አባት ያስጠነቅቃል፦ ከኢየሩሳሌም ሽሹ
ኤርምያስ ከበባው ሲጠብቅ ያያል፤ መሪዎችም ባላከሙት ቍስል ላይ ሰላምን ተስፋ ሲሰጡ ይሰማል። አብ አንድ መውጫ ያቀርባል፤ በመንታ መንገድ ላይ ቁሙ፣ የጥንቱን መንገድ ጠይቁ፣ በእርሱም ሂዱ። ሕዝቡ አንሄድም ብለው ይመልሳሉ። እርሱም የተጣለ ብር ብሎ ይጠራቸዋል።
6 1“እናንተ የብንያም ልጆች ሆይ፣ ከኢየሩሳሌም ወጥታችሁ ለደኅንነታችሁ ሽሹ! በቴቁሐ መለከትን ንፉ፤ በቤትሃኬሬምም ላይ ምልክት አንሡ፤ ከሰሜን መዓት፣ ታላቅ ጥፋት ያንዣብባልና። 2ውቢቱንና ናዛዋን የጽዮንን ሴት ልጅ አጠፋታለሁ። 3እረኞች ከመንጎቻቸው ጋር ይመጡባታል፤ በዙሪያዋ ድንኳኖቻቸውን ይተክላሉ፤ እያንዳንዱም የራሱን ድርሻ ያሰማራል።”
4በእርሷ ላይ ለጦርነት ተዘጋጁ! ኑ፣ በቀትር እናጥቃት! ነገር ግን ወዮልን፣ ቀኑ እያለፈ ነውና፤ የማታውም ጥላ እየረዘመ ነው። 5ኑ፣ በሌሊት እናጥቃት፤ ምሽጎቿንም እናፍርስ!
6የሰማይ ሠራዊት አባት እንዲህ ይላልና፦ ዛፎቿን ቍረጡ፤ በኢየሩሳሌም ላይ የከበባ ዐምባ ሥሩ። ይህች ከተማ መቀጣት አለባት፤ በውስጧ ከጭቈና በቀር ሌላ ነገር የለም። 7“ጕድጓድ ውሃውን ትኵስ አድርጎ እንደሚጠብቅ፣ እርሷም ክፋቷን እንዲሁ ትኵስ አድርጋ ትጠብቃለች። ዐመፅና ጥፋት በውስጧ ያስተጋባል፤ ደዌና ቍስልም ሁልጊዜ በፊቴ ናቸው። 8ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ተገሠጺ፤ አለዚያ በመጸየፍ ከአንቺ እርቄ ባድማ አደርግሻለሁ፤ ማንም የማይኖርባት ምድርም አደርግሻለሁ።”
9የሰማይ ሠራዊት አባት እንዲህ ይላል፦ ወይን ፈጽሞ እንደሚለቀም የእስራኤልን ቀሪዎች ይለቅማሉ። ፍሬ እንደሚሰበስብ ሰው፣ እጅህን መልሰህ በቅርንጫፎቹ ላይ አሳልፍ።
10“ይሰሙኝ ዘንድ ለማን ተናግሬ አስጠነቅቅ ዘንድ እችላለሁ? ጆሮዎቻቸው ተዘግተዋል፤ ስለዚህ ሊሰሙ አይችሉም። የአባታችን ቃል ለእነርሱ የሚያስከፋ ሆኖባቸዋል፤ በእርሱም ደስ አይሰኙም።
11እኔ ግን በአባታችን ቍጣ ተሞልቻለሁ፤ ይዤው ለመቆየትም ደክሞኛል። በመንገድ ላይ ባሉ ሕፃናት ላይ፣ በተሰበሰቡት ጐበዛዝት ላይ አፍስሰው፤ ባልና ሚስት፣ ሽማግሌውና ዕድሜ የገፋው ሁሉ ተማርከው ይወሰዳሉ።” 12ቤቶቻቸው ለሌሎች ይሰጣሉ፤ እርሻዎቻቸውና ሚስቶቻቸውም አብረው ይወሰዳሉ፤ በምድሪቱ በሚኖሩት ላይ እጄን እዘረጋለሁና፣ ይላል አባታችን። 13ከታናሹ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉም ዓመፀኛ ረብ ይስገበገባሉ፤ ከነቢዩ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉም ሽንገላን ይፈጽማሉ። 14የሕዝቤን ቍስል ከባድ እንዳልሆነ አድርገው ያክማሉ። ሰላም በሌለበት ጊዜ፣ ‘ሰላም፣ ሰላም’ ይላሉ። 15በሠሩት አስጸያፊ ድርጊት ዐፈሩን? አይ፣ ከቶ አላፈሩም፤ ማፈርም እንኳ አያውቁም። ስለዚህ ከወደቁት መካከል ይወድቃሉ፤ በምቀጣቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፣ ይላል አባታችን።
16አባታችን እንዲህ ይላል፦ በመንገዶች መገናኛ ላይ ቁሙና ተመልከቱ፤ የቀደሙትን መንገዶች ጠይቁ፤ መልካሙ መንገድ የት እንደ ሆነ ጠይቁ፤ በእርሱም ተመላለሱ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ። እነርሱ ግን፣ ‘በእርሱ አንመላለስም’ አሉ። 17በላያችሁ ጠባቂዎችን ሾምሁ፤ እንዲህም አልሁ፦ ‘የመለከቱን ድምፅ አድምጡ!’ እነርሱ ግን፣ ‘አናደምጥም’ አሉ። 18“ስለዚህ እናንተ አሕዛብ ሆይ፣ ስሙ፤ እናንተ ምስክሮችም፣ በእነርሱ ላይ የሚሆነውን ዕወቁ። 19ምድር ሆይ፣ ስሚ፦ በዚህ ሕዝብ ላይ መዓትን አመጣለሁ፤ ይህም የራሳቸው ተንኰል ፍሬ ነው፤ ቃሌን ስላልሰሙ፣ ሕጌንም ስለ ናቁ ነው። 20ከሳባ ስለሚመጣ ዕጣን ለኔ ምን ያገባኛል? ከሩቅ ምድር ስለሚመጣስ ጣፋጭ ሸንበቆ? የሚቃጠለው መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት የለውም፤ መሥዋዕቶቻችሁም ደስ አያሰኙኝም።”
21ስለዚህ አባታችን እንዲህ ይላል፦ በዚህ ሕዝብ ፊት መሰናክሎችን አኖራለሁ። አባቶችና ልጆች በእነርሱ ይሰናከላሉ፤ ጎረቤቶችና ወዳጆችም ይጠፋሉ።
22አባታችን እንዲህ ይላል፦ እነሆ፣ ከሰሜን ምድር ሠራዊት ይመጣል፤ ታላቅ ሕዝብም ከምድር ዳርቻ ይነሣሣል። 23ቀስትንና ጦርን ይዘዋል፤ ጨካኞች ናቸው፤ ምሕረትም የላቸውም። ድምፃቸው እንደ ባሕር ይጓራል፤ በፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይጋልባሉ፤ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ አንቺን ለመውጋት ለጦርነት ተሰልፈዋል።
24ወሬያቸውን ሰምተናል፤ እጆቻችንም ዝለው ተንጠልጥለዋል። ጭንቀት ይዞናል፤ እንደ ምጥ ሴት ሥቃይም ተሰምቶናል። 25ወደ እርሻ አትውጡ፤ በመንገድም ላይ አትሂዱ፤ ጠላት ሰይፍ አለውና፤ ድንጋጤም በየአቅጣጫው ነው። 26የሕዝቤ ሴት ልጅ ሆይ፣ ማቅ ልበሺ፤ በዐመድ ላይም ተንከባለዪ፤ አንድ ልጅ እንደሞተባት ሁሉ መራራ ልቅሶ አልቅሺ፤ አጥፊው በድንገት ይመጣብናልና።
27“በሕዝቤ መካከል የማዕድን ፈታኝ አድርጌ ሾምሁህ፤ መንገዳቸውን ታስተውልና ትፈትን ዘንድ ነው። 28ሁሉም እልከኛ ዓመፀኞች ናቸው፤ ሐሜትን እያናፈሱ ይዞራሉ። ናስና ብረት ናቸው፤ ሁሉም ጠማማ ሥራ ይሠራሉ። 29ወናፉ በኀይል ይነፋል፤ እርሳሱን በእሳት ለማቃጠል፤ ነገር ግን ማንጠሩ ከንቱ ነው፤ ክፉዎች አልተለዩምና። 30የተጣለ ብር ይባላሉ፤ አባታችን ጥሏቸዋልና።”