የዔሳው ትውልድ
የዔሳው ዘሮች የራሳቸው ሙሉ መዝገብ አላቸው፤ ሚስቶች፣ አለቆች፣ በእስራኤልም ላይ ማንም ንጉሥ ሳይነግሥ በኤዶም የነገሡ ነገሥታት። የታለፈው ወንድም ከታሪክ አልተሰረዘም፤ የተረጋጋ ታሪክ ያለው ጎረቤት ሕዝብ ሆነ።
36 1የዔሳው (ማለትም የኤዶም) የትውልድ ታሪክ ይህ ነው። 2ዔሳው ሚስቶቹን ከከነዓን ሴቶች ልጆች መካከል አገባ፤ የኬጢያዊው የኤሎን ልጅ ዓዳን፣ የኤዊያዊው የሲብዖን ልጅ የዓና ልጅ አህሊባማን፣ 3የናባዮትን እኅት የእስማኤልን ልጅ ባሥማትንም አገባ። 4ዓዳ ለዔሳው ኤልፋዝን ወለደች፤ ባሥማትም ራጉኤልን ወለደች፤ 5አህሊባማም የዑስን፣ ያላምንና ቆራን ወለደች፤ እነዚህ በከነዓን ምድር የተወለዱለት የዔሳው ልጆች ናቸው። 6ዔሳው ሚስቶቹን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ ቤተ ሰቡን ሁሉ፣ ከብቶቹን፣ እንስሶቹን ሁሉ፣ በከነዓን ያፈራውን ንብረቱን ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ርቆ ወደ ሌላ ምድር ሄደ። 7ሀብታቸው ብዙ ስለ ነበር አብረው መኖር አልቻሉም፤ የሰፈሩባት ምድር ከብቶቻቸው ስለ በዙ ሁለቱንም ልትሸከም አልቻለችም። 8ስለዚህ ዔሳው በሴይር ተራራማ አገር ሰፈረ። (ዔሳው ኤዶም ነው።)
9በሴይር ተራራማ አገር የኤዶማውያን አባት የሆነው የዔሳው የትውልድ ታሪክ ይህ ነው። 10የዔሳው ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፤ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጅ ኤልፋዝ፤ የዔሳው ሚስት የባሥማት ልጅ ራጉኤል። 11የኤልፋዝ ልጆች ቴማን፣ ኦማር፣ ሴፎ፣ ጋዕታምና ቄኔዝ ነበሩ። 12የዔሳው ልጅ የኤልፋዝ ቁባት ተምናዕ አማሌቅን ወለደችለት፤ እነዚህ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጆች ነበሩ። 13የራጉኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ናሖት፣ ዛራ፣ ሳማ፣ ሚዛ። እነዚህ የዔሳው ሚስት የባሥማት ልጆች ናቸው። 14የሲብዖን ልጅ የዓና ልጅ የሆነችው የዔሳው ሚስት የአህሊባማ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ለዔሳው የዑስን፣ ያላምንና ቆራን ወለደችለት።
15የዔሳው ልጆች አለቆች እነዚህ ናቸው። የዔሳው በኵር የኤልፋዝ ልጆች፤ አለቃ ቴማን፣ አለቃ ኦማር፣ አለቃ ሴፎ፣ አለቃ ቄኔዝ፣ 16አለቃ ቆራ፣ አለቃ ጋዕታም፣ አለቃ አማሌቅ፤ እነዚህ በኤዶም ምድር የኤልፋዝ አለቆች ናቸው፤ እነዚህ የዓዳ ልጆች ነበሩ። 17የዔሳው ልጅ የራጉኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፤ አለቃ ናሖት፣ አለቃ ዛራ፣ አለቃ ሳማ፣ አለቃ ሚዛ። እነዚህ በኤዶም ምድር የራጉኤል አለቆች ናቸው። እነዚህ የዔሳው ሚስት የባሥማት ልጆች ናቸው። 18የዔሳው ሚስት የአህሊባማ ልጆች፤ አለቃ የዑስ፣ አለቃ ያላም፣ አለቃ ቆራ። እነዚህ የዓና ልጅ የሆነችው የዔሳው ሚስት የአህሊባማ አለቆች ናቸው። 19እነዚህ የዔሳው (ማለትም የኤዶም) ልጆች ናቸው፤ አለቆቻቸውም እነዚህ ናቸው።
20በምድሪቱ ይኖሩ የነበሩት የኦሪያዊው የሴይር ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሎጣን፣ ሦባል፣ ሲብዖን፣ ዓና፣ 21ዲሶን፣ ኤጽር፣ ዲሳን። እነዚህ በኤዶም ምድር ያሉት የሴይር ልጆች የኦሪያውያን አለቆች ናቸው። 22የሎጣን ልጆች ሖሪና ሄማም ነበሩ፤ የሎጣንም እኅት ተምናዕ ነበረች። 23የሦባል ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ዐልዋን፣ ማናሃት፣ ዔባል፣ ሴፎና ዖናም። 24የሲብዖን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ አያና ዓና። የአባቱን የሲብዖንን አህዮች ሲጠብቅ በምድረ በዳ ፍል ውሃ ያገኘው ይህ ዓና ነው። 25የዓና ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ዲሶንና የዓና ልጅ አህሊባማ። 26የዲሶን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሐምዳን፣ ኤሽባን፣ ይትራንና ካራን። 27የኤጽር ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ቢልሃን፣ ዛዋንና ዓቃን። 28የዲሳን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ዑፅና አራን። 29የኦሪያውያን አለቆች እነዚህ ናቸው፤ አለቃ ሎጣን፣ አለቃ ሦባል፣ አለቃ ሲብዖን፣ አለቃ ዓና፣ 30አለቃ ዲሶን፣ አለቃ ኤጽር፣ አለቃ ዲሳን። እነዚህ በሴይር ምድር ባላቸው ነገድ መሠረት የኦሪያውያን አለቆች ናቸው።
ከእስራኤል ነገሥታት በፊት የነገሡ ነገሥታት
31በእስራኤላውያን ላይ ማንም ንጉሥ ከመንገሡ በፊት በኤዶም ምድር የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ናቸው፤ 32የቢዖር ልጅ ቤላ በኤዶም ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዲንሐባ ነበረ። 33ቤላ በሞተ ጊዜ የባሶራው የዛራ ልጅ ዮባብ በእርሱ ቦታ ነገሠ። 34ዮባብ በሞተ ጊዜ ከቴማናውያን ምድር የመጣው ሔሳም በእርሱ ቦታ ነገሠ። 35ሔሳም ሞተ፤ በሞዓብ ምድር ምድያምን ድል ያደረገው የበዳድ ልጅ ሐዳድ በእርሱ ቦታ ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዓዊት ተባለ። 36ሐዳድ በሞተ ጊዜ የማስሬቃው ሳምላ በእርሱ ቦታ ነገሠ። 37ሳምላ በሞተ ጊዜ በኤፍራጥስ አጠገብ ካለችው ከሬሆቦት የመጣው ሳኦል በእርሱ ቦታ ነገሠ። 38ሳኦል በሞተ ጊዜ የዐክቦር ልጅ በኣልሐናን በእርሱ ቦታ ነገሠ። 39የዐክቦር ልጅ በኣልሐናን በሞተ ጊዜ ሐዳር በእርሱ ቦታ ነገሠ፤ የከተማው ስም ፋዑ ነበረ፤ የሚስቱም ስም የሜዛሃብ ልጅ የሆነችው የማጥሬድ ልጅ ሜጤቤል ነበረ።
40በነገዳቸው፣ በቦታቸውና በስማቸው መሠረት የዔሳው አለቆች እነዚህ ናቸው፤ አለቃ ተምናዕ፣ አለቃ ዐልዋ፣ አለቃ ይቴት፣ 41አለቃ አህሊባማ፣ አለቃ ኤላ፣ አለቃ ፊኖን፣ 42አለቃ ቄኔዝ፣ አለቃ ቴማን፣ አለቃ ሚብሳር፣ 43አለቃ መግዲኤልና አለቃ ዒራም። በያዙት ምድር በሰፈሩበት ስፍራ መሠረት የኤዶም አለቆች እነዚህ ናቸው። ዔሳው የኤዶማውያን አባት ነበረ።