ስለ እግዚአብሔር የሚነገሩ ቃሎች
ኤሊሁ ስለ እግዚአብሔር ይናገራል፤ መከራ ተግሣጽ ነው፣ ጆሮ የሚከፈትበት ነው፣ ኢዮብም ወደ ሰፊ ስፍራ ሊሳብ ይችል ነበር። ከዚያም ቃናው ወደ መደነቅ ይለወጣል፤ ከጉም የሚንጠባጠብ ዝናብ፣ ነጎድጓድ፣ ወደ ዒላማው የተወረወረ መብረቅ። እግዚአብሔር ታላቅ ነው፣ እኛም አናውቀውም።
36 1ኤሊሁም እንዲህ ሲል ቀጠለ፦ 2“ጥቂት ታገሠኝ፤ አሳይሃለሁና፤ ስለ እግዚአብሔር ለመናገር ገና ቃሎች አሉና። 3ዕውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፤ ለፈጣሪዬም ጽድቅን እሰጣለሁ። 4በእውነት ቃሎቼ ሐሰት አይደሉምና፤ በዕውቀት ፍጹም የሆነ ከአንተ ጋራ ነው። 5እነሆ፣ እግዚአብሔር ኀያል ነው፤ ነገር ግን ማንንም አይንቅም፤ በማስተዋል ብርታት ኀያል ነው። 6ክፉዎችን በሕይወት አያኖርም፤ ለተጨነቁትም ፍርድን ይሰጣል። 7ዓይኖቹን ከጻድቃን ፈጽሞ አያነሣም፤ ከነገሥታት ጋራ በዙፋናቸው ላይ ለዘላለም ያስቀምጣቸዋል፤ ከፍ ከፍም ይላሉ። 8በሰንሰለት ቢታሰሩ፣ በመከራ ገመድ ቢያዙ፣ 9ሥራቸውንና ዐመፃቸውን፣ በትዕቢት እንደ ተመላለሱ ይነግራቸዋል። 10ጆሮአቸውን ለተግሣጽ ይከፍታል፤ ከኀጢአትም እንዲመለሱ ያዝዛል። 11ቢሰሙና ቢያገለግሉት፣ ዘመናቸውን በበረከት ይፈጽማሉ፤ ዓመታቸውም በደስታ ያልፋል። 12ባይሰሙ ግን በሰይፍ ይጠፋሉ፤ ያለ ዕውቀትም ይሞታሉ። 13በልባቸው ዓመፀኞች የሆኑ ቍጣን ይሰበስባሉ፤ ባሰራቸውም ጊዜ ለእርዳታ አይጮኹም። 14ነፍሳቸው በወጣትነት ትሞታለች፤ ሕይወታቸውም በቤተ ጣዖት ሴሰኞች መካከል ያልቃል። 15የተጨነቁትን በመከራቸው ያድናል፤ በጭንቀትም ጆሮአቸውን ይከፍታል። 16አንተንም ከጭንቀት አፍ አውጥቶ ጥበት ወደሌለበት ሰፊ ክፍት ስፍራ ያደርስህ ነበር፤ ገበታህም በሥብ ይሞላ ነበር። 17አንተ ግን ለክፉዎች በተገባ ፍርድ ተይዘሃል፤ ፍርድና ፍትሕ ጨብጠውሃል። 18ቍጣ ወደ ፌዝ እንዳያታልልህ ተጠንቀቅ፤ ታላቅ ቤዛም እንዳያስትህ። 19ጩኸትህ ከጭንቀት ይጠብቅሃልን? ወይስ የብርታትህ ኀይል ሁሉ? 20ሌሊትን አትናፍቅ፤ ሕዝቦች ከስፍራቸው የሚወገዱበትን። 21ተጠንቀቅ፤ ወደ ኀጢአት አትመለስ፤ ከመከራ ይልቅ ይህን መርጠሃልና። 22እነሆ፣ እግዚአብሔር በኀይሉ ከፍ ከፍ ይላል፤ እንደ እርሱ መምህር ማን ነው?
23“መንገዱን ማን አዘዘለት? ወይስ፣ ‘በደል አድርገሃል’ ሊል የሚችል ማን ነው? 24ሰዎች በመዝሙር ያከበሩትን ሥራውን ከፍ ከፍ ለማድረግ አስብ። 25ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፤ ሰውም ከሩቅ ያየዋል። 26እነሆ፣ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እኛም አናውቀውም፤ የዘመኑ ቍጥር ከምርመራ በላይ ነው። 27የውሃውን ጠብታዎች ይስባልና፤ ከጉሙም ዝናብ ሆነው ይንጠባጠባሉ፤ 28ደመናትም ያፈሱታል፤ በሰዎችም ላይ አትረፍርፈው ያዘንቡታል። 29የደመናትን መዘርጋት፣ የድንኳኑንም ነጐድጓድ ሊያስተውል የሚችል አለን? 30እነሆ፣ መብረቁን በዙሪያው ይበትናል፤ የባሕሩንም ጥልቅ ይሸፍናል። 31በእነዚህ ሕዝቦችን ያስተዳድራልና፤ ምግብንም አትረፍርፎ ይሰጣል። 32እጆቹን በመብረቅ ይሞላል፤ ዒላማውንም እንዲመታ ያዝዘዋል። 33ጩኸቱ ስለ እርሱ ይናገራል፤ ከብቶች እንኳ ማዕበሉ መምጣቱን ያውቃሉ።”