፈጸመ ጊዜ ወደ አባቱ ጐን ተመለሰ — ከእርሱ ጋር የሚካፈለው የክብር ስፍራ። 20እነርሱም ወጥተው በየስፍራው ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር እየሠራ፣ በሚከተሉት ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር።