አባታችን በጎግ ላይ ይናገራል
የማጎጉ ጎግ በመንጋጋው በገቡ መንጠቆዎች ተመልሶ ሊዘርፋት ባቀዳት፣ ሰው እንደገና በሰፈረባትና ቅጥር በሌላት ምድር ላይ ይሳባል። ነጋዴዎች ምርኮ ልትወስድ መጥተሃልን? ብለው ይጠይቃሉ። አብ ወረራው የገዛ ሥራው እንደ ሆነ ይናገራል፤ ምድርም ራሷ ትናወጣለች።
38 1የአባታችን ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦
2የሰው ልጅ ሆይ፣ በማጎግ ምድር ወደ ሚኖረው፣ የሞሳሕና የቶቤል ዋና አለቃ ወደ ሆነው ወደ ጎግ ፊትህን አዙር፤ በእርሱም ላይ ትንቢት ተናገር። 3እንዲህም በል፦ ጌታ አባታችን እንዲህ ይላል፤ “የሞሳሕና የቶቤል ዋና አለቃ ጎግ ሆይ፣ እኔ በአንተ ላይ ነኝ። 4አዙሬ እመልስሃለሁ፤ በመንጋጋህም መንጠቆ አግብቼ፣ አንተንና ሰራዊትህን ሁሉ አወጣሃለሁ፤ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፣ ሁሉም ጦር የለበሱ፣ ትልቅና ትንሽ ጋሻ የያዙ ብዙ ሰራዊት፣ እያንዳንዳቸውም ሰይፍ የጨበጡ ናቸው። 5ፋርስ፣ ኩሽና ፉጥ ከእነርሱ ጋር ናቸው፤ ሁሉም ጋሻና የራስ ቍር የታጠቁ ናቸው፤ 6ጎሜር ከነሰራዊቱ ሁሉ፣ ከሩቅ ሰሜንም ቤትቶጋርማ ከነሰራዊቱ ሁሉ ከአንተ ጋር ናቸው፤ ብዙ ሕዝቦችም ከአንተ ጋር ናቸው።
7ተዘጋጅ፤ አንተና በዙሪያህ የተሰበሰቡት ሰራዊት ሁሉ ተዘጋጁ፤ ለእነርሱም ጠባቂ ሁን። 8ከብዙ ቀናት በኋላ ትጠራለህ። በኋለኞቹ ዓመታት ከጦርነት ወደ ተመለሰች ምድር ትወርራለህ፤ ሕዝቧ ለረጅም ዘመን ባድማ ሆነው ወደ ነበሩት የእስራኤል ተራሮች ከብዙ አሕዛብ ተሰብስበዋል። ከአሕዛብም መካከል ወጥተው አሁን ሁሉም በደኅንነት ይኖራሉ። 9አንተም ትወጣለህ፤ እንደ ዐውሎ ነፋስ እየገሰገስህ ምድሪቱን እንደሚሸፍን ደመና ትሆናለህ፤ አንተና ሰራዊትህ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝቦች ትሆናላችሁ።”
10ጌታ አባታችን እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ቀን በልብህ ሐሳቦች ይመጣሉ፤ ክፉ ተንኰልም ታውጠነጥናለህ። 11እንዲህም ትላለህ፤ ‘ቅጥር ወደ ሌላቸው መንደሮች ምድር እወጣለሁ፤ በደኅንነት በሚኖር ሰላማዊ ሕዝብ ላይ እዘምታለሁ፤ ሁሉም ቅጥር፣ መወርወሪያ ወይም በር የሌላቸው ናቸው፤’ 12ብዝበዛና ምርኮ ለመማረክ፣ እንደ ገና በተቋቋሙ ፍርስራሾች ላይና ከአሕዛብ በተሰበሰበው ሕዝብ ላይ ለመዝመት ነው፤ ይህ ሕዝብ ከብትና ንብረት አፍርቷል፤ በምድርም እምብርት ላይ ይኖራል። 13ሳባ፣ ድዳንና የተርሴስ ነጋዴዎች ከወጣት አንበሶቿ ሁሉ ጋር፣ ‘ምርኮ ለመማረክ መጣህን? ብርና ወርቅ ለመውሰድ፣ ከብትና ንብረት ለመማረክ፣ ታላቅ ብዝበዛም ለመዝረፍ ሰራዊትህን ሰበሰብህን?’ ብለው ይጠይቁሃል።”
14ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፣ ትንቢት ተናገር፤ ጎግንም እንዲህ በለው፦ ጌታ አባታችን እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል በደኅንነት በሚኖርበት ጊዜ፣ አታውቀውምን? 15አንተና ከአንተ ጋር ያሉ ብዙ ሕዝቦች ከሩቅ ሰሜን ካለው ስፍራህ ትመጣላችሁ፤ ሁሉም ፈረስ የተቀመጡ፣ ታላቅ ሰራዊት፣ ኀያል ጭፍራ ናችሁ። 16ምድሪቱን እንደሚሸፍን ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። ጎግ ሆይ፣ በመጨረሻው ዘመን በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ፤ በአንተም በኩል በዓይናቸው ፊት ቅዱስ መሆኔን ባሳይ ጊዜ አሕዛብ ያውቁኛል።”
17ጌታ አባታችን እንዲህ ይላል፤ በጥንት ዘመን በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያት በኩል የተናገርሁት አንተ አይደለህምን? በዚያ ዘመን በእነርሱ ላይ እንዳመጣህ ለዓመታት ትንቢት ተናግረዋልና። 18በዚያ ቀን፣ ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በሚዘምትበት ጊዜ፣ የተቀጣጠለ ቍጣዬ ይነድዳል፣ ይላል ጌታ አባታችን። 19“በቅናቴና በቍጣዬ እሳት እንዲህ ብዬ ተናግሬአለሁ፤ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ላይ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል። 20የባሕር ዓሦች፣ የሰማይ ወፎች፣ የምድረ በዳ አራዊት፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀስ ተንቀሳቃሽ ሁሉ፣ በምድርም ላይ ያለ ሰው ሁሉ በፊቴ ይንቀጠቀጣሉ። ተራሮች ይደረማመሳሉ፣ ገደሎች ይፈራርሳሉ፣ ቅጥርም ሁሉ መሬት ላይ ይወድቃል።” 21በተራሮቼ ሁሉ ላይ በጎግ ላይ ሰይፍ እጠራለሁ፣ ይላል ጌታ አባታችን፤ የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይዞራል። 22“በቸነፈርና በደም ማፍሰስ እፈርድበታለሁ፤ በእርሱና በሰራዊቱ፣ ከእርሱም ጋር ባሉ ብዙ ሕዝቦች ላይ ዶፍ ዝናብ፣ የበረዶ ድንጋይ፣ እሳትና ዲን አዘንባለሁ። 23እንዲህም ታላቅነቴንና ቅድስናዬን አሳያለሁ፤ በብዙ አሕዛብም ፊት ራሴን አስታውቃለሁ። ያን ጊዜ እኔ አብ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”